Get Mystery Box with random crypto!

#_ለክርስቶስ_ዓላማ_እንደ_አህያ_ተመችተነዋል? ተወዳጆች ሆይ ከጥንት ጀምሮ አህያ ለሰው ልጆች ሕ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

#_ለክርስቶስ_ዓላማ_እንደ_አህያ_ተመችተነዋል?

ተወዳጆች ሆይ ከጥንት ጀምሮ አህያ ለሰው ልጆች ሕይወት ትልቅ ባለውለታ ብትሆንም፤ ሰዎች ጉልበቷን እየተጠቀሙ ስሟን ስድብ አደረጉት። ብርቱዋ፣ ዕቃ ተሸከሚዋ፣ ታዛዥዋ አህያ እርባና ለሌለው ሰው፣ የሚሉትን ለማይሰማ ሰው፣ ስሟ ስድብ ሆነ።

ለጠንካራና ለታታሪ ሰው "አህያ" የሚለው ስም እንደ ነውር ይቆጠራል። ግን አህያ ሰው በቀላሉ የማያየውን መልአክ ለማየት፤ ዘባነ ኪሩብን ተክታ ጌታዋን ለመሸከም የበቃች ፍጡር ነች። /ዘኁ 22÷23—34, ዮሐ 12÷15/

ጌታችን በሥጋ ተገልጦ በነበረበት ጊዜያት ከሰው ያልተናነሰ አህያ በሰው መሃል ጌታዋን አገልግላለች። እኛስ ጌታችንን በሰው መሃል አገልግለናል? ጌታችን አህያዋን "ፍቱና አምጡልኝ" ሲል ሐዋርያትን ሳትራገጥ፣ ተፈትታም ሳትፈረጥጥ፣ ወደ ጌታዋ መጥታ አገልግላለች።

እኛ ግን ጌታችን መምህራንን ካህናትን ልኮልን ከታሰርንበት የኃጢአት ማሰርያ ፈተው ወደ ጌታ ሊወስዱን ሲሉ የኃጢአቱን ገመድ እያጠበቅን፣ ከአህያ አንሰን፣ አልፈታም ብለን ሸሸን፤ ጌታንም ለማገልገል እንቢኝ አልን። አህያ ባልተለመደ መልኩ ልብስ ለበሰች፤ እኛ የጌታችንን ጸጋ መልበስ አቃተን። ማቴ 21÷7

አህያ ጌታ ሲመሰገን ክብሩን በዓይኗ አይታለች፣ ለጌታ የተነጠፈውን ዘንባባ በኮቴዋ ረግጣለች። እኛ የጌታ ክብር በማህሌቱ በቅዳሴው ሳናይ፣ የጸጋ ዝንጣፊ የተነጠፈበትን የእግዚአብሔርን ደጅ ዘወትር ሳንረግጥ፣ እንደ ሰነፍ አህያ የጌታን ጸጋ ለመሸከም ስናለምጥ ስንት ዓመት ሆነን? በእውነት በሕይወታችን ለክርስቶስ አላማ እንደ አህያ ሳትንቸው ከኖርን፣ ከአህያ አነስን ማለት ነው።

የቅዱሳን አምላክ ለበለአም አህያ የገለጠውን ምስጢር ይግለጥልን፡፡ አህያ እያልን ከምንሳደበው እንስሳ የተሻልን ያድርገን፡፡

ሚያዝያ 1-8-15 ዓ.ም
አዲስ አበባ