Get Mystery Box with random crypto!

#ቅዱስ_ቶማስ_ዘመርዓስ_ የመርዓስ ኤጵስ ቆጶስ የነበረው አባት አባ ቶማስ ክርስቶስን በማመን በጾም | Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት

#ቅዱስ_ቶማስ_ዘመርዓስ_
የመርዓስ ኤጵስ ቆጶስ የነበረው አባት አባ ቶማስ ክርስቶስን በማመን በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ፣ ቀንና ሌሊት በመትጋት ለድኆችና ለምስኪኖችም በመራራት ተጠምዶ የሚኖር ነበር። በዚህ ፅናቱ የክብር ባለቤት ጌታችን መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስ ቆጶስ ይሆን ዘንድ መንጋውንም ይጠብቅ ዘንድ መረጠው አባታችን ቶማስም ሐዋርያዊ ተልዕኮውን እየፈፀመ፣ ሕዝቡን እየመራ ሳለ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በሱ ላይ፣ በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ ላይም ተነሳባቸው፣ ክርስቲያኖችንም ያሰቃያቸው ጀመር በአንድ ወቅት ከመኳንንቶች አንዱ የነበረው፣ ቅዱስ ቶማስን ወደ እርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ እነርሱም እየደበደቡ በምድር ላይ እየጎተቱ ወሰዱት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ ከዚህም በኋላ መኮንኑ ቅዱስ ቶማስን ለአማልክት ስገድ አለው ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት «እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣኦታት አልሰግድም ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና» በዚህም ጊዜ መኮንንኑ በጣም ተቆጥቶ እጅግ የበዛ ስቃይን አሰቃየው የነዳጅ ድፍድፍን አፍልተው በላዩ በአፉና በአፍንጫው እስከመጨመርም ደረሱ ልባቸው እንደ ድንጋያ የፀና ስለ ነበር ቅዱስ ቶማስን ገድለው ቶሎ ማሣረፍ አልፈለጉም ይልቁንም የስቃዩን ዘመን አስረዘሙ እንጂ እርሱም ስለ ስህተታቸው ይዘልፋቸው ነበር፣ እንደ ማይመልስም ሲገባቸው በጨለማ ቦታ ጣሉት በየዓመቱም ወደ እርሱ እየሄዱ ከሕዋሳቱ አንድ፣ አንዱን ይቆርጡ ነበር፡፡
በዚህም ለሃያ ሁለት(፳፪) ዓመት ቆየ ሲቆይ ግን አፍንጫውን፣ ከንፈሮቹን፣ ጆሮዎቹን፣ እጆቹንና እግሮቹን ቆርጠው ነበር፤ በዚህም ምክንያት የአገሬው ሰው ሞቷል ብለው አስበው በየዓመቱ መታሰቢያ ያደርጉለት ነበር ይህ ለምን ሳይሞት ቢሉ ጊዜው ሲረዝም ቢሞት ነው እንጂ እስካሁንማ ይመጣ ነበር ብለው ስላሰቡ ነበር፤ ነገር ግን ከሕዋሳቶቹ አብዛኛው ክፍል ቆርጠው ቢጥሉትም አካሉ ግን ተቆራርጦ ሲጣል አንዲት ሴት አየችው፣ ይህችም ሴት በሌሊት ወደርሱ ተሠውራ በመሔድ ትመግበው ነበር፡፡
ጻድቅ ቈስጠንጢኖስም እስከነገሠና የቀናች የክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከገለጥ ድረስ እንዲህ ሲሰቃይ ኖረ፡፡
#ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ ስለክርስቶስ በመታመን የታሠሩ እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ በማዘዙ ሁሉም ተፈቱ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ግን የተጣለበት ቦታ፤ በሕይወት ያለም ስላልመሠላቸው አላወጡትም ነበር፤ ነገር ግን ይህን አዋጅ ትመግበው የነበረችው ሴት ሰምታ ነበርና ወደ ካህናቱ ዘንድ ሄዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ሃያ ሁለት ዓመት በዚያ ስለመኖሩ ነገረቻቸው ቦታውንም አመለከተቻቸው እነርሱም ባገኙት ጊዜ አንስተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑም ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደስ ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ ከርሱ ይባረኩና የተቆረጡ ሕዋሳቱንም ይሳለሙ ነበር፡፡ ከቦታ ቦታ ይዘዋወር የነበረውም በቅርጫት ኹኖ በዘህያ ላይ ተጭኖ ነው፡፡

ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ የከበሩ ፫፻፲፰ ኤጲስ ቆጶሳትን (ሠለስቱ ምዕት) የአንድነት ጕባኤን በኒቂያ አገር በሰበሰበ ጊዜ ይህ አባት (ቅዱስ ቶማስ) ከሠለስቱ ምዕት አንዱ ነበር፤ ወደ ኒቅያ ጕባኤ በቅርጫት ሁኖ በአህያ ተጭኖ እየሄደ መሆኑን አርዮሳውያን ሲሰሙ፤ ቶማስማ በጕባኤው ከተገኘ ተከራክሮ ይረታናል አንችለውም በማለት መንገድ ላይ ባደረበት ይዘውት ይጓዙት የነበሩትን አህዮች በጨለማ በሰይፍ መተዋቸዋል፤ ነገር ግን ሌሊት ሊነጋጋ ሲል ለመንገድ ሲነሱ ቶማስ በተዓምራት አግልጋይ ረድኡን የተቆረጡትን የአህያዎቹን አንገታቸውን ከሰውነታቸው አጋጥመው ይነሳሉ ብሎ ሲያዘው የአንዱን አህያ ከሌላኛው አህያ ቢያጋጥመውም ቅሉ አህዮቹ ሕይወት አግኝተው ጕባኤ ኒቅያ አድርሰውታል፤ በዚያም አርዮስን መልስ እስኪያጣ ድረስ በጽናት ሲከራከረውና መልስ ሲያሳጠው የጕባኤው ሊቀ መንበር ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እስኪደነቅ ድረስ በማየቱ ሃይመኖትስ የእነ ቶማስ ዘመርዓስ ነች ብሎ አጽንቶ ወስኗል፡፡ በጕባኤውም አርዮስን ተከራክረው ከረቱ በኋላ አውግዘው ለይተውታል፤ ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ፤ ሕግና ሥርዐትን ሥጋዊና፤ መንፈሳዊ ፍርድንም ሰሩ። ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ ከተመለሰ በኋላ ካህናቱና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ አነበበላቸው እርሱንም እንዲያስተውሉት እንዲጠበቁትም በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው፡፡ ይህ አባት ለ፵ ዓመት ያህል በሢመቱ አገልግሎ በነሐሴ ፳፬ ቀን አርፋል፡

በቀጨኔ ደ.ሰላም መድኀኔዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት የተዘጋጀ ::/
፠፠፠
#share
.Facebook...
https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
.YouTube... https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
.Telegram...
https://t.me/medihanaelem
http://tiktok.com/@finotehiwot
www.finotehiwotsundayschool.com
#Share #like