Get Mystery Box with random crypto!

ነፃ ሁን! ይህ ህይወት እንጂ ትግል አይደለም ፤ የምትኖረው እንጂ በሆነው ባልሆነው እየተጨ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ነፃ ሁን!

ይህ ህይወት እንጂ ትግል አይደለም ፤ የምትኖረው እንጂ በሆነው ባልሆነው እየተጨነክ እራስህን የምትጎዳበት አይደለም ፤ በረከቶችህን እየቆጠርክ የምትደሰትበት እንጂ የለኝም በምትላቸው ነገሮች የምታማርርበት አይደለም ። በምስጋና ስትመላለስ ንዴትና ብስጭት ቦታ አያገኙም ፤ የህይወትን መልካምነት ስትቀበል ችግሮችህ በሚሒደት ይቀረፋሉ ፤ ነፃ ሆነህ ማሰብ ፣ መኖርና የፈለከውን ማድረግ ስትጀምር ከባቢህ በሙሉ ሰላምና ፍቅር ይሆናል ። እንዳለመታደል ሆኖ ህይወታችንን የምናከብደው እራሳችን ነን ፤ ትንሿን ክፍተት እናጎላለን ፤ ውድቀትን እንደ ሞት እናየዋለን ፤ ተቀባይነት ማጣት በተሳሳተ መንገድ እየተጓዝን እንዳለን እንድናስብ ያደርገናል ፤ ሁሉም ሰው በሃሳባችን ካልተስማማ ትክክል የሆንን አይመስለንም ፤ ሁሌም በማጣትና በችግሮች ውስጥ እንደምንኖር ፣ ዛሬ ያጣነውን ነገ እንደማናገኝ ፣ ጊዜያዊው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ሁሌም እንደዛው እንደሚቀጥል እናስባለን ።

አዎ! ጀግናዬ..! ነፃ ሁን! ህይወት እንደ ወራጅ ወንዝ ነች ። በየመሃሉ ድንጋይና የተለያዩ መሰናክሎች ቢገጥሟትም እስከመዳረሻዋ ድረስ ደስበሚስ ፍሰት ጉዞዋን ትቀጥላለች ። ሁሉም ነገር አንድ ቀን እንደሚያበቃ እያሰብክ ህይወትህን በነፃነት ተመላለስባት ፤ አንድ መቋጫ እንደሚኖራት እያስታወስክ በሙላት ኑራት ፤ በፍቅር ተደሰትባት ፤ በሃሴት ተትረፍረፍባት ። እርግጥ ነው ብዙ የምትፈልገው ነገር የለህም ነገር ግን የሚያስፈልግህና የሚገባህ ነገር በእጅህ ላይ ነው ፤ በህይወት አለህ ፤ ጤነኛ ነህ ፤ የምትበላው አላጣህም ፤ አምላክህ አብሮህ አለ ፤ የሚያስብልህ ፈጣሪ አለህ ። ካጣሀው በላይ ያለህ ነገር እጅግ ብዙ ነው ። በምሬትም ይሁን በምስጋና ፣ በደስታም ይሁን በሃዘን ፣ በሳቅም ይሁን በለቅሶ ህይወት አንድ ቀን ፍፃሜ ይኖራታል ፤ ትናንት የነበረ ነገር ዛሬ ላይ ላይኖር ይችላል ፤ ዛሬ ላይ አብረውን የሆኑ ወዳጆቻችን ነገ ላይኖሩ ይችላሉ ። በህይወት ቋሚ ነገር የለም ፤ ሁሉም ነገር ተለዋዋጭ ፣ አላፊና ጠፊ ነው ።

አዎ! ለእራስህ ደረጃ አበጅ ፤ ልክህን አስቀምጥ ፤ መገለጫህ ቀላልና የተረጋጋ ህይወት እንዲሆን አድርግ ። ችግር አለ ፤ የሚያስጨንቅህ ጉዳይ ይኖራል ፤ እንቅልፍ የነሳህ ነገር አለ ፤ አንተ ግን ከእርሱ በላይ ነህ ፤ ቀዳሚው ያንተ መኖርና ያንተ ሰላም ፣ ደስታና ፍቅር ነው ። ህይወት ትግል ባይኖራት ጠዓም ታጣ ነበር ፤ ትግሏ ግን አብዝቶ ተስፋ የሚያስቆርጥ ፤ በምሬት የሚያሰቃይና ተስፋን የሚጨልም ከሆነ ገደብና ልኬት ሊበጀትለት ይገባል ። ለመኖር እንጂ ሙሉ ዘመንህን ለመሳቀቅና ለመሸማቀቅ ወደዚህ ምድር አልመጣህም ። የተፈጠርከው ለትርፍ ነው ፤ ትርፍህም ለእራስህ መልካም ሆነህ ለሰዎችም መድረስ መቻል ነው ። ህይወትህን መታገልህን አቁመህ መኖር ጀምር ፤ የሚያሳምምህን የተበዳይነት ስሜት ልቀቀው ፤ የሚያስጨንቅህን የሰዎች ትቺችና ዘለፋ ጣለው ፤ ከሚያሳዝንህ የጎደለ ነገር እራስህን ነፃ አድርግ ። ህይወትን ቀለል አድርገህ በአምላክህ መልካም በረከቶች በፍቅር ኑራት ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q