Get Mystery Box with random crypto!

ጀልባዎቻችን እናቃጥል! **** «ሂድና ጀልባችንን አቃጥለው!» ይኼ ለሚወዳት አገሩ ስፔን አዲስ | Christian Tadele Tsegaye

ጀልባዎቻችን እናቃጥል!
****
«ሂድና ጀልባችንን አቃጥለው!»

ይኼ ለሚወዳት አገሩ ስፔን አዲስ ግዛት ለማስገኘት እ.ኤ.አ በ1519 በአገረ ሜክሲኮ ቬራክሩዝ (Veracruez) ባሕር ወሽመጥ ከጦር ጓዶቹ ጋር የነበረ ኼርናንዶ ኮርቴስ ከሥሩ ለነበረው ኮሎኔል ያስተላለፈው አስገራሚ ትዕዛዝ ነው።

የጦር ጀነራሉ ኮርቴስ ከፊት ለፊታቸው እስከ አፍንጫቸው የታጠቀ ጠላት፣ የስንቅ መመናመን እንዲሁም ከዚያ በፊት የማያውቋቸው በሽታዎች ሰራዊቱን እየፈተነው መሆኑን ቢያውቅም ወደ ባሕር ወሽመጡ ያመጧቸውን ጀልባዎች ለማምለጫነት ከመጠቀም ይልቅ ወታደሮቹን ለዓላማቸው እስከመጨረሻው እንዲፋለሙና ኅልውናቸውን በማሸነፍ ላይ ብቻ የተመረኮዘ እንደሆነ የሚያስረግጠውን ቀጭን ውሳኔ አሳለፈ፤ ጀልባዎቹ እንዲቃጠሉ! በኮርቴስ ትእዛዝ መሰረትም ጀልባዎቹ በእሳት ተንቀለቀሉ። የቃጠሎው እሳት በወታደሮቹ ልብና መንፈስ ላይ የቆራጥነት ፍሙን ጣለ። ነበልባሉም ወደ ድል መንገድ የሚመራ ችቦ ተደርጎ ተቆጠረ። በሕይወት ለመቀጠል ያላቸው ብቸኛ ምርጫ ማሸነፍ መሆኑን የተረዱት ወታደሮቹ በጀግንነት ተዋጉ። ኅልውናቸውንም በድላቸው አፀኑ።

አማራ እንደሕዝብ ያጋጠመውን ፈተና ተሻግሮ ኅልውናው የሚቀጥለው ሲያሸንፍ የመሆኑን መሪር ኃቅ ደጋግመን ማሳሰባችን አሁናዊ ትውስታ ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ ለምን አሁን ላለንበት ታሪካዊ ውርደት ተዳረግን? መልሱ ግልፅ ነው፤ ጀልባዎቻችንን ስላላቃጠልን ነው።

«አማራና አማራነት እየተጎዳ፤ ኅልውናውም አደጋ ላይ ነው» እያልን ... ዞር ብለን በአውራጃዊነት ጀልባችን ተሳፍረን እንገኛለን። አማራነትን ከተወለድንበት መንደር ከተቀበረ እትብታችን አንፃር እየለካን የሩቅና የቅርብ አማራ በሚል ወንዜ ጀልባችን ላይ መፈናጠጥ ያምረናል።

የተሰባሰብነውና የተደራጀነው መሰባሰባችን የኅልውናችን እርሾ የሚጣልበት በመሆኑ ነው። የምንሰባሰበውና የምንደራጀው የተጋረጠብንን የኅልውና አደጋ በብቃት እንዳንመክት ትግላችንን እንደጭቃ ግድብ ውሽልሽል ያደረጉብንን ጎታች «ጀልባዎቻችንን» በማቃጥል አማራ በሚለው ኃላችን በክብር ለመገለጥ ነው። የተሰባሰብነው ከሕይወት እጅግ የሚልቅ ዋጋ ያለውን ነፃነት ለሕዝባችን ለማቀዳጀት ነው። የምንሰባሰበው በእኩልነት መሶብ ለሁሉም የሚበቃ የፍትሕ እንጀራን ለማቅረብ ነው። ከጅሩ እስከ ባሕር ዳር፤ ከወልድያ እስከ ጎንደር በአደባባይ ደማቸው የፈሰሰ ወገኖቻችን ሰማእትነትን የተቀበሉት ፍትሕ ለተጠማ ሕዝባችን ሲሉ ነው።

«ታላቁ አማራ ተዋርዷል፤ እንዲህ ተዋርዶ ከምናይ ሞት በስንት ጠዓሙ» ብለን ምለን ተገዝተን ለሕዝባችን ነፃነት ሁለመናችንን አሳልፍን ልንሰጥ ወደ ትግል ሜዳው ከገባን በኋላ... «ታሰርን፤ ተገፋን፤ ስማችን ጠፋ፤ ምቾታችን ተጓደለ፤ ወዘተርፈ» በሚል ወልካፋ የሙሾ ጀልባችን መሳፈር ይዳዳናል። በዚህ ሁሉ መሐል ደግሞ እራሳችንን የአማራነት መስፈሪያ ቁና አድርገን ነቃፊ አደናቃፊ በመሆን በራስ አምልኮ የመታበይ ጀልባችን ላይ ለመምነሽነሽ ልባችን ይቋምጣል። ይህን ሁሉ ሆነን ድል እንናፍቃለን። ድል በትግል እንጂ በምኞት የምንቋደሰው መጎምዠት አይደለምና እነሆ የሆንነውን ሁሉ ለመሆን ተገደናል። ጀልባችንን እናቃጥል!