2022-04-10 11:13:14
በዓዕምሮ ጤናና ህመም ዙርያ ያሉ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች እና ተገቢ የእርማት ሀሳቦች
~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ስህተት 1: የዓዕምሮ ጤና እክሎች ስርጭታቸው እጅግ አናሳ ነው
እውነታ: የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንዳመለከተው ከ አራት ሰዎች አንዱ የዓዕምሮ ጤና እክል አለበት። በሃገራችንም አስደንጋጭ ስርጭት አለው።
ስህተት 2: የዓዕምሮ ጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም
እዉነታ: ለዓዕምሮ ህመምተኞች የተለያዩ የመድሃኒትና የስነልቦና ህክምና አማራጮች አሏቸው። እነዚህንና ሌሎች የህክምና እርዳታዎች በማግኘት የዓዕምሮ ህመምተኞች ታክመው ትርፋማ የሆነና ውጤታማ ህይወት መምራት ይችላሉ። ተስፋ አላቸው።
ስህተት 3: የዓዕምሮ ህመምተኛ ለሆነ ሰው ምንም ማድረግ አልችልም።
እውነታ: በደንብ ትችላለህ! ትችያለሽ!
እንዴት? በለኝ
መጀመርያ ስለዓዕምሮ ህመም አስተሳሰብህንና የምታሳያቸውን ድርጊት ቀይር/አስተካክል
3.1 ለእርዳታ አጠገባቸው እንዳለህ አሳውቃቸው/አሳውቂያቸው
3.2 የዓዕምሮ ህክምና እንዲያገኙ በመርዳት
3.3 ስለዓዕምሮ ጤና መረጃዎችን በዙርያህ ለሚገኙ ሰዎች በማካፈል
3.4 በአክብሮትና በፍቅር በመያዝ
3.5 አብዛኛው ማህበረሰብ በመደበላቸው ስያሜ ባለመጥራት (ጠሽ ቀዌ እብድ ንክ ወፈፌ ቀውስ ንቅል መራቱ)
3.6 ሌሎች ሰዎችን እንደምታናግር በትህትናና በአክብሮት አናግራቸው
3.7 በስራ በትምህርት በቤት እንዲሁም በሌሎች የኑሮ ግንኙነት ወቅት የዓዕምሮ ህመም ያለባቸውን ሰዎች መብት አክብር እንጂ አታግልል አታዳላ።
ይሄ ከቁጥር በላይ የሆነ እርዳታ ነው!!
ስህተት 4: ህፃናት ልጆች በዓዕምሮ ህመም አይያዙም። የባህሪህ ችግር ቢያሳዩም መልካም ያልሆነ የአስተዳደግ ውጤት ነው።
እውነታ: ህፃናት ልጆች እንደ አዋቂዎች ሁሉ ለተለያዩ የዓዕምሮ ህመሞች ይጋለጣሉ። ይሄም ጥሩ ካልሆነ የአስተዳደግ ውጤት ብቻ ሳይሆን በስነልቦናዊ ማህበራዊ እና ሌሎች መንስዔዎች ጋር ይያያዛል።
ስህተት 5: የዓዕምሮ ህመም እኔን ሊይዘኝ አይችልም ብሎ ማሰብ
እውነታ: የዓዕምሮ ህመሞች በሚያስደንቅ ሁኔታ ከፍተኛ ስርጭት ያላቸው ሲሆኑ ማንም ሰው የዓዕምሮ ህመም ላለመታመም ምንም ዓይነት ዋስትና የለውም።
የዓዕምሮ ህመም ቀለም የትምህርት ደረጃ ሀብት ፆታ ዘር ሳይል የሚይዝ ህመም ነው። ነገር ግን በተቻለ አቅም በተለዬ ሁኔታ የሚያጋልጡ ነገሮችን መለየትና ለዓዕምሮ ጤና መጎልበት የሚረዱ ነገሮች ላይ ማተኮሩ ግን አማራጭ የለውም። እንደ ቀላል የሚታይ ጭንቀት ድብርት ተያያዥ የስሜት መረበሾች ሲኖሩም ወደ ባለሙያ መሄዱ ሸጋ ነው። የአልኮልና የዕፅ ሱሶች ላይ አትኩሮት ሰጥቶ መስራቱ እንዳለ ሆኖ!
ስህተት 6: የዓዕምሮ ህመም ከግለሰቡ የስብዕና/የባህሪ ድክመት የሚመጣ ነው
እውነታ: የዓዕምሮ ህመም በስነልቦናዊ ስነ-ህይወታዊ እና ማህበረሰባዊ ቀውስ/መረበሽ የሚመጣ እንደሆነና የነዚህ ድምር ውጤት ወይ በተናጥል የነበረውን የዓዕምሮ ጤና እንደሚያውኩ ጥናቶች ያሳያሉ።
ስህተት 7: ልጆች በትምህርት ቤት ወይ በቤቴ የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪህና በትምህርት ቤት የሚወድቁት ትኩረት ለመሳብ ነው።
እውነታ: የባህሪህ ችግሮች በህፃናትና በታዳጊዎች ላይ ከሚታየው የስሜት የእድገት ውስንነት እክል የባህሪህና ሌሎች የዓዕምሮ ህመሞች እንጂ ትኩረት ለመፈለግ አይደለም። እነዚህ ልጆች ተገቢውን የቤተሰብ/የመምህራን መረዳት ትኩረትና የዓዕምሮ ጤና ግልጋሎት ካገኙ ውጤታማ ልጆች ሆነው ያድጋሉ።
ስህተት 8: ለዓዕምሮ ህመም መድሃኒት ብቻ መውሰድ በቂ ነው ሌላ ህክምና አያስፈልግም።
እውነታ: ተጨማሪ የንግግርና የኤሌክትሪክ ንዝረት የሙዚቃ ህክምናዎች አሉ። ስለዚህ ባለሙያው በሚያስረዳው መሰረት የመድሃኒት ህክምናና ተጨማሪ እንደህመሙ ባለሙያው ያዘዘውን መከታተል ይመከራል።
ቃልኪዳን ዮሐንስ
የስነ-ዓዕምሮ ባለሙያ
ብሩህ ጊዜ!
https://t.me/ethiopsychiatry
1.9K views08:13