Get Mystery Box with random crypto!

#_ታሪክ_ድንግል_ማርያም_! #_የልደቷ_ነገር! በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም ሼር በማድረግ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

#_ታሪክ_ድንግል_ማርያም_!

#_የልደቷ_ነገር!

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!

የወለላይቱ እመቤት ልጆች የእመቤታችን ታሪክ አበው ቅዱሳን ናቸው፡፡ ይህንን ዳዊት “መሠረቶቿ ተቀደሱ ተራሮች ናቸው“ እንዳ በተለያያ ቅዱሳን መሠረት ስትወርድ እንደመጣች የቤተክርስትያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መዝ 86፥1

#_ጥንተ_ታሪክ፡-በኢየሩሳሌም አካባቢ በቅዱስ ጋብቻ ተወስነው ለፈጣሪ ተገዝተው የሚኖሩ ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ቅዱሳን ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች በትዳር ሕይወታቸው ልጅ የሌላቸው መካኖች ነበሩ፡፡ በተለይ በዘመናቸው ያፈሩትን የተትረፈረፈ ምድራዊ ሀብት የሚወርስላቸው ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ይተክዙ ነበር፡፡

አንድ ቀን ጴጥርቃና ቴክታ ስለ ሀብታቸው ብዛት ከተወያዩ በኋላ ጴጥርቃ በተስፋ መቁረጥ ስሜት “እህቴ ይህ ሁሉ የሰበሰብነውን ሀብታችንን ምን እናደርገዋለን? አንቺ መካን ነሽ የሚወርሰን ልጅ የለንም እኔ ደግሞ ከአንቺ ሌላ ሴት አላውቅም“ አላት፡፡

የተባረከች ቴክታም “ጌታዬ ሆይ የእስራኤል አምላክ ለእኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደ እኔ ልጅ አልባ ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ሴት ውለድ እንጂ“ ብላ ብታሰናብተው ጴጥርቃም “እንዲህ ያለ ነገር እንኳን ላደርገው በልቦናዬ እንደማላስበው የእስራኤል አምላክ ያውቃል“ አላት፡፡

ከዚህ በኋላ ብርክት ቴክታ ለክቡር ጴጥርቃ እንዲህ አለችው “እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም፡ ትላንት ማታ በሕልሜ ነጭ ጥጃ ከማህጸኔ ስትወጣ ያቺም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እስከ ሠባት /7/ ትውልድ ድረስ ሲዋለዱ ሰባተኛዋ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ“አለችው፡፡

ሁለቱም በራዕዩ ተደንቀው እግዚአብሔርን አመስግነው ወደ ሕልም ፈቺ ዘንድ ሄደው ያዩትን ነገሩት፡፡ ሕልም ፈቺውን በነገራቸውን ከሰማ በኋላ በመደነቅ እእዲህ አላቸው “አግዚአብሔር በምህረቱ በቸርነቱ አይቷችኋል የሕልማችሁም ፍቺ እንዲህ ነው ፦ ነጭ ጥጃ መውለዳችሁ ጥጃዋም እስከ ሠባት ትውልድ ስትዋለድ ማየታችሁ ሴት ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡

ሴቶቹም እስከ ሠባት ትውልድ ይዋለዳሉ። ሰባተኛይቱ ጨረቃን መውለዷ ከሰው የበለጠች በጸጋየከበረች ከመላእክት የተለየች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልታወቀኝም አልተገለጠልኝም“ አላቸው፡፡

በዚያም ወራት ክብርት ቴክታ ጸነሰች፡፡ ሴት ልጅም ወለደች፣ ስሟንም ሄሜን ብለው አወጡላት፣ ሄሜንም ዴርዴን ወለደች፣ ዴርዴም ቶናን ወለደች፣ ቶናም ሲካርን ወለደች፣ ሲካርም ሴትናን ወለደች፣ ሴትናም ሄርሜላን ወለደች፣ ሄርሜላም ማጣትን አግብታ ከሴቶች ተመርጣ የክርስቶስ አያት የሆነችውን ቅድስት ሐናን መስከረም 7 /ሰባት/ ቀን ወለደች፡፡

ቅድስት ሐናም በመንፈሳዊ ሥርዓት አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግስት ለተወለደው ክቡር ፃዲቅ ለሆነው ለቅዱስ ኢያቄም ዳሯት፡፡

እመቤታችንም እንደ ነጭ ዕንቁ ከቀድሞ ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ስታበራ ኖራለች፡፡ ከአዳም ቀጥሎ ለልጁ ለሴት የተሰጠች እርሷ ናት፣ ከሴትም ለሄኖክ የተሰጠች እርሷ ናት። ጥበበኛው ሰሎሞን ከሠባቱ ሰማያት ተልካ ጥበብ በፃድቃን ሰዎች ውስጥ ትመላለሳለች እንዳለ እመቤታችንም ከሄኖክ እስከ ደገኛው አብርሃም፣ ከአብርሃም እስከ ንጉሱ ዳዊት፣ ከዳዊት እስከ ቅድስት ሐና በቅድስና ወርዳለች፡፡

የብርሃኗ ነፀብራቅም ወርዶ በማህጸነ ሃና እስከ አደረ ድረስ አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ በሴቶች ማህጸን እንደ እርሷ ያለ የነጸብራቀ ብርሃን አልታየም፡፡ ሴቶች የተባሉት ከሔዋን ጀምሮ እስከ ብፅዕት ሐና፣ ከብፅዕት ሐና እስከ ዕለተ ምፅአት ያሉት ናቸው፡፡

ቅድስት ሐና ባሏ ኢያቄም ካገባት ጊዜ ጀምሮ ወንድ ወይም ሴት ልጅ ባለመውለዷ የመረረ ለቅሶ ስታለውስ ትኖር ነበር፡፡ በዚህም እስራኤላውያን ናቋት እንዲህም አሏት፡፡ “አንቺ በእስራኤል መካከል ለኢያቄም ቤት የሚቆም ስሙን የሚያስጠራ ዘርዕ ወይም ልጅ የሌለሽ መካን በመሆንሽ ከመካከላችን ውጪ፡፡

የኢያቄምን ቤት አጥፍተሻል ከሃገራችን ሂጂ፡፡ ከእኛም ጋር መኖር አትችይም፡፡ በሕጋችን መሠረት መስዋዕት ወይም ቁርባን በምናሳርግበት ጊዜ ከእኛ ጋር አንድነት የለሽም፡፡“ በኦሪት ሕግ ልጅ የሌላቸው ሰዎች ከመሠዊያው ቦታ ያባርሯቸው ወደ ውጪም ያስወጧቸው ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ቅድስት ሐና በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች፡፡ እንዲህም አለች “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዓለም መጨረሻ የምትኖር፤ ከዓለም በፊት የነበርክ ዓለምን አሳልፈህ የምትኖር የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሃቅ፣ የያዕቆብ አምላክ፣ የእስራኤል ጌታ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ሆይ ልመናዬንና ጸሎቴን ስማ ሁሉ ይቻልሃል የሚሳንህ የለም፡፡

አንተ ትገድላለህ ታድናለህ፣ አንተ ትዘጋለህ አንተ ትከፍታለህና ማህጸኔን ክፈትልኝ። አንተ ባዘዝከው መሠረት ያማረ የተወደደ መስዋዕት እጅ መንሻ አድርጌ እሰጥህ ዘንድ አንተን ደስ የሚያሰኝ ፍሬ ስጠን። ጸሎቴን ሰምተህ ልመናዬን ተቀብለህ የለመንኩህን ካልፈጸምክልኝ ያማረ የተቀደሰ ዘር ካልሰጠኸኝ አባቶቼ እናቶቼ ለዘለዓለም ወደሚኖሩበት የሞት ሃገር እኔንም ውሰደኝ።

እኔ አኗኗሬ የከፋ የልብ ሐዘንተኛ ስሆን በምድር ላይ መኖርን ለምን እመኛለሁ፡፡ የእስራኤል ሴቶች ልጆቻቸውን በደስታ ተሸክመው እኔ ላይ ይዘባበታሉ። ልጅ ባለመውለዴም ይስቁብኛል። እኔንም ባዩ ጊዜ እራሳቸውን ይነቀንቃሉና፡፡ “አቤቱ ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ የተናቅሁኝ የተጣልኩኝ የእኔን የገረድህን ስቃይ እይ ተመልከት“ ብላ በእስራኤል ሴቶች መካከል ሃና ልመና አበዛች፡፡

ባሏ ኢያቄምም አይኖቹ በሃዘን ወደምድር ሲመለከቱ ሕሊናውን ግን ወደ ሰማይ አቅንቶ “ሳይነግሩህ ሁሉን የምታውቅ የእስራኤል አምላክ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ ለምን ለጠላቶቼ መሳለቂያ መዘባበቻ አደረከኝ? አለምንም ካለመኖር ወደመኖር አምጥተህ የፈጠርክ አንተ ነህና። ጸሐይና ጨረቃን የምታፈራርቅ አንተ ነህና ልመናዬን ስማኝ፡፡

የልቤን ጭንቀት አቅልልኝ የጥበብና የአዕምሮ መንፈስ ያለው ወደ አንተ መስዋት አድርጌ በማቀርበው ልጅ ስጠኝ፡፡ በእስራኤል ሁሉ ዘንድ የተናቅሁ አታድርገኝ አንተ ብዙውን ትንሽ ትንሹንም ብዙ ማድረግ ትችላለህና“ አለ፡፡

ከዚህ በኋላ ጸሎታቸውንም በጨረሱ ጊዜ እግዚአብሔር የሃናን ሀዘን የኢያቄምን ጭንቀት አየ፡፡ ሃናም ሌሊት በራዕይ ከሰባቱ ሰማያት ነጭ ወፍ ወርዳ በማህጸኗ ስታድር አየች፡፡ ኪሩቤል እንደ ሰው እጅ በምስጋና ይጋርዳት ነበር፡፡ በእጁ የሕይወት ገመድ ተይዟል፡፡ ይህም የሕይወት መንፈስ በነጭ ወፍ አምሳል በሃና እራስ ላይ ተቀመጠ፡፡ ባህሪዋ ከኢያቄም አብራክ ወጥቶ በሃና ማህጸን ባደረ ጊዜ ሃና በማህጸኗ ተቀበለቻት፡፡

ይህም ባሕርይ የእመቤታችን ሥጋ ነው፡፡ ነጭ ባሕርም የተባለው ንጽህናዋ ነው። ነጭ ወፍም የተባለው ንጹህ ነፍሷ ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር በፊት በሕሊና አምላክ ታስባ ትኖር ነበርና። በአባቱ ቀኝ ነጭ ወፍም ነጭ ባሕርይም በእጁ ነበረችና ሳይነጣጠሉ ሁለቱ ባሕርያት በሐና ማህጸን አደረ፡፡

ይህ ነገር ከዚህ በፊት በሐና ማህጸን ያልተለመደ ስለሆነ የሐና ማህጸን ታወከ፡፡ ኢያቄምም በራዕዩ በሐና እጅ የሚመስለው የሌለ የሚጣፍጥ መልካም ፍሬ ተይዞ አየ፡፡ ከሴቶች ሁሉ እንደ እመቤታችን ንጽህት ሆኖ የተፈየረ የለም፡፡