Get Mystery Box with random crypto!

#ክፉኛ_የዝሙት_አጋንንትና_የዝሙት_ፈተና_በአረጋዊ_መንፈሳዊ_ በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም! ሼር | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

#ክፉኛ_የዝሙት_አጋንንትና_የዝሙት_ፈተና_በአረጋዊ_መንፈሳዊ_

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም!

ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!

ተወዳጆች ሆይ በመጻሕፍተ መነኰሳት በአረጋዊ መንፈሳዊ ላይ ስለ ዝሙት አጋንንት ክፉኛ ፈተና ተጽፏል። ለአንባቢ እንዲመች ይዘቱን ሳይለቅ አቀራረቡን ብቻ ጥቂት በመቀየር፣ ትንሽ በመጨመር አቅርቤዋለሁ።

ከአጋንንት ሁሉ ይልቅ የዚህ የሰይጣን ዝሙት ፈተናው ቡዙ ነው። የዝሙት አጋንንት ሕዋሳታችንን የሚያዝልበት ጊዜ አለ። ልቦናችንን የሚለውጥበት ጊዜ አለ። ሕሊናችንን የሚሰውርበት ጊዜ አለ። ሰውነታችንን ማዘዝ የማንችልበት ጊዜ አለ። ከጸጋ ስጦታ ለይቶ ኅሊናችንን ይለውጣል። ተኝተን ሳለን በዝሙት የሚዋጋን ጊዜ አለ።

የዝሙት አጋንንትን አመጣጡን እንወቅበት። በምን እናውቃለን? ካልን የዝሙት እሳቱ በፊታችን ላይ እንደ እሳት ብልጭ ይልብናል። የዝሙት አጋንንት ሲመጣ ድንግጥ ድንግጥ እንላለን። የዝሙት አጋንንት ሲፈትነን ጸሎታችን፣ ስግደታችን ይከብደናል። እንዳንጸልይ እንዳንሰግድ ከባድ አድርጎ ያሳየናል።

የዝሙት አጋንንት ሲፈትነን ጸሎታችንን የአምልኮት ስግደታችንን ትተን ወይም አቋርጠን እንተኛለን። ቆመን ተኝተን ሕዋሳታችንን እንዳብሳለን። እግራችንን እናፋትላለን። ነገር ግን ታግሰን ብንጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ ይረዳናል። ብንጸልይ ብንሰግድ ብንተጋ ፈተናው ይቀልልናል ይርቅልናል።

እነዚህ የዝሙት አጋንንት የፈተና ምልክቶች እያሉብን ያለ ጸሎትና ያለ ስግደት መተኛት የለብንም። ያለ ጸሎት ያለ ስግደት ብንተኛ ጠባቂ መልአክ ይርቀናል የዝሙት አጋንንት ቀርቦ ይፈትነናል።

የዝሙት አጋንንት በዓይን ይገባል። በዓይን ሲገባ ወደ ሰውነታችን ገብቶ በመቆጣጠር ሕዋሳችንን በእጅ እንድናሽ ያደርገናል። /ይህ አባባል ግለ ወሲብ እንድንፈጽም ያደርገናል ለማለት ነው/ የዝሙት አጋንንት እንዲህ ሲፈትነን በክርስቶስ ኃይል እናማትብበት።

ወደ ተግባረ ዝሙት እንዳይከተን በርትተን መጸለይ መስገድ አለብን። ይህን ካለደረግን የዝሙት አጋንንት ወደ አባለ ዘር ገብቶ ያለ ርህራሄ በዝሙት ፈተና ያስጨንቀናል በዝሙት ይጥለናል።

የዝሙት አጋንንት ሰዎችን እንደ ጊንጥ ይነድፋሉ። ቆመንም ቢሆን፣ ተቀምጠንም ቢሆን፣ ሥራም በያዝንበት ጊዜም ቢሆን የዝሙት ስሜት ቢያነሳሳብን በሕሊናችን እንጸልይ እንገስጸው።

ከወትሮ ይልቅ አብዝተን ስንበላ ስንጠጣ የዝሙት ፆር ይጸናብናል። አብዝቶ መብላት መጠጣት እና እላፊ መተኛት የዝሙት አጋንንትን ያቀርበዋል። አብዝተን ስንበላ ስንጠጣ ያኔ የዝሙት አጋንንት ሊዋጋን እንደቀረበ እንወቅ። ሰውነታችንን ለዝሙት ካነሳሳ ያኔ የዝሙት አጋንንት እንደሰለጠነብን እንወቅ።

ወዳጆቼ ብዙዎቻችንን ከንስሐ መንገድ ያራቀን፣ ክብራችንን ቅድስናችንን ያስጣለን፣ ከዓለማዊ እስከ መንፈሳዊ፣ ከምዕመን እስከ አባቶች እናቶች፣ በአምልኮት ሕይወት ከጸኑት፣ በቅዱስ ቁርባን እስከ ተወሰኑት ወዘተ የዝሙት አጋንንት እየፈተነን በቀላሉ እየጣለን ነው። በዚህም ቅድስና ከሕይወታችን ርቋል።

ከዝሙት አጋንንት የሸሸ እግዚአብሔርን ይከተላል። ከዝሙት አጋንንት የሸሸ ጸጋና በረከቱን ይዞ ይኖራል። ከዝሙት አጋንንት የሸሸ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በማዕረግ ያገባል። ከዝሙት አጋንንት የሸሸ ንጽሕናውን ቅድስናውን ይጠብቃል። ከዝሙት አጋንንት የሸሸ ከርኩሰት ይሸሻል። ከዝሙት አጋንንት ሸሽቶ፣ ወደ እግዚአብሔር ተጠግቶ የሚኖር ሰማያዊ ሽልማት ያገኛል። ከዝሙት አጋንንት እና ከዝሙት እንሽሽ። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ "ከዝሙት ሽሹ" ያለን። /1ኛ ቆሮ 6፥ 18/

እጅግ በጣም የገረመኝ አረጋዊ መንፈሳዊ "የሰይጣናት ተንኮላቸውን እናገር ዘንድ ከምን ተችሎኝ ላልፈጽመው" በማለት ገና ያላወቅናቸው ነገር ግን በወጥመዱ የተያዝንባቸው፣ በሴራው የወደቅንባቸው ተንኮሎቹ እንዳሉ ይነግረናል።

እኛ ግን ስለ ጥንተ ጠላታችን ከገነት ስላስወጣን፣ ከእግዚአብሔር ስለለየን፣ ከዘላለማዊ መንግሥቱ እንድንባረር ስላደረገን ሰይጣን ተንኮሉ ሴራው ውጊያው ሲነገረን ስለ ሰይጣን የተሰበክን መስሎን እንጃጃላለን። ስለ ጠላታችሁ ንቁ እወቁ ሲባሉ ሰይጣን ለምን ተነካ የሚሉ አሉ።

ቅዱስ ጴጥሮስ ግን "ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና" በማለት ውጊያው ቀላል እንዳልሆነና የማንጸልይ፣ የማንሰግድ፣ ቅዱስ ቁርባን የማንቀበል ከሆነ እንደ አንበሳ፣ በሕይወታችን እያገሳ ስንት ነገራችንን እየነሳ ይኖራል። /1ኛ ጴጥ 5፥8/

ወዳጆቼ ዲያቢሎስ "ፈልጎ እንደሚያገሳ" መባሉን ልብ በሉ። እኛ ባንፈልገውም እሱ ፈልጎ ይዋጋናል። የመንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ማለትም ጸሎት፣ ስግደት ወዘተ የማያነሳ ሰው ላይ እንደ አንበሳ መሆኑን አንርሳ።

ሚያዝያ 24-8-15 ዓ.ም

አዲስ አበባ