Get Mystery Box with random crypto!

በልክ አድርጊው! አዎ! እዳሽን አታብዢ፣ ሌላ የቤት ስራ እራስሽ ላይ አትጨምሪ፤ እንደ አቅምሽ፣ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

በልክ አድርጊው!

አዎ! እዳሽን አታብዢ፣ ሌላ የቤት ስራ እራስሽ ላይ አትጨምሪ፤ እንደ አቅምሽ፣ እንደ ማንነትሽ መኖር ጀምሪ። ልህቀትሽ ሲጨምር፣ አስተውሎትሽ ከፍ ሲል፣ መለወጥሽ ትርጉም ሲያገኝ ድካምሽ የእነርሱን ስህተት ለማረጋገጥ ሳይሆን የእራስሽን ልክነት፣ የእራስሽን በተገቢው ስፍራ መገኘት ለእራስሽ ማረጋገጥ ይሆናል። ለህይወትሽ መበላሸት ወይም እንደፈለግሽው አለመሆን ሃላፊነት ሊወስዱ የሚገባቸው አካላት ቢኖሩም ለእራስሽ የምታዝኚና የምታስቢ ከሆነ ግን ጣትሽን ማንም ላይ መቀሰር አቁመሽ እራስሽ ላይ መስራትና እራስሽን መቀየር ትጀምሪያለሽ። የእራስሽ ደስታ እራስሽ መሆን እስከፈለግሽ ድረስ ለማንም ብለሽ እራስሽን መውቀስ አቁሚ።

አዎ! ጀግኒት..! በልክ አድርጊው! የእራስ ወቀሳውን፣ አራስን መተቸቱን፣ በትንሹም በትልቁም እራስን መክሰሱን፣ ሁሌም እራስ ላይ ፊት ማዞሩን፣ እራስ ላይ መጨከኑን መጠን አብጂለት፣ ልኬት ስጪው። እራስሽን የምታብጠየጥይው ለመኮነን ወይስ ለመፅደቅ ነው? እራስሽን ከማንም እንዳነሰ፣ እንደ ምንም የምትመለከቺው ማን እንዲወድሽ ነው? "እኔ አልችልም፣ እኔ ይሔ አይገባምኝም፣ እኔ ይሔ ነገር ያስፈራኛል" የምትይው ከማን አድናቆትና ሙገሳን ለማግኘት ነው? በየጊዜው እራስሽ ላይ የትቺት ናዳ እያወረድሽባት፣ ያለእረፍት እየወቀስሻት፣ ያለምንም እረፍት እያስጨነቅሻት እንዴት ደስተኛ እንድትሆን ትጠብቂያለሽ? የቀማሻትን ቀምተሻት፣ ማንነቷን አሳጥተሽ፣ ሰላሟን አጥፍተሽ፣ ከአንድ ሰው ወይም ከቁስ ጋር አዋህደሻት እንዴት በእራሷ ደስተኛና የተረጋጋች ሴት እንድትሆን ትመኚያለሽ? ውጪውን ለአፍታ ተወት አድርጊው፣ የሚመለከቱሽን፣ የሚያደንቁሽን፣ የሚወዱሽን ሰዎች ለጊዜ ተወት አድርጊያቸው። እራስሽን አዳምጪ፤ ለእራስሽ ይቅርታ አድርጊ።

አዎ! ጀግናዬ..! ለእራስህ እዘንለት፤ ከልብህ አዳምጠው፤ ውስጡን ተመልከተው። ለእራስህ ጊዜ የሰጠሀው፣ ውስጥህን ያዳመጥከው፣ ህመምህን በእራስህ ለማከም የሞከርከው፣ ወደ ውስጥህ የተመለከትከው፣ ሽክሞችህን ያስተዋልከው መቼ ነበር? ከህይወት ጡዘት ፋታ ሳትወስድ፣ አንዴም ለእራስህ ጊዜ ሳትሰጥ፣ የግል ጥያቄህን ሳትመልስ  ሌላ የእራሱ ጥያቄ ያለውን ሰው ለመወዳጀት አትቸኩል። ለእራስህ ጉዳይ ጊዜ ይኑርህ፤ ለእራስህ የግል ጥያቄ ትኩረት ስጥ፤ አስቀድመህ እርሱን መልስ። ከምንም በላይ ህመምህን ለማከም ከአምላክህ በቀር የማንንም እርዳታ አትጠብቅ። የህይወትን እጥረት አስተውል፤ እራስህን እያሳቀክና እያስጨነክ ይባስ አጨርና ዋጋ ቢስ አታድርጋት። ለእራስህ ደስታና መረጋጋት ስትል በፈለከው መንገድ በነፃነት ኑራት።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q