Get Mystery Box with random crypto!

ወር በገባ በ 21 ★★★እሳታዊው ሀያል አባት አቡነ ቀውስጦስ★★★ #አቡነ_ተክለ ሃይማኖት_ጋር_አ | መዝሙር ዘ ተዋህዶ

ወር በገባ በ 21
★★★እሳታዊው ሀያል አባት አቡነ ቀውስጦስ★★★
#አቡነ_ተክለ ሃይማኖት_ጋር_አብረው_አንድ_ቤት_ያደጉ
#470300_አጋንንትን_ከሰማይ_እሳት_በፀሎት_አውርደው_አቃጥለው_ህዝቡን_ያዳኑ
#በጦር_በተወጋው_ጎናቸው_በፈሰሰው_ደም_እኩለ_ሌሊቱን_ከፀሀይ_ሰባት_እጅ_በሚበልጥ_ብርሃን_የቀየሩት
#ዳዊታቸው_ክንፍ_አውጥታ_የበረረች
#በበትረ_መስቀላቸው_ፀበል_ያፈለቁ
#ሰባት_አክሊላትን_የተቸሩ
★ታላቁ ፃድቁ ሀያሉ እጅግ የከበረው የመሐግሉ ንቡረ እድ አቡነ ቀውስጦስ ከነገስታት ዘር ከሆኑት ከደጋጎቹ ገላውዴዎስ እና እምነ ፅዮን በሸዋ ክፍለ ሀገር ተወለዱ። ገላውዴዎስ እና እምነ ፅዮን ልጅ በማጣት ለእመቤታችን ብዙ ጊዜ ፀልየዋል ታድያ አንድ ቀን በታህሳስ 12 በሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ቀን ከእመቤታችን ስእለ አድኖ ስር ተደፍተው ሲፀልዩ ስእሏ አፍ አውጥታ « አንድ ልጅ አስቀድማችሁ ትወልዳላችሁ የሚወለደውም እኔ በተወለድኩበት ቀን ግንቦት 1 የሚያርፈውም እኔ ባረፍኩበት ቀን ጥር 21 ነው። እሱም የሰማያዊ ንጉስ ጭፍራ ይሆናል። ሁለተኛውም ለአስራት ሀገሬ ኢትዮጵያ ንጉስ ይሆናል ይህን ደግሞ ስሙን ይኩኖ አምላክ ይባላል ከእርሱም ጋር መልካም ሴት ትወልዳላችሁ» አለቻቸው። ከዚያም ግንቦት 1 1207 ዓም የኛ ውድ እና እንቁ የሆኑ አባት አቡነ ቀውስጦስ ተወለዱ።
★ አባታችን ገና ከመወለዳቸው አፋቸውን ፈትተው ሥላሴን አመስግነዋል እንዲሁም በህፃነነታቸው በእናታቸው ጀርባ ታዝለው ሳለ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም እንደዚሁ በእናታቸው ጀርባ ታዝለው ሲገናኙ ሁለቱ ፃድቆች እጃቸውን ተጨባበጡ ሆኖም ግን እጃቸውን እርስ በርስ ተጣብቆ ቀረ። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት ካህኑ ፀጋዘአብ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በፀሎት ቢጠይቅ ሊቀ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ «የኔ ወታደር ነው ከልጅህ ጋር ይደግ ቤት ውሰደው፤ ከንፅህናው የተነሳ ቁጥሩ ከመላእክት የተደመረ ነው ክብሩ ታላቅ ነውና» አለው ከዚያም በአንድ ቤት አብረው አደጉ።
★ ፃድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ የዚህን አለም ደስታና ተድላ ጣዕም ንቀው ፈለገ ሀዋርያትን ተከትለው በሸዋ በከፋ በጅማ ተዘዋውረው የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመስበክ ከአረማዋያን ንጉሶችና ባላባቶች የሚደርስባቸውን በደሎች ተቋቁመው ብዙ ህዝብን ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰዋቸዋል።
★ አባታችን በተለይ በሸዋ አርሲ ፈንታሌ ላይ ሠርቲ ለምትባል ጠንቋይ እየተላላኩ ህዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ አራት መቶ ሰባ ሺህ ሦስት መቶ 470,300 አጋንንትን እንደ ነብዩ ኤልያስ በፀሎታቸው ከሰማይ እሳት አውርደው ተራራ ደምስሰው አቃጥለዋቸዋል። ታላላቆቹ እነ አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ መብአ ፅዮን የአባታችን ረዳኢ ነበሩ።
★ አቡነ ቀውስጦስ በብዙ ተጋድሎ ሲኖሩ በሰማእትነት ያርፉ ዘንድ ስለ እግዚአብሔር መንግስትና ዘላለማዊ ህይወት የሚተጉ እንጂ የዚህ አለም ሀብትና ስልጣን የማይሹ እውነተኛ መናኝ ነበሩና የታናሽ ወንድማቸው የአፄ ይኩኖ አምላክ ልጅ አፄ አምደ ፅዮን የአባቱን እቁባት በማግባቱ «ይህንን ልታደርግ አይገባህም» ብለው እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ቢገስፁት በሌሊት 11 ወታደሮቹን ልኮ ከበዮ ወደ እንሳሮ ሀገር ካስወሰዳቸው በኋላ ከበዩ ተራራ ላይ ኮሶ አረህ ከሚባለው አፋፍ ላይ እጅ እና እግራቸውን አስረው ቢገድሏቸው (ሰማእት ቢያደርጓቸው) ደማቸው ሲፈስ ጀማ ድረስ ሆነ።
★በእኩለ ሌሊት ጎናቸው በጦር ሲወጋ ደማቸው ቀይ ብርሃናማ ሆኖ ሌሊቱን ቀይሮት ከፀሀይ 7 እጅ የሚያበራ ብርሃን ሆኖ እስከ ታላቁ ወንዝ ደረሰ። በደማቸው ሌሊቱ ወደ ብርሃናማ ቀን ስለተለወጠ ቦታው አሁን ድረስ ቀን እየተባለ ይጠራል።
★ ደማቸው ከወንዙ ጋር ተቀላቅሎ እርሳቸው ከገደሙት ገዳም ደረሰ ድንበሩ ጋር ሲደርስም ቆመ ከዚያም እንደ እሳት ፈላ ቦታውም ደም እሳት እየተባለ መጠራት ጀመረ።
★ ዳዊታቸውን በስተቀኝ በኩል ቢወረውሯት እየበረረች አሁን ደብረ ዳዊት እየተባለ በሚጠራው ስፍራ አርፎ ተሰውሯል እስከ አሁን የት እንደደረሰ አይታወቅም።
★ በግራ የያዙትን በትረ መስቀላቸውን ቢወረውሩት መሬት ላይ ቢሰካ ዛሬ አለም ሁሉ የሚድንበት ፀበል ፈልቆልናል።
★ በዚህም ጥር 21 1332 ዓም በ125 አመታቸው አረፉ። ጌታችን እመቤታችንንና መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ 7 የብርሃን አክሊላትን አጎናፅፏቸዋል።
★ቃልኪዳናቸው
፩ ደጅህን ለረገጠ 84 ትውልድ እምርልሃለሁ
፪ ቤተ መቅደስህን የሰራ ብቻ አይደለም፣ ሲሰራ ያየ፣ ቦታህን የጠቆመ ያመላከተ 64 ትውልድ እምርልሃለሁ
፫ ገድልህን የሰማ ያሰማ፣ ስምህን የጠራ፣ ስለአንተም የተነጋገረ 26 ትውልድ እምርልሃለሁ
፬ በሰንበት ቀን በስምህ የሚዘክረውን፣ ከመቃብርህ ጭብጥ አፈር ወስዶ በቤቱ የሚያኖረውን ከክፉ ሰው ከድንገተኛ አደጋ እጠብቀዋለሁ፣ እባብም አይነድፈውም።
፭ የመቃብርህን አፈር ዘግኖ ወስዶ ከሞተ ቤተሰቡ መቃብር ቢበትነው የሞተው ቤተሰቡ የሞተው ሰው ሲኦል ቢሆን ከመቅስፈት ገነት አስገባልሀለሁ።
፮ ለቁርባን ያልበቃ ቢሆን በተወለድክበት ቀን ባረፍክበት ቀን እጣን፣ ዘቢብ፣ ጧፍ ይዞ ለመጣው ስጋወ ደሙ እንደተቀበለ አደርግለታለሁ።
፯ ደጅህን መጥቷ የረገጠውን የሲኦልን ደጅ አያየውም፤ ላልምረው ደጅህን አላስረግጠውም
፰ ስለ እኔ ሰማእት የሆንክባት ምድር እንደ ዳዊት ሀገር ኢየሩሳሌም ትሁንልህ ወደ እርሷ የሄደውን ሁሉ ወደ መቃብሬ ጎለጎታ እንደሄደ እቆጥርለታለሁ። ብዙ ሀጢያት የሰራ ሰው ንሰሀ ገብቶ በዚች ቦታ ጥቂት ምፅዋት ቢሰጥ ሀጢያቱን እደመስስለታለሁ፣ በጠበልህም ቢጠመቅ በደሉን አጠፋለታለሁ ብሎ ጌታችን የማይታበይ ቃልኪዳኑን ሰጥቷቸዋል
ዛሬም ድረስ ልዩ ልዩ ተአምራትን የሚያደርጉት አባታችን በገዳማቶቻቸው አእላፍ ደዌ በሽታ ችግርን አባረዋል። በተጨማሪም እኛም ሼር በማድረግ የበረከቱ ተሳታፊ እንሁን እላለሁ።
የፃድቁ የሰማእቱ የቅዱሱ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ በረከታቸው ረድኤታቸው ፀሎታቸው ይደርብን አሜን።
★★★ገዳማቸው 2ቱም ወደ ደብረ ሊባኖስ መንገድ ከአዲስ አበባ 120 ኪሜ ወደ ጅሩ አርሴማ መንገድ ሙከጠሪ ከተማ ሚጤና በዩ ልዩ ስሙ መገንጠያ ሌላኛው መንገዱ በዚያው ሆኖ በእግር 1 ሰአት ገደማ "ቀን ማርያም" (የእረፍት ቦታቸውና መቃብር ስፍራቸው ያለበት)★★★
በጎደለ አቡነ ቀውስጦስ ይሙሉ
በጠፋ አቡነ ቀውስጦስ ይማሩን