Get Mystery Box with random crypto!

#_በካሊፎርኒያ_የነበረኝ_የንስሐ_አገልግሎት! 'ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

#_በካሊፎርኒያ_የነበረኝ_የንስሐ_አገልግሎት!

"ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር" /ማቴ 3፥6/

ተወዳጆች ሆይ በዚህ አገልግሎት እጅጉን ከምደሰትበት አንዱ የንስሐ እና የቄደር ጥምቀት አገልግሎት ነው። የመጥምቀ መለኮት ጥምቀት ሥጋዊ ፈውስ ወይም ሥጋዊ ድህነት ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም። የነፍስ ፈውስ ላይም ያተኮረ ነበር።

ብዙዎች ለመጠመቅ ወደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ይመጣሉ ተጠምቀው ብቻ ሳይሆን ንስሐ ገብተውም ነው የሚመለሱት። ለዚህም ነው "ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር" ተብሎ የተጻፈው። /ማቴ 3፥6/

የጥምቀት አገልግሎት ከንስሐ ጋር ሲሆን ለተጠማቂው ሁለት ድህነት ይሰጠዋል። ንስሐ ገብቶ የሚጠመቅ ሰው በመጀመሪያ በነፍሱ ይድናል ወይም ከኃጢአት በሽታ ይፈወሳል። ሁለተኛው ከያዘው ደዌና ክፉ መንፈስ ይፈወሳል። አንዳንዴ ንስሐ ሳንገባ ጸበል ስለምንጠመቅ ድህነት ሊዘገይብን ይችላል። ስለዚህ የትኛውም ጸበል ስንጠመቅ በመጀመሪያ ንስሐ እንግባ በነፍሳችንም እንዳን። ነፍስ ከዳነች ሥጋ ቀላል ነው። ምክንያቱም የነፍስ ድህነት የሥጋን ድህነት ያስከትላልና።

የሚያሳዝነው ብዙዎች ንስሐ ለመግባት ይፈራሉ ይጨነቃሉ። "ኃጢአቴን እንዴት እናዘዛለሁ? ከየት ጀምሬ ነው የምናገረው? ይህን ሁሉ ኃጢአት እንዴት ልናዘዝ? የሚረዳኝ ካህን ይኖር ይሁን? ወዘተ" ጥያቄዎች ያስጨንቋቸዋል።

በዚህ ሰራሁት የምንለው ኃጢአት ያስጨንቀናል በወዲያ ንስሐ እንዳንገባ መናጢው ያስፈራራናል፣ እግዚአብሔር የይቅርታ አባት መሆኑን ያስረሳናል። ብቻ ንስሐ ለመግባት ጭንቅ ነው። ታዲያ የሰይጣንን ፈተና አልፈው፣ ንስሐ ለመግባት ወስነው መጥተው ንስሐ ሲገቡ፣ ሸክማቸው ሲቀል፣ የነፍስ ነፃነት፣ የኃጢአት ስርየት አግኝተው ሲሄዱ ከማየት የበለጠ ምንም ደስታ የለም።

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የሆነውም እንደ ወይን አምባ ነው። የንስሐ እና የቄደሩን ጥምቀት ጥሪ ተመልክተው ብዙዎች መጥተው ንስሐ ገብተው ቄደር ተጠምቀው ነበር። በጣም የገረመኝን ልንገራችሁ። መደበኛውንና የቄደሩን ጥምቀት አጥምቄ፣ ቅብዓ ቅዱስ ቀብቼ ስንብት ላይ ሰንብቼ ሰዓት አልበቃ ብሎኝ ነበር። ነገር ግን ንስሐ የሚገቡት ሰዓት ቢሄድም ንስሐ ሳንገባ አንሄድም ብለው እስከ ምሽቱ 12፥30 ንስሐ ስሰጥ ነበር።

ምዕመናኑ ተራውን ጠብቆ ታግሶ ንስሐ ለመግባት ያሳዩኝ ትዕግስት ድንቅ ነበር። ደፈር ያለው ፊት ለፊት ይናገራል፣ ፈራው ደግሞ ኃጢአቷን በወረቅ ጽፋ ለቅዱስ ኤፍሬምና ለቅዱስ ባስልዮስ እንደሰጠቻቸው ደግ ሴት በወረቀት ጽፈው ይሰጡኝ ነበር።

ወዳጆቼ ምዕመናኑ ተይዟል መተንፈሻም አጥቷል ንስሐ የሚገቡበትን መርሃ ግብር ብናዘጋጅ፣ በሳምንት አንዱን ቀን ለንስሐ ብናውጅ ኃጢአቱ ያስጨነቀው፣ ያ መናጢ ግራ ያጋባው ሰው በሙሉ ልብ ቀን ቆርጦ ወስኖ ንስሐ ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ንስሐ ግቡ ብለን ብቻ ማስተማር ሳይሆን ምዕመናኑ ንስሐ የሚገቡበትን አንድ ቀን ለእነሱ ብንሰጣቸው፣ ቀኑንም ተዘጋጅተን ብናዘጋጃቸው ንስሐ ይገባሉ። ሁላችንንም ለእውነተኛ ንስሐ ያብቃን!

መጋቢት 23-7-2015 ዓ.ም

ካሊፎርኒያ አሜሪካ!