Get Mystery Box with random crypto!

#እመጓ........ 'በአፍላ ትጀምሩታላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሱታላችሁ፣ ያ | Metsihaf media መጽሐፍ ሚዲያ ®

#እመጓ........

"በአፍላ ትጀምሩታላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሱታላችሁ፣ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፣ የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ። ምኞታችሁ ልክ የለውም፣ አእምሮአችሁ ብዙ ነው። ያማራችሁን ስታገኙ ወዲያው ይሰለቻችኋል። ተው የተባላችሁትን ትሰራላችሁ፣ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፣ የተፈቀደላችሁን ችላ ትሉታላችሁ። ቤተ መቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደፊት ቤተ መቅደሱን በመስታወት ሠርታችሁ መቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከውጪ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ።

ሁሉን ማወቅ ትፈልጋላችሁ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም፤ ሁሉ አላችሁ ፣ ግን ባዷችሁን ናችሁ። ሃይማኖት እንጂ እምነት የላችሁም!" ቀጠሉ አባ። ሰውነታቸው እንደ ቅኔ ዘራፊ ይናጣል።

"መድኃኒት ነው ያልከው? መቀመሚያውን ነግሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ብቻ ትሄዳለህ። ጥበብን "ሀ ግእዝ" ብዬ ላስተምርህ ብሞክር መንደር ውስጥ በቃረምካት ዕውቀት ተመክተህ በመሰልቸት "ሆ ሳብዕ" ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ። የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተለከፈከፈ የተማሪ ኩፋዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል። ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ፣ ሠርታችሁ ሀብት ስታፈሩ ከላይ የሆናችሁበትን ሀገር ለቃችሁ ሰፋ ወዳለው እንሂድ ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ። ትቀጥላላችሁ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ። ትቸኩላላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ። በጽኑ ታማችኋል!"

ከታሪክ ፍቅርንና ልማትን ሳይሆን ጥላቻንና ጥፋትን ለይታችሁ ትቆፍራላችሁ። ከዚያም ቀጥላችሁ የከበረ ማዕድን እንዳወጣችሁ ሁሉ በኩራት ደረታችሁን ነፍታችሁ ሳትመርጡ ሁሉን በአደባባይ ትዘሩታላችሁ፣ እናም ወደ ኋላ ስለ ታሪካችሁና ስለ ቅርሳችሁ ባሰባችሁ ቁጥር ፍርሃትና ሃፍረት ይሰማችኋል። ስለሆነን ከኋላ ታሪካችሁና ክብራችሁ እየራቃችሁ መጣችሁ። የአሸናፊነትና የተሸናፊነት ትርጉም የያዙ ሃውልቶች በአንድ ላይ ታቆማላችሁ። ለግልፅነትና ለነፃነት እያላችሁ በምታደርጉት ሽኩቻ እርቃን ወደ መሆን ወረዳችሁ።

ቅቤ ላይወጣችሁ ትናጣላችሁ። በዚህ አለም ጥድፊያ ታማችኋል። ሀገራችሁን ትንቃላችሁ፣ ጥላችሁ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ፣ ከሄዳችሁ በኋላ ደግሞ አፍታ ሳትቆዩ አገሬ ናፈቀኝ ትላላችሁ። በቁማችሁ የናቃችሁትን የሃገራችሁን አፈር በሞታችሁ ልትለብሱት ትናፍቃላችሁ። ለሀገሬ አፈር አብቃኝ ብላችሁ በድናችሁን ልካችሁ የወገኖቻችሁን ልብ ትሰብራላችሁ። ግብዝነታችሁ መጠን የለውም። ሁለት ሀገር እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ፣ አንዱን በደም ሌላኛውን በመታወቂያ ታስባላችሁ። ከአንዱም ግን በአግባቡ አትኖሩም። ዘመናችሁም በምልልስና በመዋተት ያልቃል። ምን እንደምትፈልጉ አታውቁም እናም ፍለጋችሁ አያልቅም።

በዚህም የተነሳ ሚስጥር ለመካፈል ቅርስ ለመረከብ የሚያስችል ስብዕና አልገነባችሁም። እኛ የመገናኛውን ድልድይ ስላልሰራንና ከእናንተ ስለራቅን ሳይሆን ስለማታዩት ወይም ማየት ስለማትፈልጉት አለበለዚያ እንደ ልብወለድ ገፀ ባህርይ የራሳችሁን ያሸበረቀ አስረካቢ ፈጥራችሁ እውኑን ሳይሆን ምናባችሁን መረከብ ፈልጋችሁ ስለምታጡት ነው። እኛ ደግሞ እናንተ ታዩት ዘንድ አላሸበረቅንም፣ ማሸብረቅም አንፈልግም። በዚህ ምክንያት ለእናንተ ምስጥር ለመንገር ቅርስ ለማውረስ ከባድ ሆኗል። እኛ አባቶቻችንን እናምናለን። በእነርሱም ደስ ይለናል። የነገሩንን ተቀብለን ቃልኪዳናቸውን ጠብቀን እንኖራለን።

"ፅላተ ሙሴ አክሱም ፂዮን እንዳለች ሲነግሩን መጋረጃ ገልጠን ሳጥን ከፍተን እንይ አላልንም"

"ጌታ የተሰቀለበት ግማደ መስቀሉ ክፋይ ግሸን ማርያም አለ ሲሉን ቆፍረን አውጥተን እንይ አላልንም"

"ቅዱሱ ፅዋ መንዝ ውስጥ አለ ሲሉንም ዋሻ እናስስ አላልንም"

አባቶቻችንን አምነን ሀገራችን የበረከት ምድር መሆኗን ተረድተን የጌታችንን የጸጋ ስጦታ ተቀብለን በእምነት እንኖራለን። ምንም የለንም ሁሉ ግን የእኛ ነው። ድሆች ብንባልም ባለጸጎችም ነን። የተራቆትን ብንመስልም የጸጋ ልብስ አለን። ሐዘንተኞች። ብንመስልም ደስተኞች ነን። ስለ ሀገራችን መባረክ ፣ ቅድስት ሀገር መሆን፣ ቅዱስ ቅርስ በእጃችን እንዳለ አለም እንዲያረጋግጥልን አንፈልግም። የሌለንን አለን፣ ያልተሰጠንን ተቀበልን ብለን የምንኮፈስ ግብዞችም አይደለንምና። የሌለን ነገር ለመጠበቅና ለመታመን ስንል ሥጋችንን እየጎሰምን በገዳም ለመኖር የምንወስን ጅሎችም አይደለንምና"።

Credit :- "እመጓ" በዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ገጽ 162 - 164


@metsihafmedia
@metsihafmedia