Get Mystery Box with random crypto!

#ቤተክርስቲያን_እና_መጽሐፍ_ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን የዶግማዋ፤ የቀኖናዋ፤ የትውፊቷ | 🔴 ምክረ አበው MEKRA ABAW™

#ቤተክርስቲያን_እና_መጽሐፍ_ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን የዶግማዋ፤ የቀኖናዋ፤ የትውፊቷ፤ የባህሏ እንዲሁም የዝማሬዋ ወዘተ መገኛ ነው፡፡
በጥቅሉ መጽሐፍ ቅዱስ ፡-
1ኛ.የመሰረተ እምነትዋ(ዶግማ) ምንጭ እና መገኛ ነው
2ኛ.የሥርዓትዋ ምንጭ ነው
3ኛ የባህልዋ ምንጭ ነው
4ኛ የዝማሬዋ ምንጭ ነው
5ኛ የጸሎትዋ ምንጭ ነው፡፡

1ኛ #የመሰረተ_እምነትዋ_ምንጭ_ነው፡-
ይህንን ስንል የቤተክርስቲያን መሠረተ እምነት የምንለው አምስቱን አዕማደ ምስጢር እና ሰባቱን ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ራሱን መጽሐፍ ቅዱስንም ጨምሮ ነው፡፤ ቅዱስ ጳውሎስም አምስቱ አዕማደ ምስጢራት የቤተክርስቲያን መሰረታዊ የእምነት ትምህርተ እንደሆኑ ለማስረዳት‹‹በማኅበር እልፍ ቃላት ከምናገር ይልቅ በአእምሮዬ አምስት ቃላትን ብናገር እወዳለሁ›› ብሎ ያስተማረው 1ቆሮ14÷19፡፡ እነዚህም በጥቂቱ ሲዘረዘሩ፤ ስለ ምስጢረ ሥላሴ ዘፍ1÷26 ዘፍጥ18÷1 ማቴ 28÷19 ቆሮ13÷13 እና በመሳሰሉት ተዘርዝሯል፡፡ ምስጢረ ሥጋዌ የአምላክ ሰው መሆን ምስጢር ነው ይህንንም የተማርነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው መዝ. 8÷2 መዝ.113÷3 መዝ131÷6 ሉቃ2÷10 ዮሐ1÷14፤ የምስጢረ ጥምቀትንም ትምህርት የተማርነው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ለማየት እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥቅሶች ማየት ጠቃሚ ነው ማቴ. 3÷16 ዮሐ 3÷5 ማቴ 28÷19 ምስጢረ ቁርባንንም የተማርነው እንዲሁም የምንማረው እና የምናስተምረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው ዘጸ12÷1 ማቴ. 26÷26 1ኛቆሮ. 11÷26 ምስጢረ ትንሳኤ ሙታንንም የተማርነው የምንማር እና ምናስተምረው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው 1ተሰ. 4÷13-17 2ኛተሰ.2÷1 የምስጢራተ ቤተክርስቲያን መገኛ ምንጭ መሰረትም መጽሐፍ ቅዱስ ነው ይህንንም በምሳሌ እንይ ምሳሌ የምስጢረ ጥምቀት ሥርዓትን በተመለከተ ማቴ 28÷19 ሮሜ 6÷3 የምስጢረ ሜሮንን ሥርዓት በተመለከተ ደግሞ ዘፍ 28÷18 ያዕቆብ ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ ዘይት መቀባቱ አዲስ ቤተክርስቲያን ሲመረቅ በሊቃነ ጳጳሳቱ አማካይነት በሜሮን ለመክበሩ፤ ምዕመናን በሜሮን አማካኝነት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እንደሚያገኙ የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ የምስጢረ ቁርባንን ሥርዓት በተመለከተ ዮሐ. 6÷53 መዝ 4÷7 1ኛቆሮ.11÷27 ላይ ተጽፏል፡፡ የምስጢረ ክህነት ትምህርትንም ያገኘነው ከሊቀ ካህናት ክርስቶስ ነው፡፡ ማቴ16÷19 በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድር የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆና በማለት ዮሐ. 20÷22 ስለ ሥርዓተ ክህነት ሲመተ ክህነት 1ኛጢሞ.3÷8 ምስጢረ ንስሐን በተመለከተ ደግሞ በማቴ 9÷13 ሕዝ.18÷27 ሉቃ.15÷4 ማቴ.8÷4 ራስህን ለካህን አሳይ በማለት ሊቀ ካህናት መምህራችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ የምስጢረ ተክሊልን ሥርዓት በተመለከተ ማቴ.19÷5 ሁልጊዜ በሥርዓተ ተክሊል ላይ የሚነበበብ ነው፡፡ኤፌ.5÷28-32 የምስጢረ ቀንዲልን ሥርዓት በተመለከተ ኢሳ.1÷6 ያዕ.5÷14 ተጽፎ እናገኛለን፡፡

2ኛ- #የቤተክርስቲያን_የሥርዓትዋ_ምንጭ_ነው፡-
የሥርዓተ ቅዳሴው መገኛ ምንጩ በሥርዓተ ቅዳሴ ሚከናወነው ሚነበበው ሚዜመው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በቅዳሴ መግቢያ ላይ ምዕመናኑ ከካህናቱ ጋር በኅብረት ‹‹በቅዳሴ ወቅት ከምዕመናን መካከል ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባ ቢኖር ሥርዓተ ቅዳሴው እስኪያልቅ የማይታገስ ቅዱሳት መጻህፍትን የማይሰማ ቅዱስ ቁርባንን የማይቀበል ቢኖር ከቤተ ክርስቲያን ይውጣ ሐዋርያት አብጥሊስ በተባለ መጽሐፋቸው እንዲህ እንዳስተማሩን›› እያልን ምንዘምረው ከሰማንያ አንዱ በመጽሐፈ አብጥሊስ ቅዱሳት መጻሕፍት በአንዱ እንዲህ ስለተጻፈ ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ መሐሉ መጽሐፍ ቅዱስ ማጠናቀቂያው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በሥርዓተ ቅዳሴ መጽሐፍ ቅዱስ የማይነበብበት ክፍል የለም፡፡ የሐዲስ ኪዳንን ቅዳሴ የጀመረውም ጌታ ነው፤ ‹‹አመስግኖም ይህ ሥጋዬ ነው ብሎ ሰጣቸው›› እንዲል ማቴ 26÷26፡፡ መንበሩን እየዞሩ የሚያጥኑት ሲያጥኑም የሚናገሩት በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 6÷13-15 የተጻፈውን እየደገሙ ነው፡፡ የዕጣኑም ሥርዓት በራእ8÷3-4 ካህናት የሚለብሱት ልብስ፤ ሲካኑ የሚፈጸመው ሥርዓት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ዘጸ 39÷1 ዮሐ 20÷22

3ኛ- #የቤተክርስቲያን_የባህሏ_ምንጭ_ነው፡-
የለቅሶ ባህል ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ሰው ሲሞት ፍትሐት ምንፈታው ከእናንተ ያዘነ ቢኖር ይጸልይ መጽሐፍ ቅዱስ ስላስተማረን ነው ያዕ5÷13 ሥርዓተ ታቦት ዘንግስ፤ ታቦታቱን ካህናቱ አክብረው ሲወጡ ምዕመኑ እልል እያለ እየተከተለ የሚሄደው ለታቦቱ የሚሰግደው በታቦቱ ላይ ስመ እግዚአብሔር ስለሚጻፍ ለሱም መስገድ እንደሚገባን መጽሐፍ ቅዱስ ስላስተማረን ነው ፊል2፤10 ታቦታቱን ተከትለን የምንዞረው ተከተሉ ተብለን መበጽሐፍ ቅዱስ ስለታዘዝን ነው ኢያሱ3፤3 የምግብ ሥርዓታችን ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ይህን ብሉ ይህን አትብሉ ተብለን ታዘናልና ዘሌ11፤1ጀምሮ፡፡ የበዓላቶቻችን ምንጭ መገኛ መሰረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ዘሌ 23÷1

4ኛ. #የጸሎትዋ_ምንጭ_መገኛው_ነው፡-
ከጸሎት መጻህፍት አንዱና ዋነኛው መዝሙረ ዳዊት ሲሆን መዝሙረ ዳዊት በቤተክርስቲያን የማይጸለይበት አንድም ቀን የለም አይኖርምም፡፡ ሌላው በሁሉም ምዕመናን የሚወደድ ጸሎት እና የጸሎት መጽሐፍ ውዳሴ ማርያም ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ለምሳሌ የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ለእስራኤል የነገሠ ዳዊት ከቤተልሔም ምንጭ ውሃ ሊጠጣ ወደደ 2ኛ ሳሙ 23÷15-17፤ 1ኛዜና.11÷17-19

5ኛ- #የዝማሬዋ_ምንጭ_መሰረት_ነው፡-
በቤተክርስቲያናችን ትምህርት የዜማ ቤት ትምህርት ከውዳሴ ማርያም ቀጥሎ የሚሰጠው የዜማ ትምህርት መዝሙረ ዳዊት ነው የቅዱስ ያሬድ አምስቱ የዜማ መጻህፍቶቹ ምንጭ መገኛቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ለዚያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለምሳሌ ማቴ24 ላይ ጌታችን ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ ያለውን ቅዱስ ያሬድ በድጓዋው በለስ ያላት ቤተ እስራኤልን ነው ብሎ ተርጉሞታል፡፡
የሰዓታት ዜማ ምንጭ መገኛው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ‹‹ኢሰማዕነ ወኢርኢነ ወኢነገሩነ አበዊነ ከመቦ ባዕድ አምላክ ዘእንበሌከ አልሰማንም አላየንም አባቶቻችንም አልነገሩንም ካንተ በቀር ሌላ ባእድ አምላክ አናመልክም›› ይህም በዘዳ. 4÷35 ተጽፏል፡፡

(በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ትምህርትና ሥልጠና ዋና ክፍል የተዘጋጀ፡፡)
ዘወትር ምክረ አበውለማግኘት ሰማያዊውን ነክታችሁ ተቀላቀሉ ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ
@mekra_abaw
@mekra_abaw
@mekra_abaw