Get Mystery Box with random crypto!

አመሰግናለሁ የተከበሩ አፈጉባዔ፤ አመሰግናለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በመጀመሪያ በምክርቤት አባ | Christian Tadele Tsegaye

አመሰግናለሁ የተከበሩ አፈጉባዔ፤
አመሰግናለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤

በመጀመሪያ በምክርቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት በመካከላችን ስለተገኙ ማመስገን እፈልጋለሁ። የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመፍታት የፌዴራሉ መንግስትና የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር በደቡብ አፍሪካ በፈረሙት የሰላም ስምምነትም እንደሕዝብ እንደራሴ በበጎ የምመለከተውና ለሕዝባችንም ለጊዜውም ቢሆን እፎይታን የሰጠ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ።

ከዚህ በመቀጠል ጥያቄዎችን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
1) በመራጭ ተመራጭ መድረክ በነበረን ውይይት ሕብረተሰቡ የአገራችን መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምንድን ነው መጥተው ያልጎበኙን የሚል ጥያቄ አቅርቧል። በተለይም በቋሪት የምርጫ ክልል በቅኔ መፈጠሪያነት በሚታወቀው ዋሸራ ለታሪካዊ የቱሪዝም መስህብነት እጅግ ምቹ ከመሆኑም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ታሪካዊውን ቦታ እንዲጎበኙ እና የመዳረሻ ልማት እንዲሰራላቸው ብርቱ ጥያቄ ስላቀረቡ ይህን የሕዝብ ግብዣና አደራ ለማቅረብ ነው። በተመሳሳይ መንገድ በከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር ከአገራችን የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዘው እና ለአገር ኢኮኖሚም ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለው የምዕራብ ጎጃም ዞን ዩኒቨርሲቲ ስላልተከተፈተለት ከፍተኛ ቅሬታ አድሮበታል። ይኼ የዘመናት ዩኒቨርሲቲ ይከፈትልን የሕዝብ ጥያቄን እንዴት ያዩታል?

2) የፌዴራሉ መንግስት በዚህ ምክርቤት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ትሕነግ ጋር ድርድር አድርጎ ስምምነት ተደርሶ እያለ የመንግስትን አሰራርና አመራር የሚተቹ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እየታፈኑ ለእስር ተዳርገዋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም በየአካባቢው የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን እየነቀሱ የፖለቲካ ትግል እያደረጉ ያሉ የአብን አባላትና አመራሮች ጭምር ታፍነው እየታሰሩ ነው። እርስዎ በዚህ ምክርቤት ጭምር በማሸማገልና በማቀራረብ አግዙን ብለው ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት ለአብነት እነአርበኛ ዘመነ ካሴን ለማቀራረብ ጥረት ብናደርግም ይህን በጎ ጥረት መና በሚያስቀርና የቆዬውን የሕዝብ የሽምግልና ወግና ባሕል በሚጥስ መልኩ እስር እየተፈፀመ ነው። መንግስትዎ እነዚህን ቅሬታዎችና ቅራኔዎች በምን መልኩ ለመፍታትና ከሕዝብ ጋር ያለውን መተማመን ለማሳደግ አስቧል?

3) የፌዴራሉ መንግስት ከትሕነግ ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ስምምነት ያልተደረሰባቸውን አካባቢያዎች «በሕገመንግስታዊ መልኩ ይፈታሉ» የሚል ስምምነት መደረሱን ነግሮናል። ይሁንና አካባቢያዎች (ወልቃይትና ራያ) የኢፌዴሪ ሕገመንግስት ከመጽደቁ በፊት ወደ ትግራይ ክልል በፖለቲካ ውሳኔ የተካለሉ ናቸው። በሁለቱ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝባችን ማንነቱ እንዲከበርለት፣ ባሕሉን እንዲያበለጽግ፣ በቋንቋ ልጆችን እንዲያስተምርና እንዲዳኝ እንዲሁም አስተዳደሩም በማንነት ከሚቀርበው የአማራ ሕዝብ አስተዳደር ጋር እንዲሆን ከ3 አስርት ዓመታት በላይ በሰላማዊ መንገድ ሲታገል ኖሯል። ሕገመንግስታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ተደፍቆ ማንነቱ ተፍቆ የኖረው ወገናችን በኃይል በትግራይ ክልል በሚተዳደርበት ዘመን ሁሉ ጅምላ ፍጅትና ማፈናቀልን ጨምሮ የማያባራ ግፍ ሲደርስበት ኖሯል። የቅርቡን ብናስታውስ እንኳን የማይካድራ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሪፖርት ጭምር ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ መፈፀሙ ተረጋግጧል። ይህ በሆነበት ሁኔታ እነዚህን አካባቢዎች በመስዋእትነታቸው ያረጋገጡትን አንፃራዊ እፎይታ ለአላስፈላጊ ክርክርና ሙግት በሚዳርግ መልኩ ስምምነት መደረሱን እንዴት ያዩታል? 

አመሰግናለሁ!

(በተከበሩ አበባው ደሳለው የጂጋ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተመራጭ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች)