Get Mystery Box with random crypto!

#_የሌንጊኖስ_ጦር_እና_የክርስቶስ_ፍቅር! #_ጎኑን_በጦር_ቢወጋው_ጌታ_የጠፋውን_ዓይኑን_አበራ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

#_የሌንጊኖስ_ጦር_እና_የክርስቶስ_ፍቅር!

#_ጎኑን_በጦር_ቢወጋው_ጌታ_የጠፋውን_ዓይኑን_አበራለት!

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ሼር በማድረግ ለወዳጆ ያዳርሱ

ተወዳጆች ሆይ የሞተ የገደለ ጀግና አይባልም፡፡ ሌንጊኖስ የሞተ ለመግደል የጨከነ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን በራሱ ፍቃድ በቀራኒዮ አደባባይ መከራን ሲቀበል አይሁድና ሕዝቡ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን ብዙ ግፍ አድርሰውበታል፡፡ በተለይ እንደ ተራ ሰው በጥፊና በኩርኩም በመምታት፤ ጸያፍ ምራቃቸውን ፊቱ ላይ በመትፋት፤ ከመሳደብ በዱላ እስከ መደብደብ፤ ከግርፋት እከከ ሞት አድርሰውታል።

ጌታም በራሱ ፍቃድ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ፣ የከበረውን ሥጋ በመስቀል ላይ ትቶ ባለበት ሰዓት ሌንጊኖስ በቀራንዮ አልነበረም። ሌንጊኖስ ከሮማ ወታደሮች አንዱ የነበረ ሲሆን በተለይ በባሕርይው ከሰው ጋር በነገር መቀላቀል አይወድም ነበር። በዚህ ምክንያት በጌታ ሞት አልገባም አልተባበርም በማለት በዱር ተደብቆ ዋለ። ማምሻውን ስለ ጌታ ሁኔታ ሰው ሲጠይቅ "እሱማ ሞተ" አሉት።

አይሁድና ሮማውያን በሞቱ ያልገባውን/ያልተባበረውን/ እንደ ንጉሥ ጠላት አድርገው ያዩት ስለነበር ከእነሱ ላለመውጣት ፈልጎ በፈረሱ ወደ ቀራንዮ ተራራ ገሰግሶ ወጥቶ የሮማ ወታደሮች የሁለቱን ወንበዴዎች ጭኖቻቸውን ሲሰብሩ አይቶ እሱም ‹‹ከሞተ አልጎዳም ስለዚህ እኔስ ለምን ይቅርብኝ›› በማለት ጦሩን ነድሎ፣ የጌታን ቀኝ ጎኑን በጦር ጎልግሎ ወጋው።

ሌንጊኖስ አስቀድሞ አንድ ዓይና/ዓይኑ የጠፋ/ ሰው ስለ ነበር የጌታ የደመ መለኮቱ ፍንጣሪ ጌታ ባወቀ የጠፋ ዓይኑን ቢነካው ብርሃን ተጎናጽፎ፣ ፍቅርና ድኅነትን አትርፎ ተመልሷል፡፡ የሌንጊኖስ አመጣጥ ለጥፋት፣ የጌታ መልስ ግን ቸርነት ነበር፡፡ /ዮሐ 19፥34/

ወዳጄ ሁሌም በእግዚአብሔር መንገድ ለጥፋት፣ ለበደል ብትሰለፍ፣ በክርስቶስ መዳፍ በመታቀፍ ስለምትኖር እርሱ እንደ ሌንጊኖስ ይፈልግኃል፡፡ አንተ ሕጉን ለማፍረስ የእርሱ የሆነውን ለማጥፋት ብትሮጥ እርሱ በፍቅር ወጥመድ፣ በማሳደድ ይይዝኃል፡፡

ዛሬም ብዙ ሌንጊኖሶች አለን፡፡ በጥፋትና በኃጢአት ጎዳና ስንሮጥ ከርመን፣ ጌታ በቸርነቱ ስቦን የራሱ ያደረገን፡፡ ሌንጊኖስ ስለ ጌታ አምላክነት ስላላወቀ፣ ጦሩን በጌታ ላይ ሰበቀ፡፡ ዛሬ ደግሞ እኛ የጌታን አምላክነት አውቀን፣ የጽድቅን ሳይሆን የኃጢአትን ጦር ታጥቀን የተነሳን፣ በኃጢአት የዘመትን አለን፡፡ ሌንጊኖ ባለማወቅ የአይሁድ ተባባሪ ሆኖ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ እኛ እያወቅን የሰይጣን ተባባሪ ሆነናል፡፡

ዛሬም ጌታ የሞተላቸው ሌንጊኖሶች ጌታን በምንፍቅና በክህደት ጦር እየወጉት ነው፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ‹‹ሌሊት ጸሎቴን ጨርሼ በተኛሁ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚያበራና እስከ እግሩ ድረስ ረጅም ልብስ የለበሰ አንድ ወጣት ወደ እኔ ሲገባ አየሁት፡፡ ልብሱም ተቀድዶ፤ የተቀደደውን ልብስ ቁራጭ በእጁ ይዞ ስላየሁት ‹‹ልብስህን ማን ቀደደብህ›› ብዬ በመጮህ ብጠይቀው እርሱም ‹‹ልብሴን የቀደደብኝ አርዮስ ነው›› በማለት ያየውን ተናግሯል፡፡

ወዳጄ የጌታ ልብስ መቀደድ ምሳሌ አርዮስ ጌታችንን ከሦስቱ አካላት በመለየት ‹‹ፈጣሪን ፍጡር ነው›› በማለቱ ነው፡፡ ዛሬም እንደ አርዮስ "ፍጡር ነው፤ አማላጅ ነው" እያሉ የጌታን ልብስ በክህደት በመቅደድ፣ እንደ ሌንጊኖስ የጌታን ጎን በመውጋት የሚኖሩ አሉ፡፡ አይሁድ በቀራኒዮ አደባባይ በጌታ ላይ የፈጽሙትን ግፍ እና ክደት ዛሬም የሚደግሙት አሉ፡፡

እንደ ሌንጊኖስ የጌታን ጎን ዳግም የሚወጉትን፣ በክህደት ልባቸውን ያደነደኑትን ሐዋርያው ‹‹በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፡፡ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና›› በማለት ይገልጻቸዋል /ዕብ 6፥6/

ወዳጄ በሌንጊስ ጥፋት ውስጥ የክርስቶስ ማዳን እንዳለ ሁሉ ባንተም ክፋት ውስጥ የጌታ ማዳን ስላለ ወደ ክርስቶስ ለመጠጋት እንደ ሌንጊኖስ የክፋት ጦር ሳይሆን የጽድቅን ጦር ስበቅ ያኔ ጌታ የጠፋብህን መንፈሳዊ ሕይወት ያበራልሃል።

ሌንጊኖስ የክርስቶስን ቸርነትና ማዳን ካየ በኋላ በመጨረሻ ምን ሆነ? ምን አደረገ? ካልከኝ ሌንጊኖስ ዓይኑ ከበራለት በኃላ "የጠላትን ዓይን ያጠፉታል አንጂ እንዴት ያበሩታል" በማለት በመገረም በዕለተ አርብ የተደረጉትን ተአምራቶች መመርመር ጀመረ።

የጌታን በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሳት ሲሰማ እውነቱን እንዲያስረዳው ወደ ጌታችን አጥብቆ ጸለየ። ጌታም ቅዱስ ጴጥሮስን ልኮለት ወንጌልን በሚገባ ተምሮ በስሙ መስበክ ጀመረ። በኢየሩሳሌምም የአይሁድና የሮማውያን ተቃውሞ ስላስቸገረው ወደ ታናሽዋ እስያ ወደ ቀጰዶቅያ ሄዶ ወንጌልን በማስተማሩ ብዙዎችን በክርስቶስ ወደ ማመን መልሷቸዋል።

በመጨረሻም ወንጌልን በማስተማሩ ተከሶ በቀጰዶቅያ ከተማ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ በሰማዕትነት ሐምሌ 23 ቀን አርፏል። በሌንጊኖስ ጦር ውስጥ የክርስቶስን ፍቅር አየህ?

ወዳጆቼ ጌታችን በደሙ የመሠረታትን ቅድስት ቤተ-ክርስትያናችንን በብሔር ሽፋን፣ በፖለቲካ ተንኮል እንዳትከፋፈል በርትተን እንጸልይ፡፡ ዛሬ ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ነገ ቆመን ማውረድ እንችልምና በአንድነት መንፈስ እንጽና፡፡

"ሌሊቱ አልፎአል፣ ቀኑም ቀርቦአል እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ" ሮሜ 13÷12

‹‹ከክርስቶስ ጋር እንዴት እንኑር?›› ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ፡፡

ሚያዝያ/ 6/15 ዓ.ም
አዲስ አበባ