Get Mystery Box with random crypto!

በዓለ ጰራቅሊጦስ ‹‹ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም›› /ዮሐ. 14፥18/ ጰራቅሊጦስ፡- | መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

በዓለ ጰራቅሊጦስ

‹‹ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም›› /ዮሐ. 14፥18/
ጰራቅሊጦስ፡- ቃሉ ግሪክ ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት መጽንኢ በእምነት የሚያጸና፣ መንጽሒ ከኃጢአት የሚያነጻ፣ ናዛዚ ያዘኑትን የሚያረጋጋ፣ መስተፍስሒ፣ የተጨነቁትን የሚያስደስት፣ ከሣቲ ምስጢርን የሚገልጽ ማለት ነው፡፡ 
ጰራቅሊጦስ፡- መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የጰራቅሊጦስ በዓል ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡ 
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የሚሠራውን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ አባቴ እሄዳለሁ (አርጋለሁ) ሲላቸው ደነገጡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም መደንገጣቸውን አይቶ ‹‹ኢይደንግድክሙ ልብክሙ እመኑ በእግዚአብሔር ወእመኑ ብየ እስመ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ወምዕራፍ ቦቱ›› (ልባችሁ አይደንግጥባችሁ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም እመኑ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ ማለት ባባቴ ቤት በመንግሥተ ሰማያት ብዙ ማዕርገ ሀብታት አለ) /ዮሐ. 14፥1)
እንዲሁም /በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፥18/ ላይ እንደተጻፈው ‹‹ኢየጎድገክሙ ዕጓለ ማውታ ትኩኑ›› (ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም) ሲል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን አጽናንቷቸዋል፡፡ 
/በሉቃስ ወንጌል 24 ቁጥር 49/ ላይ እንደተጻፈው የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርግ ሲል ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም›› (እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ) አላቸውና ዐረገ፡፡ እነርሱም ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ በኢየሩሳሌም በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው ተሰብስበው ሳሉ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአረገ በአሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን የጰራቅሊጦስ እለት ጧት በሦስት ሰዓት ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወረደላቸው ከዚህ በኋላ ፍርሃት ከውስጣቸው ወጣ መንፈሳዊ ድፍረት አገኙ፡፡ አንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ብቻ ነበር የሚያውቁት ሰባ አንድ ዓይነት ቋንቋ (የአገሩ ሁሉ ቋንቋ) ተገለጸላቸው፡፡ ከእነርሱ ጋር በሰባ ሁለት ዓይነት ቋንቋ ተናገሩ፡፡ የአገሩ ሁሉ ቋንቋ የተገለጸላቸውም ሁሉንም በአገሩ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከተለያየ ክፍለ ዓለም የመጡ ነበሩ፡፡ እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንዴት የእኛን አገር ቋንቋ ሊናገሩ ቻሉ? በማለት ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ፡፡ ሌሎች ግን ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረው ነው አሉ  ነገር ግን 
ቅዱስ ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡- የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፡- ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ቃሎቼንም አድምጡ፡፡ ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና ነገር ግን ይህ በነቢዩ ኢዩኤል የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፡- ይህም ‹‹እግዚአብሔር ይላል በኋለኛይቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡ ድንቆችንም በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር ደምም፣ እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል የታወቀችዋም ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል›› /ኢዩ. 2፥28-32/ ይህን መሠረት በማድረግ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብን የሚነካ ትምህርት ሰጠ፡፡ ሕዝቡም ቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትምህርት ልባቸው ተነካ ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? አሉአቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሠረይ ዘንድ ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው 
ስለዚህ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ዓለም አድኑ ብሎ መከራቸው፡፡ በዚህ ቀን ሦስት ሺህ ሰዎች አምነው ተጠመቁ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነሱ ላይ ሲያድር ለቤተክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ይህ የጰራቅሊጦስ በዓል በግሪኮች ቋንቋ ጰንጠቆስጤ ይባላል፡፡ ጰንጠቆስጤ ማለት ሃምሳኛ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሃምሳኛው ቀን ነው፡፡ ይህም ዕለት በዓለ ሃምሳ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡ 
እንዲሁም ታላቁ ሊቅ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል በሚገባ አነጋገር ‹‹የቤተክርስቲያን የልደት ቀን›› ብሎታል፡፡ ይህ በዓል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዓል (በዓለ ሰዊት) ይባላል፡፡ እስራኤል የነጻነት በዓላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዓለ ፋሲካ ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው ይሰነብታሉ፡፡ በሃምሳኛው ቀን በዓለ 
ሰዊትን (የእሸት በዓላቸውን) ያከብራሉ፡፡ በሀገራቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት በሀገራችን ከመስከረም እስከ ኅዳር እንዳለው የእሸት ወራት (የጸደይ ወራት) ነውና የእሸት በዓላቸውን የሚያከብሩት በኦሪት ዘሌዋውያን /ምዕራፍ 23፥10-17/ በታዘዘው መሠረት ማንኛውም እሥራኤላዊ ገበሬ ከዘራው ሁሉ በያይነቱ እሸቱን ቆርጦ ተሸክሞ ወደ ምኩራቡ ይመጣል፡፡ በቤተ መቅደስ 
የሚያገለግለው ካህን ተቀብሎ ባርኮ ጸልዮ የሚጠበሰው እየተጠበሰ የሚታሸው እየታሸ በማኅበር አንድነት ይበላል፡፡ ይህም ‹‹ቀዳምያት›› ይባላል፡፡ የመጀመሪያው ማለት ነው፡፡ ከማንኛውም በረከት የመጀመሪያው እግዚአብሔር ፊት መቅረብ፣ ለእግዚአብሔር መሰጠት እንዳለበት ታዟልና፡፡ 
በዚህ መሠረት ከበዓለ ጰራቅሊጦስ የምንማረው፡-ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ›› ባላቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ተቀምጠው ተስፋውን ሲጠባበቁ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ ዛሬ መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ናት ‹‹ ሚ መጠን ግርምት ዛቲ ዕለት ወዕፅብት ዛቲ ሰዓት እንተ ባቲ ይወርድ መንፈስ ቅዱስ እመልዕልተ ሰማያት››     (ይህች ቀን ም ያህል የምታስፈራ ናት? ይህች ሰዓት ምን  ያህል የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት) /ሥርዓተ ቅዳሴ/ ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ለእኛም እንዲወርድልን ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ይገባል፡፡ ከቤተክርስቲያን ተለይቶ ጽድቅ የለም
ቤተ ክርስቲያን፡- የመንግሥተ ሰማያት በር ናት ‹‹ዛቲ ይእቲ ኆኅታ ለሰማይ›› (ይህች የሰማይ ደጅ ናት) /ዘፍ 28፥17/
በዚህ መሠረት ለእኛም በ40 ቀንና በሰማንያ ቀን የተሰጠን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅና ጧት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ይገባል፡፡ 
ለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም ቅዱሳን በአማላጅነታቸው ይርዱን፡፡ 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡፡