2021-10-04 22:09:12
በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ያጋጠመኝ ላካፍላችሁ ወደድኩ
ቀኑ የመስቀልን አውደ አመት ለማክበር ወደ ሀዋሳ ከተማ በከተምኩበት ጊዜ ነበር ወደ ሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንኳን በሰላም አስገባኸኝ ለማለት እና ለመሳለም ባቀናሁ ጊዜ
አንድ ነጭ ደመና የለበሱ የሚመስሉ
እርጅናቸው የክብር ጌጥ የሆነላቸው ገፀ-ፍቅራቸው ከሩቅ የሚጣራ መነኩሴ እናት ነፍሴን ሳቧት።
እኔም ምስጋናዬን ጨርሼ መቼም ከቤተ ክርስቲያን አዛውንት የሚገኝ በረከት ታግለው ቢፆሙ አያገኙትምና የእማሆይን በረከት ለማግኘት እግሬን አነሳሁ።
ገና ከሩቅ የሚማርኩት እማሆይ ስጠጋቸው ነገሩ ለየቅል ሆነብኝ ።
የተሸበሸበው ፊታቸው ላይ እንባ ኮለል ኮለል እያለ ይዘንባል ውስጣቸው ማዘኑን ግንባራቸው ላይ ያሳብቃል አንገታቸውን ደፍተው አንዳች ነገር ያብሰለስላሉ!
ውስጤ አንዳች ነገር ሲሰበር ተሰማኝ እጅግ ደነገጥኩ ተረበሽኩ ምን ያስብኩት በረከት ቀረና ምን እንደሆኑ ለመጠየቅ ጓጉቼ ጠጋ አልኳቸውና
እማሆይ እንዴት አሉ? አልኳቸው
እማሆይ :ሳግ በተቀላቀለው ድምፅና በተከፋ ፊት ደህና እግዚአብሔር ይመስገን አሉኝ
ምነው ምን ሆኑብኝ የተከፉ ይመስላሉ ስል አጠገባቸው ቁጭ ብዬ አቀፍኳቸው
ሆድ እየባሳቸው !! አዪ ልጄ ሰማይ ምድሩ ተደፍቶብኝ ነዋ
እኔ: ምነው እናቴ !!!
እማሆይ : አይ ልጄ
አሉኝ ማልቀስ እየዳዳቸው
እኔ: ነገሩኝ እማ ግድ የለዎትም
እማሆይ: እይውልህ ልጄ የምኖርባት የልብስ ብጫቂ የምታክል ቤት ነበረች እሷንም ተከራይቼ ነው እናም አሁን ኪራይ ከከፈልኩ 2 ወር አለፈኝ ከይት ላምጣው !!! አሁን ከየት እንደማመጣው ጨነቀኝ እንዳያስወጡኝም ሰጋሁ ቀኑ ጨለመብኝ ልጄ
አሉና አቀረቀሩ
ይህን ሲነግሩኝ ክፉኛ ልቤን ተሰማኝ ኋላም አይዞዎት እማ ይሄ ደሞ ምን ችግር አለ ብዬ
ኪሴ ውስጥ የየዛኩትን ትንሽ ብር ስስጣቸው
አዪ ልጄ!! ብለው እንቅ አረገው ሳሙኝ የምርቃት ዝናብ አዘነቡብኝ እንደ ጉድ
ያ ዳምኖ የነበረው ፊታቸው ወገግ አለ ጨልሞ የነበረው ፊታቸው ፈካ !!! በጣም ደስ አላቸው ደስ ሲላቸው ስመለከት ነፍሴ ረካች እንኳንም መጣሁ አልኩ።
እማሆይም ያ ጭንቁ ጠፍቶ ሳቅ በሳቅ አደረጉኝ አሁንማ አሉኝ እማሆይ
አሁንማ ጥርስም ባይኖረኝ እስቃለሁ አሉኝና በሳቅ አረሰረሱኝ !!!
ከዚህ በኋላ እኔ አለሁ ስላቸው በቃ ቅድም ተደፍቶባቸው የነበረው ምድርና ሰማይ አሁን በደስታ ጠበባቸው
እኔም በድስታቸው ደስ አለኝ!!!
አፉ ወርቅ የተባለለት ቅዱስ ዮሐንስ ያለው ድንቅ ቃል ትዝ አለኝ
"በቤተክርስቲያን ደጃሽ ከተቀመጡት ምስኪኖች ውስጥ ጌታን ካላገኘኸው እመነኝ ቤተመቅደሱ ውስጥ ከቅዱስ ቁርባኑ ውስጥ አታገኘው"
እውነት ነው ለካ ቤተመቅደስ ገብተን ሰላም ያጣነው እንደ እማሆይ አይነት ምስኪኖች እየገፋን ረስተናቸው ነው ።
ቆርበን ሰላም ያጣነው ቤተመቅደሱ የቅርብ እሩቅ የሆነብን እግዚአብሔርም የሸሸን ድሆችን በሩ ላይ ረስተናቸው ነው ።
የቤተ-ክርስቲያን ሊቃውንት ድሆች ማለት የመንግስተ ሰማያት መግቢያ ቁልፎች ናቸው ይላሉ
ተወዳጆች ይህን የጉዞ ማስታዎሻ ላካፍላችሁ የወደድኩት የአሳዳጁ ጀሌዎች እንደሚሉት ለታይታ አይደለም እኔ ከሁሉ ያንስኩ ጭንጋፍ ነኝ
ዳሩ ግን ተወዳጆች እናንተም ወደ ደጁ ስትሄዱ እማሆይን መሰል ብዙ የመንግስተ ሰማይ ቁልፎች አሉና ተጠቀሙባቸው ለማለት ነው ።
መፅሀፉም ለድሀ የሚሰጥ ለእግዚአብሔር ያበድራል እንዲል አሁን በየአቅጣጫው ለተደቀነብን ውስብስብ ስቃይ አንደኛው መፍቻ ውሉ ምፅዋት ነው
እማሆይ አሁን ሳቃቸው ያጠግባል ፣ ደስታቸው ያረካል ወላጅ እናቴን ጠይቄ እንደማጣሁ ተሰምቶኝ ፣ ደስታቸው ደስ አለኝ በየጊዜውም እንደምጎበኛቸውም ቃል ገብቼላቸው ወደ ቀዬዬ ተመልስኩ !!!!!!!!!!!
የኛ ጌታ የሳሮን ፅጌሬዳ ይህን እንዳደርግ ስለፈቀደልኝ ስሙ ቡሩክ ይሁን!
"ምፅዋትን በቤትህ አደልባት እርስዋም ከመከራ ሁሉ አንተን ለማዳን ትችላላች" ሲራክ 29÷12
የምትነድ እሳትን ውኃ እንደሚያጠፋት ምፅዋትም ሀጢያትን ታስተሰርያለች ፡ ምፅዋትን ለሚሰጥ ሰው በመጨረሻ ይታሰብለታል ፡ በሚሰናከልበትም ጊዜ መጠጊያን ያገኛል። ሲራክ 3÷ 28
በጎቹ" ድምፁን ይሰሙታል!
╭══•|❀:✞✟✞❀|•══╮
✥┈┈••●◉✞◉●••┈••✥
ከመልአከ ኃይል ቀሲስ ኃይለመለኮት ግርማ ወንድሙ
18 /01/2014 ዓ.ም
ከሕይወት ተራራ ላይ መንፈሳዊነት ይብለጥ!
✥┈┈••●◉✞◉●••┈┈✥
╰══•|❀:✞✟✞❀|•══╯
4.2K views19:09