Get Mystery Box with random crypto!

ዕለተ ሠሉስ ዕለተ ተስዕሎ/የጥያቄ ቀን ይህ ቀን ጌታችን በዕለተ ሰኑይ/ሰኞ/ በተናገረውና ባደረገ | 🔴 ምክረ አበው MEKRA ABAW™

ዕለተ ሠሉስ
ዕለተ ተስዕሎ/የጥያቄ ቀን

ይህ ቀን ጌታችን በዕለተ ሰኑይ/ሰኞ/ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ ቀን ይባላል። ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምር ነው፡፡

በዚህ ዕለት አይሁድ ጌታን የተንኮል ጥያቄ ጠይቀውታል። ጌታም አይሁድን ጥይቋቸዋል። አይሁድ የጠየቁት ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡

በዕለተ ሠሉስ(ማግሰኞ ዕለት) ፍጥረትን(ዕፅዋትን) በቃሉ የፈጠረውን አምላክ በዕለተ ሠሉስ አይሁድ ጠየቁት። ቀዳሜ ፍጥረት አዳም በዚህች ዕለት የተፈጠረቺውን ዕፀ በለስን በልቶ ከእግዚአብሔር ፊት በተሸሸገ ጊዜ " አይቴ ሀሎከ አዳም?" "አዳም ሆይ ወዴት ነህ" ብሎ አዳምን በገነት የጠየቀውን አምላክ አይሁድ በምድር ጠየቁት።

"ዘስልጣኑ ዲበ መትከፍቱ" የተባለውን አምላክ አይሁድ "ይህን በማን ስልጣን ታደርጋለህ?" አሉት።

ለሐዋርያት ስልጣነ ክህነትን የሰጠ፤ ነሥታትን የሚሾም፣ የሚሽረውን አምላክ አይሁድ ግን ስለስልጣኑ ጠየቁት። "ነገሥታት በእንቲአከ ይገድፉ ጌራ ወእጠቆሙ ይፈትሁ ሐራ(ነገሥታት ስላንተ ዘውዳቸውን ያወርዳሉ። ሰራዊቶቻቸውም ትጥቃቸውን ይፈታሉ።) የተባለለትን ጌታ አይሁድ ግን ከሮም መንግስት ሊያጋጩት የተንኮል ጥያቄ ጠየቁት። ይህን የታገሰ የጌታችኝ ትሕትና ምን ይደንቅ፣ ምን ይረቅ።

አይሁድ ይህን "ይህን በማን ስልጣን ታጀርጋለህ?" ብለው መጠየቃቸው የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለ ተሞላ እንዲሁም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነበር። ጌታ ይህንን በራሴ ስልጣን አደርጋለሁ ብሏቸው ቢሆን ገበያ መፍታት፣ ነጋድያንን ማባረር የመንግስት ድርሻ ነው። ይሄስ በሮማ መንግሥት ላይ የተነሳ ነው ብለው ለመክሰስ ነበር አላማቸው።

"እግዚአብሔርሰ ልበ ይሬኢ/እግዚአብሔርስ ልብን(የልብን ሐሳብ) ያያል" እንዲል እግዚአብሔር ወልድ የተባለ ማዕምረ ኅቡዓት የሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸሐፍት፣ ፈሪሳውያንን የልባቸውን ሐሳብ እውቆ እንዲህ ብሏቸዋል።


"እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ" ብሎ አንዲት ጥያቄ ጣየቃቸው። "የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?" አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ።
ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።" ማቴ 21 ÷ 24-27
ጌታም እንዲህ ብሎ ከመለሰላቸው በኋላ አንድ ምሳሌ ነገራቸው ቅዱስ ማቴዎስ እንዲህ ይተርከዋል።

----------
28፤ ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው።

29፤ እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ።

30፤ ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።

31፤ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።

32፤ ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።"

ከላይ ጌታ ለአይሁድ የነገራቸውን ምሳሌ ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ተርጉመውታል። ታላቅ ልጅ የተባሉት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ናቸው። ታናሽ ልጅ የተባሉት ደግሞ ኃጥአን መጸብሐን ናቸው። ታላቁ ልጅ እሄዳለሁ ብሎ እንደቀረ ጸሐፍት ፈሪሳውያንም ኦሪትን ተቀብለው በወንጌሉ ሳያምኑ ቀርተዋልና። ታናሹ ልጅ ደግሞ አልሄድም ብሎ እንደሄደ ኃጥአን መጸብሐንም ሕጉን ካፈረሱ በኋላ በወንጌል አምነዋልና።

እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር ለብርሃነ ትንሣኤሁ በፍስሐ ወበሰላም።
ምክረ አበው
በቴሌግራም
@mekra_abaw
በዩቲዩብ ማግኘት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/channel/UCfWtKqb7qsxjXey4kN_tykg?sub_confirmation=1