2022-04-18 23:53:11
በድር ክፍል ሶስት
በበድር እለት የተከሰቱ አጃኢቦች
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሰሀቦች ለነብዩ ሰ.0.ወ እኛ ሙሳ ዐ.ሰ ወገኖቹ ሂድ አንተ እና ጌታህ ተዋጉ እንዳሉት አንልህም። ይልቁንስ ከቀኝህም ከግራህም ከፊትህም ከኋላህም ሆነህ እንዋጋለን ብለው ነበር።
ሀኪም ኢብኑ ሂዛም ለኡትባ ይህን ጦር ይዘህ ተመለስ ዘልአለም ምትወደስበት ነገር ነው ብሎት ነበር። ኡትባ በነገሩ ሲስማማ አባ ጀህል ግን ኡትባ እንመለስ ያለው በፍርሀት ነው እንጂ አምኖበት አይደለም አለ። ኡትባ መልሱን ሲሰማ ከእኔ እና ከእሱ ማን እንደፈራ ያያል። አለ አቡ ጀህል የኡትባን ሀሳብ አከሸፈ ስሜት ጥበብን አሸነፈ። ነብዩም ሰዐወ ውጊያው ሊጀመር ሲል በቀይግመል ላይ ኡትባን ሲመለከቱ "ከመሀከላቸው በጎ ሰው ቀይ ግመል ላይ የተቀመጠው ብቻ ነው እሱን ከተከተሉ ቅኑን መንገድ ይይዛሉ " ብለው ነበር።
ነብዩ ሰዐወ የሙስሊሞችን ረድፍ ሲያስተካክሉ እንጨት ይዘው ነበር ለአንድ ሰሀባ "ሰዋድ ሆይ ሰልፍህን አስተካክል" ብለው ወጋ አደረጉት። እሱም "አሳመሙኝ እኮ ብድሬን ልመልስ ይፍቀዱልኝ" አለ። እሳቸውም ሆዳቸውን ገልጠው "ብድርህን መልስ" አሉ እሱም አቀፋቸው እና ሆዳቸውን ሳማቸው።ለምን እንዲ እንዳደረገ ሲጠይቁት "ምናልባትም በዚህ ጦርነት ከሞትኩኝ ከእርሶ ጋር ባለኝ የመጨረሻ የግንኙነት ቅፅበት ቆዳዬ የእርሶን ቆዳ እንዲነካ ፈለግኩኝ" አለ እሳቸውም ዱዐ አደረጉለት።
ኢብሊስ በሱራቃ ቢን ማሊክ ተመስሎ መጥቶ ነበር ከዚያም መላኢኮች ሲወርዱ ደንገጦ ሲሸሽ ሀሪስ ቢን ሀሺም አጥብቆ ሲይዘው ደረቱን መቶት አመለጠ ሙሽሪኮችም "ሱራቃ የት ትሸሻለህ ጎረቤታቹ ነኝ ትለን አልነበር ሲሉት" እናንተ ማታዩትን አያለው አላህንም አፈራለው ቅጣቱም ብርቱ ነው እያለ ሸሽቶ ወደ ባህር ሰመጠ።
የኡካሻ ቢን ሙህሲን ሰይፍ ተሰበረ። ነብዩ ሰዐወ እንጨት ሰጥተውት በዚህ ተዋጋ አሉት ተቀብሎ ሲነቀንቀው ረጅም እና ጠንካራ አብለጭላጭ ሰይፍ ሆነ። በሱም ተዋጋ ሰይፉ "ዓውን" (እገዛ) ተብሎ ይጠራ ነበር። በ "ሁበሩ-ሪዳህ" ጦርነት ሸሂድ እስኪሆን በእያንዳንዱ ጦርነት ተዋግቶበታል።
አል ማዚኒይ እንዲህ ብሏል "አንዱን ካፊር ልመታው እየተከታተልኩት ሳለ ገና ሳልደርስበት ጭንቅላቱ ከአካሉ ተነጥሎ ወደቀ"። በተመሳሳይ ሌላኛው ሰሀባ አንድን ሙሽሪክ እየተከተለ ሳለ ከበላዩ የአለንጋ ድምፅ ሰማ "አይዞህ ቅደም" የሚል ድምፅም ከጆሮው ደረሰ ወደ ኋላ ሲዞር ሰውየው ወድቆ ተመለከተ የአለንጋ ግርፋት ፊቱን ሰንጥቆት፣ አፍንጫውን ሰብሮት፣ አካሉ ወይቦ ተመለከተ። ክስተቱን ለረሱል ሰዐወ ሲነግራቸው "ከሰማይ የመጣ እገዛ ነው" አሉት። ሌሎችም ሰዎች ማንም አጠገባቸው ሳይታይ አንገታቸው ተቆርጦ ይወድቅ ነበር።
አቡ ለሐብ ስለሽንፈቱ የሰማው ከአቡ ሱፍያን ሲሆን ከሰማይና ከምድር መሀከል ቦቃ ፈረስ ጋላቢዎች ነበር የገጠሙን ከፊት ለፊታቸው ማንንም አያስቀሩም ሲልም አከለ። በቦታው የነበረው አቡ ራፊዕ "ወላሂ መላኢኮች ናቸው" አለ አቡ ለሐብ ዘሎ ያዘው ከመሬት ላይ ጣለው። ደካማ ስለነበር መቋቋም አቃተው እላዩ ላይ ተከምሮ ይመታው ጀመር። ኡሙ ፈድል እንጨት አንስታ መታችው ጭንቅላቱ ተፈንክቶ ውርደትን ተከናንቦ ሄደ። ከሳምንት በላይ በህይወት አልቆየም አላህ "አደሰህ" በተሰኘ በሽታ (ቁስል) አስያዘው። በሽታው አረቦች ዘንድ ስለሚፈራ ልጆቹ እንኳ አግልለዉት ብቻውን ተሰቃይቶ ሞተ። ለሶስት ቀናት ሬሳውም አልተቀበረም። የሚደርስባቸውን ነቀፌታ ፍራቻ ጉድጉዋድ ቆፍረው በእንጨት ገፍተው ከተቱት እና ጉድጉዋዱን በድንጋይ እየወረወሩ ሞሉት።
መካዊያን በሽንፈቱ ተዋከቡ ሙስሊሞች እንዳይደሰቱ በሚል ለሞቱ ቤተሰቦቻቸው በቅጡ አላለቀሱም ነበር። አስወድ የተሰኘ በበድር ሶስት ልጆቹን ያጣ አይነስውር በሌሊት የአልቃሽ ድምፅ ሲሰማ አገልጋዩን "ሆዴ ተቃጥሏል ለልጄ አቡ ሀዚማ ላልቅስለት ሂድና መካ ለሙታኖቿ እያለቀሰች እንደሆነ አይተህ ና" አለው አገልጋዩ ቃኝቶ ሲመለስ "አንዲት ሴት ግመሏ ጠፍቷት እያለቀሰች ነው" አለው አስወድ ራሱን መቆጣጠር ተሳነው መካ ለአብራኮቿ ክፋይ ማልቀስ ተስኗት ለአንዲት ግመል መለቀሱ ሆድ ባሰው። ስሜቱንም እያንጎራጎረ ገለፀ።
ይቀጥላል. . .
@mebrukmuhammed
583 viewsedited 20:53