Get Mystery Box with random crypto!

ሃላፊነት ይሰማህ! ከእድሜህ በላይ እንደበሰልክና በጥበብ የምትመራ እንደሆንክ ከሚያመላክቱ ዋነኛ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ሃላፊነት ይሰማህ!

ከእድሜህ በላይ እንደበሰልክና በጥበብ የምትመራ እንደሆንክ ከሚያመላክቱ ዋነኛ መንስኤዎች ውስጥ አንደኛው ለእያንዳንዱ ነገር ሃላፊነት መውሰድ መቻልህ ነው። ብልህ ሰው ጣቱን ወደ ውጪ ከመቀሰሩ በፊት እራሱን ይመረምራል፤ ውስጡን ያያል፤ እራሱን ያጠናል። ምንም እንኳን ያሰበውን ነገር ማድረግ ያልቻለበት ውጫዊ ምክንያት ቢኖርም በሌላ አማራጭ መንገድ ባለመሞከሩ እራሱን ተጠያቂ ያደርጋል። ባንተ ድክመት ላመለጠህ እድል ማንንም ብትወቅስ ድክመትህን ከመጨመር ውጪ ትርፍ አይኖርህም። ብዙዎች ትችላለህ ከሚሉህ በላይ አንተ አልችልም ስላልክ ሳትችል ትቀራለህ። ለእራስህ የምትሰጠው ጭፍን አመለካከት የትልቁ ጉዞህ መሰናክል ሆኖ ታገኘዋለህ። ዞሮ ዞሮ ያለመቻልህና ተሽለህ ያለመገኘትህ ሃላፊነት በአንተ ላይ ይወድቃል።

አዎ! ጀግናዬ..! ሃላፊነት ይሰማህ፤ ተጠያቂነትን ወደ እራስህ አዙር፤ ለሆነብህ፣ ላጣሀውና ላመለጠህ ሁሉ ጣትህን እራስህ ላይ ቀስር። ሃላፊነትን ሸሽተህ አታመልጥም፤ ጣትህን በሌሎች ላይ እየቀሰርክ እራስህን አታድንም። ከመሸም ቢሆን ለውድቀትህና ለጥፋትህ ተጠያቂው እራስህ እንደሆንክ ይገባሃል። ማመን የማይገባህን ለማመንህ፣ መቀበል የሌለብህን ለመቀበልህ፣ እሺ ማለት ለሌለብህ እሺታን ለማብዛትህ፣ በትንሹ መጀመር እየቻልክ ላመጀመርህ፣ ችሎታው እያለህ ከኋላ የሚገፋህን ለመጠበቅህ ሃላፊነቱን የምትወስደው አንተ እንደሆንክ ይገለጥልሃል። እጅግ ብዙ እራስን ከመሆን የሚያግዱ፣ በእራስ መንገድ ከመጓዝ የሚመልሱ፣ ባመኑበት ሃሳብ እንዳይፀኑ፣ በጀመሩት አካሔድ እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉ አይነተኛ መሰናክሎች አይጠፋም። ነገር ግን እነርሱን ማስቀረት ባትችልም መቀነስ ትችላለህ።

አዎ! ለሆነው ነገር ሃላፊነት በወሰድክ ቅፅበት መቀየርና ማድረግ የምትችለው ነገር ላይ ማተኮር ትጀምራለህ፤ ያተኮርክበት ደግሞ በየጊዜው እያደገ ይመጣል። ብለሃትህን በምትችለው ነገር ላይ አውለው፤ እውቀትህን በመረጥከው ወሳኝና ጥቂት ነገር ላይ ተግብረው፤ ብስለትህን ሃላፊነትህን በአግባቡ በመወጣት አስመስክር። ጥበብ ከፈጣሪ ዘንድ ነው፤ ብስለትህም በመረዳት አቅምህ ልክ ነው። ሁሉም ሰው የአምላክ ጥበብ ማደሪያ ነው፤ ነገሮችን መመርመር፣ መረዳትና ማወቅ ደግሞ ማንኛውም ሰው በተሰጠው ጥበብ ተጠቅሞ የሚደርስበት ነገር ነው። ብስለትህ ሃላፊነትን በመውሰድና እራስን ተጠያቂ በማድረግ መንገድ እንዲያሳድግህ አድርግ፤ እወቀትህ በጥበበ፣ መረዳትህም በብለሃት እንዲተገበር ፍቃዱን ለእራስህ ስጥ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q