Get Mystery Box with random crypto!

“አንድ ሰው በትርፍ ጊዜው ብዙ ሙታን ወደተቀበሩበት የመቃብር ስፍራ ሄዶ በሰዎች መቃብር ላይ የተጻ | Master Mind Group

“አንድ ሰው በትርፍ ጊዜው ብዙ ሙታን ወደተቀበሩበት የመቃብር ስፍራ ሄዶ በሰዎች መቃብር ላይ የተጻፉትን ጽሑፎች በማንበብ ላይ ሳለ፣ በአንድ ሰው መቃብር ላይ አንድ ግር የሚል ጽሑፍ አነበበ።

ጽሑፉ በ”30 ዓመቱ ሞተ፣ በ60 ዓመቱ ተቀበረ” ይላል።

ግር ብሎት ቆሞ ማሰላሰል ጀመረ፡፡ “አንድ ሰው በ30 ዓመቱ ሞቶ እንዴት ለ30 ዓመታት ሳይቀበር ሊቆይ ቻለ?” ይህንን እያሰበ የጽሑፉን ትርጉም የሚያውቅ አንድ ሰው ደረሰ፡፡

“ምን እንደምታስብ ገብቶኛል” አለው ሃሳቡን አንብቦ፡፡

ጥያቄውን በግምት ደርሶበት ኖሮ በቀጥታ መልሱን ነገረው፡፡

“ይህ ሰው እጅግ በጣም የሚያስገርም ራእይና ዓላማ የነበረው ሰው ነበር፡፡ ብዙ ነገሮችን የመስራት እቅድ የነበረውና በዚህም ትጋቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ እጅግ የታወቀና ለትልቅ ነገር የሚጠበቅ ሰው ነበር፡፡ ልክ 30 ዓመት ሲሞላው በተለያዩ ውጣ ውረዶች በማለፉ ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ ዓላማውን ሁሉ ትቶ ከርታታ ሰው ለመሆን በቃ፡፡

የሚቀጥሉትን 30 ዓመታት እንዲሁ በየቦታው ሲንቀዋለል ነው ያሳለፈው፤ ካለምንም ዓላማ፡፡ የጽሑፉ ትርጉም ይህ ነው፡፡

ሰውዬው ሞተ ብለው የሚያምኑት ራእዩን በጣለበትና ጊዜውን በተራ ነገር ማሳለፍ በጀመረበት በ30 ዓመቱ ነው - በአካል ቢኖርም ሞቷል ነው አባባላቸው፡፡ ልክ በ60 ዓመቱ ታምሞ አካላዊ ሞትን ሲሞት ያን ጊዜ ተቀበረ ማለታቸው ነው”

በአካል መኖር ብቻውን ኖሯል አያስብልም ነው ነገሩ፡፡ ህያው የሚያደርገን ራእይና የመኖር ዓላማ እንጂ ቆሞ መሄድ አይደለም፡፡

ቆሞ ለመሄድ በአራት እግር ሆነ እንጂ አህያም ይሄዳል፡፡ አህያ ግን የሰውን ስራ ከማቅለሉ ውጪ የራሱ ራዕይ የለውም፡፡ ስለሌለውም የሌሎች ባሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡

በሰው ራእይና ዓላማ የለሽ ህይወት ህይወት ሳይሆን ሞት ነው፡፡ ዓላማ አልባው ሰውም ለመቀበር ነፍሱ ከስጋው እስክትነጠል ይጠበቃል እንጂ ሙትማ ሙት ነው፡፡

ሰውን ህያው የሚያደርገው ህልሙ ነው የሚሉ ይመስላሉ ፀሐፊው፡፡ ልክ ነው! ዓላማ ያለው ሰው መሆንና በዓላማው የሚፀና ሰው መሆን ሁለት የስኬት ቁልፎች ናቸው፡፡

ስኬታማ ሰዎች ባለራዕይ ናቸው፡፡ ለራዕያቸውም ታማኝና ፅኑ ናቸው፡፡ ለፈተናም ሆነ ለየትኛውም ነገር በቀላሉ እጅ አይሰጡም፡፡ እጅ አለመስጠታቸው የህያውነታቸው ምልክት፣ የስኬታቸው ጠቋሚ ነው፡፡

ከዓላማ ውጪ የሚኖር ህይወት ከህይወት አይቆጠርም፡፡ ዓላማ ቢስ ወይም ከባለራዕይነት ወደ ዓላማ የለሽነት የመጣ ሰው ኖሯል ለማለት ከባድ ነው።

ምንጭ፦ “25 የስኬት ቁልፎች” የተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ

መልካም ቀን!