2018-12-31 18:49:20
በተማሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በአማራና በኦሮሞ ተማሪዎች መካከል #ግጭት እንዲነሳ ያስተባበሩ ተማሪዎችን ለ1 አመት ከትምህርት እንዲታገዱ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንዳስታወቀው በዩንቨርሲቲው ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ግጭት ተከስቶ ሁለት ቀናት የመማር ማስተማር ሂደቱ መቋረጡን ገልጸው የሌሎችን አላማ ለማሳካት ተልእኮ ወስደው በአማራና ኦሮሞ ተማሪዎች መካከል ግጭት እንዲነሳ ያደረጉ 10 ተማሪዎች ለአንድ አመት ከትምህርት እንዲታገዱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ግጭት በተከሰተበት ወቅት የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ጨምሮ በአካባቢውና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እርቀ ሰላም ለመፍጠር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች ለብጥብጡ መነሳት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ተማሪዎች ተለይተው ተመጣጣኝ እና አስተማሪ እርምጃ ይወሰድባቸው በሚል የአካባቢው ነዋሪዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያነሱትን ተደጋጋሚ ሀሳብ መነሻ በማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግ በዩንቨርስቲው በነበረው ግጭት አነሳሽ እና ባለቤት በመሆን ግጭቱን በመምራት ያስተባበሩ ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ህግ መሰረት ኮሚቴ በማዋቀርና በማጣራት 24 ተማሪዎችን በመለየት 10ሩ ለአንድ አመት ከትምህርት እንዲታገዱ፣ 5ቱ ከባድ የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 9ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በዩንቨርስቲው ሴኔት ውሳኔ አስተላልፏል።
አንድ አመት የተቀጡት ተማሪዎች ያጠፉት ጥፋት በዩኒቨርሲቲው ህግ መሰረት እድሜ ልክ ከትምህርት የሚያሰናብትና በማስጠንቀቂያ የታለፉትም ከሁለት ዓመት ያላነሰ ቅጣት የሚያስቀጣ ቢሆንም የሚከተሉት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን፦
1. ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታው ገፊ ምክንያት ስለሆነ
2. ተማሪዎች ወጣቶች በመሆናቸው ሌሎች ኃይሎች በቀላሉ ሊገፋፏቸው የሚችሉበት ሁኔታ ከፍተኛ ስለሆነ
3. ዩኒቨርሲቲው እርምጃውን ሲወስድ ዓላማው ማስተማር ብቻ ስለሆነ
4. ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በማብረዱና የነበረውን ሁኔታ በመመለሱ ረገድ ተማሪዎች ራሳቸው ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው በመሆኑና ሌሎችን ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ገልጾ የተቀጡ ተማሪዎች ቅጣታቸውን ጨርሰው ሲመለሱ መልካም ስነ ምግባር ያላቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ከሚኖሩበት ቀበሌ ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲው አጥፊ የሆኑ ተማሪዎች በጥፋታቸው መሰረት ባሉበት ዩኒቨርሲቲ ተገቢውን እርምት እንዲወስዱ ማድረግና ከሚኖሩበት ማህበረሰብ ጋር ተመሳስለው እና ተቻችለው እንዲኖሩ ማስተማር ሲገባ ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ እንዲዛወሩ ማድረግ መርህ አልባ አሰራር ከመሆኑ ባሻገር ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለሀገሪቱ መፍትሄ ነው ብሎ ዩኒቨርሲቲው እንደማያምን ገልጿል፡፡
ይሁን እንጅ ሰሞኑን ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከሌላ ቦታ የዝውውር ደብዳቤ ለአንድ ተማሪ ተጽፎለት አልቀበለው አለ በሚል አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነሻ ምክንያቱን ሳይረዱ የሚሰጡት ትችት አዘል አስተያየት ትክክል ነው ብሎ አያምንም ብሏል፡፡
ለእያንዳንዱ ችግር በስሜት የምንወስደው የመፍትሄ አማራጭ በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን የሰላማዊ መማር-ማስተማር እጦት ይበልጥ እያወሳሰበውና በሀገሪቱ የታየውን ተስፋ ለማጨለም ሌት ተቀን ለሚሰሩ አካላት ተጨማሪ ኃይል እንዳንሆናቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና ሁሉን ነገር በሰከነ መንገድ የማየት ልምድ ማዳበር አለብን ብሏል የሆነው ሆኖ ዩኒቨርሲቲው ተማሪውን ተቀብሎ ያስተናገደው መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ
ትምህርት ሚኒስቴር
@MINISTERY_OF_EDUCATION
94.7K viewsHENOK, 15:49