Get Mystery Box with random crypto!

[በኢትዮጵያ ያለው] የሕግ የበላይነት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ የላላ [ነው]። ~ ኮሚሽነር | Christian Tadele Tsegaye

[በኢትዮጵያ ያለው] የሕግ የበላይነት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ የላላ [ነው]።

~ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ፒኤችዲ)
****
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በያመቱ የሚያወጣውን የተጠቃለለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ሐምሌ 05/2015 ዓ/ም ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ሪፖርታቸውን በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንዲያቀርቡ በሕግ ከተደነገገላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ ቢሆንም እሰከከዛሬ ድረስ ዓመታዊ ሪፖርቱን እንዲያቀርብ በምክርቤቱ ሁኔታዎች አልተመቻቹለትም። (ሌሎች በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ማቅረብ ያለባቸው አካላት እንባ ጠባቂ፣ ጠቅላይ ፍርድቤት፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ዋና ኦዲተር ይገኙበታል። ከዋና ኦዲተር በስተቀር አንዳቸውም ሪፖርታቸውን እያቀርቡ አይደለም። ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ብናቀርብም እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ አላገኝንም።)

ገዥው ፓርቲ መንግስታዊ ሥልጣኑንና ሕግጋትን ለሥልጣኑ ማደላደያነት በመጠቀም መብት ጠያቂዎችንና ተቺዎችን ከሕግ ውጭ የማሰር፣ የመግደል፣ የመሰወር እና ሌሎችንም ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እየፈፀመ ስለመሆኑ በምክርቤት ልዩ ልዩ አብነቶችን በማቅረብና በማስረጃ በማስደገፍ ጭምር ስንሞግት ነበር። በእንደራሴነት የምናቀርባቸውን ኃቀኛ አስተያየቶች በመቀበል አሰራሩን እና አመራሩን ከማስተካከል ይልቅ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች በሰላማዊ ሰልፍ ለመደበቅ ሲታትር የባጀው ገዥው የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያወጣቸውን ሪፖርቶችም «የጽንፈኞች ክስ ነው በሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኩል የወጣው» የሚል አቋም ስለመውሰዱ የቀደሙ የውስጥ ለውስጥ ውይይቶች አረጋግጠዋል።

ይሁንና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ፒኤችዲ) ኮሚኑ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ባስተላለፉት ቁልፍ መልእክት ውስጥ፤

1/ በሕግ የተደነገገውን አሠራር በቂ ባልሆነ ምክንያት ወደ ጎን በመተው ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ አሠራሮች፣ ድርጊቶች ወይም ሂደቶች፣

2/ በሕግ የተደነገገውን በማስፈጸም ሂደት ተገቢውን የተሳትፎ፣ የምክክር እና የጥሞና ጊዜ ሳይወስዱ ለማስፈጸም መሞከር፣

3/ ተቋማት በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወሰን ውጪ/በመተላለፍ አልያም ከወሰኑ በታች/ሥልጣን እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት እንዲሁም

4/ የተጠያቂነት አለመኖር (impunity)

የሕግ የበላይነት ላለመኖሩ እርስ በእርሳቸው ተመጋጋቢ የሆኑ ምክንያቶች እና አመላካቾች መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተዋል።

በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በሰው ልጆች ላይ ሁሉ የሚፈፀም ወንጀል በመሆኑ ሁላችንም ገዥው የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ሁላችንም ልንተጋ ይገባል።