Get Mystery Box with random crypto!

ከእስራትህ ውጣ! ጥፋተኛ ስለሆንክ ላትታሰር ትችላለህ፤ ስለበደልክ፣ ስለጎዳህ ወህኒ ላትወርድ ትች | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ከእስራትህ ውጣ!

ጥፋተኛ ስለሆንክ ላትታሰር ትችላለህ፤ ስለበደልክ፣ ስለጎዳህ ወህኒ ላትወርድ ትችላለህ፤ ነገር ግን ባለማወቅም ይሁን በሃሰት ልትታሰር ትችላለህ፤ የአካል እስራትህ ግን ነፃ የሆነውን አዕምሮህን ሊያስረው አይችልም። የትኛውም ነፃነት ከአስተሳሰብህ ይነሳል፤ ከሁነኛው አቋምህ ይመነጫል፤ ከማንነትህ ይመጣል። አጠፋህ አላጠፋህ፣ ጎዳህ አልጎዳህ ሰዎች ከሚሰጡህ የአጥፊነትና የክፋት ስም ይልቅ አንተ ለእራስህ የምትሰጠው የንፅህናና የመልካምነት ስም ይልቃል። ለእራስህ ባለህ አቋም አንድ ልትወድቅ ትችላለህ፤ ሌላም ከቀድሞ በተሻለ ቀና ብለህ መታየት ትችላለህ። የአስተሳሰብህን ሃይል በመጣህበት የህይወት ጉዞ ውስጥ መመልከት ይኖርብሃል። ብትወድቅ የውድቀትህ መንስኤ ምንድነው? ብትታሰር ያሰረህ ማነው?

አዎ! ጀግናዬ..! ማንም ይሰርህ ማን፣ ማንም ይጣልህ ማን አንተ ግን ጊዜ ሳታጠፋ ከእስራትህ ውጣ፤ እራስህን ነፃ አውጣ። ያለጥፋትህ ላሰሩህ፣ ለጉዳት ለዳረጉህ፣ ጠብቀው ላደቡብህ ከልብህ ይቅር በማለት ከቂም እስራት ነፃ ሁን፤ ከጥፋተኝነት አጥር ውጣ። አስሬ ሰዎች ያደረጉብህን ደጋግመህ ብታስብ ሰዎቹን ከመጉዳት ይልቅ በፍቃድህ እራስህን መጉዳት፣ ማሰርና ማሳዘን ትጀምራለህ። የፈረዱብህ ላይ ለመፍረድ እስካልተጣደፍክ ድረስ፣ ለእራስህ ነፃነት እስካሰብክ ድረስ፣ የይቅርታ ልብ አስከኖረህ ድረስ ባላጠፋሀው መወንጀልህ፣ ባልሆንከው መጠራትህ፣ በማይገልፅህ መወከልህ ምንም አይደለም። ወደኋላ ቢያስቀርህም በንፁው ልቦናህ የተረጋጋና አስደሳች ህይወትን ያጎናፅፍሃል።

አዎ! የነፃነት መሳሪያህ አስተሳሰብህ ነው። በአስተሳሰብህ ከታሰርክ፣ እራስህን ከገደብክ፣ አቅምህን ካሳነስክ፣ በእራስመተማመን ከተሳነክ ብዙዎች ቢደግፉህ፣ ብዙዎች ቢያምኑብህ፣ ብዙዎች ቢያበረታቱህ እንኳን የትም መሔድ አትችልም። አቅምህ በአመለካከትህ ፍቃድ የሚወጣ ነው፤ ትክክለኛው ማንነትህ ካንተ አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ ነው። ከምንም ተፅዕኖ ነፃ ለመውጣት ከመታገልህ በፊት እየጎዳህ ካለው ከገዛ አሉታዊ አመለካከትህ ነፃ ውጣ፤ ሃሳብህ ላይ ሰልጥን፤ እራስህን መግዛት ጀምር፤ ትናንትን በይቅርታ የምትሽር፣ ወደፊት ለመራመድ የፈጠንክ፣ እራስህ ላይ የሰለጠንክ ብርቱና ጠንካራ ሰው ለመሆን ሞከር። አንተ ያልፈታሀውን እስር ማንም ቢመጣ ሊፈታልህ እንደማይችል አስተውል።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q