Get Mystery Box with random crypto!

ዛሬ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው 11ኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስ | Christian Tadele Tsegaye

ዛሬ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው 11ኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች፤
**
አመሰግናለሁ የተከበሩ አፈጉባዔ፤

አመሰግናለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፤

ጥያቄዬን ከማቅረቤ በፊት ስለጥያቄዬ ትንሽ ማለት እፈልጋለሁ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ምክር ቤት እና በተለያዩ መድረኮች ስለእርስዎና ስለሚመሩት የአስፈፃሚ መንግስት ተጠየቅ ሲቀርብብዎ ለተጠየቁ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጠያቂዎችን የሚያጥላላ አስተያየት ሲያራምዱ፤ አለፍ ሲልም ተጠየቅ የቀረበብዎት የወጡበት ብሔርን በመጥላት እንደሆነ አድርገው ምላሽ መስጠትዎ የቅርብ ትዝታ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ቀጥዬ የማቀርብልዎ ጥያቄ ራስዎንና መንግስትዎን የሚመለከት እንጂ ሌላ ማንንም የማይመለከት መሆኑን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። እኔም ጥያቄውን የማቀርብልዎት በብሔር አይደለም። ምላሽ ሲሰጡም የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ የተሼረበ ሴራ ነው የሚል እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ጥያቄዬ የሚከተለው ነው።

የዜጎችን ደኅንነት እና የአገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ ዝቅተኛ የመንግስት ኃላፊነት ሆኖ ሳለ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ፤ ቤታቸው ይፈርሳል፤ ንብረታቸውም ይወድማል። የአገር ሉዓላዊነትን በሚዳፈር መልኩ የጎረቤት አገራት ሰራዊቶች በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ወሰኖች በርካታ ኪሎሜትሮችን ዘልቀው በመግባት ወረራ ፈጽመዋል። አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት ዋነኛ የስጋት ምንጭ ሆኖ የምናየው ራሱ መንግስትን ነው። እርስዎ በአፍዎ «ኢትዮጵያ አትፈርስም» ቢሉንም በተግባር ግን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት በመንግስትዎ እየተናዱ ነው። የበርካታ አገራት መሪዎቸ መሰል ኃላፊነትን በወጉ ያለመወጣት ጉድለት ሲያሳዩ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው ሥልጣናቸውን ሲለቁ ይታያል። በአገራችንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመሳሳይ ሕዝባዊ ተጠየቅ ሲቀርብባቸው ሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

እርስዎስ ሥልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔው አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ? በሰብአዊነት ላይ በተፈፀሙ እንዲሁም የማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳትና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?


አመሰግናለሁ!