Get Mystery Box with random crypto!

+++ ‹ሞቴን ባሰብኩ ጊዜ› +++ ዕድሜ በጨመርኩ ቁጥር የዓለምን ከንቱነት እና አለመረጋጋት የ | ማኅቶት

+++ ‹ሞቴን ባሰብኩ ጊዜ› +++

ዕድሜ በጨመርኩ ቁጥር የዓለምን ከንቱነት እና አለመረጋጋት የበለጠ እየተረዳሁ እመጣለሁ፡፡ ስለ ምን ራሳችንን በከንቱ ነገር እናደክማለን? የዕድሜ ዘመናችን እንደ ሕልም ያጠረ፣ እንደ አመድ እና ትቢያ ሆነን በጥቂት ጊዜ ጥፋትን የምንቀምስ አይደለንምን? ዛሬ ጤና አለን ነገ ግን እናጣዋለን፡፡ ዛሬ እንስቃለን ነገ ግን ቁጡ እና ኀዘንተኞች እንሆናለህ፡፡ ዛሬ ከደስታ ብዛት የተነሣ ዓይኖቻችን የእንባን ዘለላዎች አዝለዋል። በቅርቡ ግን በኀዘን እና ሕመም ምክንያት ዓይኖቻችን የልቅሶ እንባን ያዘንባሉ፡፡ ዛሬ ሃብታችን የሚያስተማምን ነው። ነገ ግን በክፉ ገጠመኝ ያለን ይበተንብናል፤ ይወድማልም፡፡ ዛሬ መልካም ዜናን (የምሥራችን) ተቀብለናል፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን መልካሙ በመጥፎ (ክፉ ዜና) ዜና ይተካል፡፡ በከንቱ ነገር ራሳችንን እናደክማለን፡፡ ሕይወት እንደ ሌሊት ሕልም፣ እንደ ጥላም ናት፡፡ ወላጆቻችን፣ ወንድም እኅቶቻችን ፣ የቀደሙ አያቶቻችንስ ወዴት አሉ? እነዚህን ሁሉ መቃብር ተቀብላቸዋለች፡፡ ሁሉም በስብሰዋል በነፍሳትም ተበልተዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን መበስበስ እና መቃብር እኛንም እንዲሁ ልታደርግ ትጠብቀናለች። ወዮ…ወዮ… ሞት ሆይ አንተን ማሰብ ምን ያህል ምሬት ነው!

መድኃኔዓለም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ሥልጣን ሰጥቶናል፡፡(ዮሐ 1፥12) ምሕረት የሌለው ጠላታችንንም እንዋጋበት ዘንድ ብዙ አምላካዊ የጦር መሳሪያዎችን አስታጥቆናል፡፡ ነገር ግን እኛ ከሁሉም በላይ ደግሞ የምሆን ‹እኔ›ን ጨምሮ ክርስቶስ የሰጠንን የጦር እቃ ቸል በማለት የጠላታችን (የሰይጣን) እስረኛ ሆነናል፡፡የነፍሳችንንም ከሥጋችን መለየት ከመፍራታችን የተነሣ ወደ ሞት በቀረብን ጊዜ በስቃይ እና ጣር የምንንቀጠቀጥ፣ በተገኘው መንገድ ሁሉ ምድራዊ ሕይታችንን ለማቆየት የምንጥር ሆነናል፡፡ ሞት ለምን አስፈሪ ሆነብን? እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን ለምን አልተበረታታንም? ወደ ማናውቀው እና እንግዳ ወደ ሚሆን ንጉሥ ነው እንዴ የምንሄደው? አይደለም። ንጉሡማ ነፍሳችንን ከጠላት እጅ ያድናት ዘንድ ደሙን ያፈሰሰልን መድኃኒታችንና ፈጣሪያችን እኮ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ብርታትን እናጣለን? ለምንስ እንፈራለን? በእርግጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች› እንዳለ ሞትስ በጠባይዋ ቀዝቃዛ ናት፡፡ አዎን! ሞት በጠባዕይዋ የቀዘቀዘች ናት፡፡ ነገር ግን ፍርሃት የሚመጣው ከእኛው ኅሊና ነው፡፡ ነፍስ በተገቢው መንገድ እንዳልኖረች፣ በሕግጋቱም እንዳልጸናች፣ የሠርግ ልብሷንም በበጉ ደም እንዳላጠበች ኅሊና በተረዳ ጊዜ፣ ‹ይቀበለኝ ይሆን ወይስ አላውቅሽም ይለኝ? እድን ይሆን ወይንስ እኮነን?› በሚል ፍርዱን በማሰብ ከሚመጣ ፍርሃት የተነሣት በንጉሡ ፊት ራስን ማቅረብ ሐፍረት ይሆናል፡፡ ኃጢአታችንን ፈጽመን ሳንናዘዝ ንስሐም ሳንገባ ነፍሳችን ከሥጋችን ብትለይ ይህች ቀን ነቢዩ ኤርሚያስ የጠቆመን ክፉ ቀናትና ወዮ! ወዮታ! አለብን፡፡(ኤር 17፡17)

‹ስለበጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም› በእኛ የሚሠራ አምላካችን እግዚአብሔር ከእውነተኛ ትሕትና ጋር የጸጸትን መንፈስ፣ የሚገባ የንስሐ ፍሬ ማፍራትን፣ የምሕረት እና የፍቅርንም ሥራ በመስጠት ከዚህ ያድነን ዘንድ እንለምነው፡፡(ፊሊ 2፡13) እንዲህም ከሆነ የእግዚአብሔር እውነተኛ ፍርዱ በእኛ ዘንድ ምሕረት ይሆንልናል፡፡ ስለዚህም የምታስፈራው የሞታችን ሰዓት በመጣች ጊዜ ነፍሳችን በእግዚአብሔር ቸርነት ትበረታታለች ‹ምሕረቱ በእኔ በተዋረደው ባሪያው ላይ እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁ›ም ትላለች!፡፡

++++++አሜን እንዲህም ይሁንልን!++++++++

የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር ብርሃን በመጣ ጊዜ በልቅሶ ነው፡፡ሕይወቱንም በሙሾ እና በኃዘን ያሳልፋል። በመጨረሻም በእንባ እና በሕመም ይህችን ዓለም ይሰናበታል፡፡ ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው። ምኞት ትጠፋለች። ሰውም ወደ ትክክለኛው የሕይወት እውነታ ይነቃል፡፡ ይህችም ከንቱ ሕይወት እንዴት እንደምትነጉድ (እንደምታልፍ) ማንም አያስተውልም፡፡ ዓመታት ያልፋሉ ወራትም ይጠቀለላሉ ጊዜያትም ሳይገቡን ይሳሳባሉ። ድንገትም ‹ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል› የሚል መልእክት ይመጣልናል፡፡(ኢሳ 38፡1) ያን ጊዜም የሰይጣን ማተለል ያለ ግርዶሽ የተገለጠ ይሆናል፡፡የሚሞተውም ሰው ዓለም ስለ እርሱ ምን ዓይነት ጠቃሚ ሚና እንደ ተጫወተች በመረዳት ይሞታል፡፡ ጸጸት እና ጭንቀትን ይሞላል፡፡ በዋዛ ላለፉበትም ጊዜያት ዋጋን ይከፍላል፡፡ ንስሐም ገብቶ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ይችል ዘንድ አንዲት ቀን ለመግዛት ዕድሜ ዘመኑን ያጠራቀመውን ሃብት ሁሉ መስጠትን (መለወጥን) ይመኛል፡፡ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ዕድል እንኳን አያገኝም፡፡ ቀድሞ በሥጋው ወራት ‹ጊዜ› ለዓመታት በእርሱ ቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም፣ ከመጠን በላይ በሥራ በመጠመድ ፣ በመጠጥ ቤቶች ፣ በፊልም ቤቶች እና በአሳፋሪ ምኞቶች አባክኗቸዋል፡፡ ጠቢብስ የዚህችን ዓለም ጊዜያዊ የምድር ሕይወት ማታለል የተረዳ፣ ከብዙም ትርፍ ጋር በሰማይ በእግዚአብሔርም ከተማ ካለው ሃብት ያገኘው ዘንድ ስንቁን ወደ ላይኛው ቤት የሚያግዝ ብልህ ነጋዴ ነው፡፡ ጠቢብስ መከራ የሌለበት የጽድቅን ሕይወት ለዘላለም የሚኖር ነው፡፡ ሰካራም፣ ስግብግብ
፣ ገንዘብ ወዳድ ፣ ነውረኛ ፣ ነፍሰ ገዳይ እንዲሁም የቀሩት ከእኔ ጋር የኃጢአት ማኅበርተኞች የሆኑ እና ዋናቸው የምሆን እኔ ሰነፍ ግን ወደማይጠፋ እሳት እንጣላለን፡፡

እነሆ አሁን ፀሐይ ታበራለች፤ ቀንም ውብ ብርሃኗን በእኛ ላይ አድርጋለችና ከሕይወት በኋላ የሚሆነው መጪው ጨለማ ሳይቆጣጠረን ወደምንታረምበት ጎዳና ፈጥነን እንራመድ። በዚያች ጊዜ (ከሞት በኋላ) ልንላወስ አንችልምና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በማይሞት ቃሉ እንዲህ ሲል ይጮሃል ‹የተወደደ ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው› (2ኛ ቆሮ 6፥2)

ትርጉም: ዲያቆን አቤል ካሳሁን
source:-By Elder Ephrai