Get Mystery Box with random crypto!

#ከስሜ_በፊት ክፍል ሶስት(ሜርሲ ) ከእንቅልፉ የባነነበትን ምክንያት ባያውቀውም ነቅቷል።ብልድል | ሜርሲ እና ብዕሯ✍

#ከስሜ_በፊት

ክፍል ሶስት(ሜርሲ )

ከእንቅልፉ የባነነበትን ምክንያት ባያውቀውም ነቅቷል።ብልድልብሱን ገለጥ አደረግ።ከእንቅልፉ ለመባነኑ ሶስት ምክንያቶችን አስቀመጠ።
የዝናቡና የመብረቁ ድምፅ...የዳንኤል የማለዳ የፀሎት ድምፅ...ሶስተኛው ደግሞ ጨለማው ለንጋቱ እጁን እየሰጠ መሆኑ ነበር።
አተኛኘታቸውን አይቶ ፈገግ አለ።ከጎኑ ፀላዩ ዳንኤል ተንበርክኮ ስለነበር እየፀለየ የነበረው ብልድልብሱ ወደ እሱ በብዛት ተሰብስቦ ከእግራቸው በኩል የተኙትን ለብርድ አጋልጧቸው ነበር።የተለመደው ጭቅጭቅ ከሪም ከእንቅልፉ እንደተነሳ ተጀመረ።ከሪም ዓይኖቹን ሲገልጥ እንደነገሩ እንደነገሩ ተደርጎ ከተሰራው የቆርቆሮ በር በኩል የሚገባው ብረድ ጆሮ ግንዱን ሲለው በብሽቀት ተነሳ።እስከ እግሩ ብቻ ነበር ብልድልብሱ።
እጁ ላይ የገባለትን ማማሰያ ከባዶ ድስጡ ጋር ማላተም ጀመረ።ያኔ አማኑኤል በሙሉ ልቡ ነቃ።ባህሩ እና መዓዛም ዓይናቸውን እያሹ ቀና አሉ።ከሪም ያሰበው አልተሳካለትም።ዳንኤል ብልድልብሱን እንደተጠቀለለው ተንበርክኮ ድምፁን ከዝናቡ በላይ ከፍ አድርጎ ያሳርጋል።
"አቦ የምትለምነው ባልሰማ ይለፍህ!"
ዳንኤል ፀሎቱን አቁሞ ከተንበረከከበት ቀና ብሎ አየው።
በዛች ቅፅበት ከሪም ብልድልብሱን ወደ እራሱ በመሰብሰብ ተጠቀለለበት።
"ምን አለበት መፀለይ ባትችሉ እንኳ 'አሜን 'በማለት ብትተባበሩኝ።"
"እኔም እፀልያለሁ እኮ ግን በልቤ ለልቤ አምላክ እፀልያለሁ።" ይሄን ብሎት ባህሩ እየተነጫነጨ ከሪምን ተከተለው።
መዓዛና አማኑኤል በሁኔታቸው እየተሳሳቁ ይመለከቷቸዋል።
ባህሩ ከብልድልብሱ አንገቱን በማውጣት ወደ መዓዛ እየተቅለሰለሰ እያያት
"መዓዚዬ ዝናቡን እንደምታይው ነው በዚህ ሰዓት ተፍ ተፍ ማለት አንችልም።አንቺ ከጥበቡ አትጎይምና ያለችዋን ሰራርተሽ"
መዓዛ ብቻዋን ከተኛችበት ፈገግ እያለች ተነሳች።ዳንኤል ወደ ፀሎቱ ተመለሰ።

* * * *

አማኑኤል ከተወጠረችው ሸራ ቤት ፅሁፉን ፅፎ እንደጨረሰ ከሁሉም ዘግይቶ ነበር የወጣው።ዝናቡ አብቅቶ ፀሃይ ለመውጣት ከደመናው ጋር ግብ ግብ ላይ ነበረች።ስትወጣ ደመናው ሲጋርዳት።ከሪም ከግንቡ አጥር ጥግ ቁጭ ብሎ በፈገግታ ይከታተላቸዋል።አማኑኤል እየተጠዳፈ ሄዶ ከአፉ ሳያደርሰው ሃይላንዱን መንትፎ ከመሬት ወረወረው።ከሪም በድንጋጤም በንዴትም ዓይኖቹ ቀሉ።
"ባንዳ!" ብሎ ከመሬቱ እምር ብሎ ተነሳ።አማኑኤል እርሱ በተነሳበት ድንጋይ በመቀመጥ ተቁነጠነጠ።
"ለምንድነው የምትፈታተነኝ!?"
"አንተ ነህ እየተፈታተንከኝ ያለሀው ከሪም።የሲጋራው ሳያንስህ እንደገና...ይሄ እኮ ለመኪና ነዳጅነት ተብሎ የተሰራ እንጂ ለሰው አይለም!"
"ማነው ሰው ያደረገኝ!?..."
"ከሪም..."
"አቦ አማኑ ተወኝ።ሰዉ በዚህ ሰዓት ለሰውነቱ ሙቀት የሚሰጠውን የእለት ምግቡን ተመግቦ ወይ ወደ ሞቀው አልጋው ተመልሷል ወይ ደግሞ ወደ እየለት ክንዉኑ።እና እኔና መሰሎቼ ከየትኛው የሰው ሀረግ ተመዘን ይሆን ሰው ለመባል የበቃነው!?"
አማኑኤል ከተቀመጠበት ቦታ በመነሳት ወደ ውስጥ ገባ ሰከንዳት ሳይፈጅበት ተመልሶ በመውጣት ከበሩ በመቆም
"ና የምንሄድበት ስፍራ አለ"
ከሪም እያንገራገረ ተከተለው።

* * * *
"ስሜቴን መቆጣጠር እችል ነበር።ግን ሰውን ያከለ ፋጡር ሰው አለመሆኑን አምኖ ቤንዚል ሲጠጣ...ሰው አለመሆኑን ሲናገር ምንም አቅም አልነበረኝም።ሰውነት ለብሻለሁ እኮ!...ምግቡን ለመግዛት ገንዘብ ከወዴት እንዳመጣሁ ሲጠይቁኝ ተጥሎ አግኝቼ ከማለት ውጭ ሌላ ምላሽ አልነበረኝም።እንዳመኑኝ ተስፋ አደርጋለሁ።"
ቀና ሲል ትሪውን ዘርግቶ አጥንቱን ከሚግጠው ባህሩ ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጩ።ባህሩ በፈገግታ ተመለከተው።
ካገኛቸው ጊዜ ጀምሮ ይሄን ፈገግታ አይቶት አያውቀውም ጥቂት ነገር ያስደስታቸዋል እልፍ ችግር አያንበረክካቸውም።
ማስታወሻውን ከመደርደሪያው አድርጎ ወደ ባህሩ በመሄድ አጠገቡ ተቀመጠ።
መዓዛ ጥጉን ይዛ ቡናውን ትወቅጣለች።
"ዳኒ እና ከሪም ወዴት ሄደው ነው?"
"መዓዚ ለቡና ቁርስ የሚሆን ነገር እንዲገዙ ልካቸው ነው።ዕድሜ ለአንተ እና ለዛ ባለ ጨላ...ለመግዛትም በቃን እኮ።"
ይሄን እንዳለ ከሪም ዳንኤልን አስከትሎ ገባ።
"እንዴ በቆሎ!?" ባህሩ ከተቀመጠበት ሊነሳ ቃጣው።
"አንተ አርፈህ አጥንቱን ጋጥ!" ከሪም እጁን በማስጠንቀቂያነት እየጠቆመበት ከመዓዛ እግር ሥር ባማስቀመጥ ከአጠገባቸው ተቀመጠ።
ዳንኤል ከፍራሹ እየተቀመጠ
"አያችሁ የፀሎት መልሴን..."
"የታል...የታል በክህ¡?" ከሪም እያላገጠ ወደ ግራ እና ቀኝ የጠፋን ነገር እንደሚፈልግ ሰው አማተረ።
"የበላሀው ምኑን ሆነና!?"
"የበላሁት የአንዱን ቱጃር ገንዘብ!"
"አማኑን ወደ እዛ የወሰደው ማን ሆነና!?"
"እግሩ ከአጋጣሚ ጋር ተባብረው"
ክርክራቸው እየጦፈ ሄደ
"በዚህ ምድር ላይ አጋጣሚ የሚባል ነገር የለም።"
"እርሱን ለፈላስፎቹ!" አለው ከሪም በተሰላቸ ድምፅ።
"ፈላስፋዎቹማ ከአንተ ጋር ይወግናሉ።"
"እናንተን ነው ያልኩህ"
"እኛ ፈላስፋ አይደለንም አማኞች ነን!"
"አማኝ!?...የሌለን ነገር በማኖር ማመን¡?"
"እርሱ በአንተ ልብ ውስጥ ነው የሌለው"
"ሄይ...ሄይ...ክርክራችሁን ተዉትና በቆሎውን ፈልፍሉት!" መዓዛ ነበረች።
ሁለቱም ረገቡ...አማኑኤል ግን እንዲቀጥሉት ልቡ ፈልጎት ነበር። ከተቀላቀላቸው ወር አልሞላውም ግን እርሱ በአመታት ውስጥ ፈልጎ ያላገኛቸው ነገሮች አሁን ፈልገውት ወደ እርሱ እየጎረፉለት ነው።እጁን እስኪያመው ድርስ የሚከትባቸው ነገሮች በርክተውለታል።



ይቀጥላል....

@Mercy_ena_berua
@Mercy_ena_berua