Get Mystery Box with random crypto!

የዲ/ዮርዳኖስ አበበ ትምህርቶች የሚተላለፉበት ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት: ✞ በስመ አብ | ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን

የዲ/ዮርዳኖስ አበበ ትምህርቶች የሚተላለፉበት ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት:
✞ በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን :: ✞

✞ ነሐሴ 26 ✞

+*" አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ "*+

=>እኒህ ጻድቅ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው:: "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው:: ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል::

+ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ : እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች:: በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ : ምጽዋትን ወዳጅ : ቡርክት ሴት ነበረች:: እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር::

+ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማሕጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች:: ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ 7 አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች::

+ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕጻን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ:: ይሕችን ጸሎት በሕጻን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር::

+የ5 ዓመት ሕጻን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል:: ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ:: ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል:: የፈጣሪውን ስም ያቃለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል::

+ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ት/ቤት ገብተው : መጻሕፍትንም አጥንተው መንነዋል:: በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በሁዋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም::

*ባሕር ውስጥ ሰጥመው 500 ጊዜ ይሰግዳሉ::

*በየቀኑ 4ቱን ወንጌልና 150 መዝሙረ ዳዊትን ይጸልያሉ:: (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው)

*በ40 ቀናት : ቀጥሎም በ80 ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ::

*ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው::

*በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ:: (ካህን ናቸውና)

*ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ : ክቡር ደሙን ይጠጣሉ::

*በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን : መከፋትን አላሳደሩም::

+በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር:: ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በሁዋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከተትሎ መጥቶ አላቸው::

"1.ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ:
2.ስለ ምናኔሕ:
3.ስለ ተባረከ ምንኩስናህ:
4.ስለ ንጹሕ ድንግልናህ:
5.ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ:
6.ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ:
7.ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ 7 አክሊላትን እሰጥሃለሁ::"

+"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን : 500 የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ:: በስምህ የሚለምኑ : በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ! በርእስየ!' ብዬሃለሁ" አላቸው::

+ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው:: ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ 3 ጊዜ ሳማቸው:: ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች:: በዝማሬም ወሰዷት::

=>አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን: ክብራቸውን: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን::

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

   ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞

<<< በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን :: >>>

<+> ነሐሴ 26  <+>

+*" አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ "*+

=>እግዚአብሔር በ13ኛው መቶ ክ/ዘ እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ባያስነሳ ኑሮ ምናልባትም ዛሬ የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያንን በምናያት መንገድ ላናገኛት እንችል ነበር:: እውነተኛ አባቶቻችን ፈጽሞ ከሚቆረቁራቸው ነገር አንዱ የጻድቅና ሐዋርያዊ አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መዘንጋት ነው::

+እርሳቸው ፍሬ ሃይማኖት ሆነው ከጽድቅ ፍሬአቸው አዕላፍ ቅዱሳንን ወልደው ሃገራችን በወንጌል ትምሕርትና በገዳማዊ ሕይወት እንድታሸበርቅ አድርገዋል:: እስኪ በዕለተ ዕረፍታቸው ስለ ጻድቁ ጥቂት ነገሮችን እናንሳ::

+አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ የተወለዱት ጐንደር : የድሮው ስማዳ (ዳኅና) አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ዘክርስቶስና እግዚእ ክብራ ይባላሉ:: የተወለዱት በ1210 ዓ/ም ነው:: ነገር ግን አንዳንድ ምንጮች በ1196 ዓ/ም ያደርጉታል::

+ጻድቁ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር እንደሚገባ አድገዋል:: በልጅነታቸው በብዛት ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር:: በትርፍ ጊዜአቸው ደግሞ ትምሕርተ ሃይማኖትንና ሥርዓቱን ያጠኑ ነበር:: በ1240 ዓ/ም ግን (ማለትም 30 ዓመት ሲሞላቸው) ይሕቺን ዓለም ይተዋት ዘንድ አሰቡ::

+አስበውም አልቀሩ ፈጣሪን እየለመኑ ደብረ ዳሕሞ ገቡ:: በወቅቱ ዳሞ የትምሕርት : የምናኔ ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር የአቡነ አረጋዊ 5ኛ የቆብ ልጅ ካልዕ ዮሐኒ ነበሩና የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ሆኑ::

+አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በደብረ ዳሞ በነበራቸው ቆይታ ቀን ቀን ሲታዘዙ : ሲፈጩ : ውሃ ሲቀዱ ውለው ሌሊት እኩሉን በጸሎት በስግደትና የቀረውን ሰዓት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ አሳለፉ::

+በመጨረሻም ልብሰ ምንኩስናን ለበሱ:: ይህን ጊዜ 37 ዓመታቸው ሲሆን ዘመኑም 1247 ዓ/ም ነው:: ወዲያውም በዳሞ ሳሉ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ወደ ወሎ ሐይቅ ሒድ : ብዙ የምትሠራው አለና" አላቸው::

+በአንዴም ከዳሞ (ትግራይ) ነጥቆ ሐይቅ እስጢፋኖስ (ወሎ) አደረሳቸው:: በዚያም ለ7 ዓመታት በዼጥሮስ ወዻውሎስ ቤተ መቅደስ በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌል : በማዕጠንትና ሐይቁ ውስጥ ሰጥሞ በመጸለይ ኖሩ::

+ቅድስናቸውን የተመለከቱ አበውም በግድ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው:: ይህ ነው እንግዲህ በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ መሠረት የተጣለበት አጋጣሚ:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+ስም አጠራሯ የከፋ ዮዲት ጉዲት ለ40 ዓመታት ሃገሪቱን እንዳልነበረች ብታደርጋት ክርስትና ተዳከመ:: ባዕድ አምልኮም ነገሠ:: አቡነ ኢየሱስ ሞዐ (ትርጉሙ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸነፈ ማለት ነው) ደግሞ ሃይማኖታቸው የቀና ከ800 በላይ ክርስቲያኖችን ሰበሰቡ::

+በሃገሪቱ ትልቅና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ቤተ መጻሕፍት አደራጁ:: እነዚያን አርድእት በቅድስናና በትምሕርት አብስለው አመነኮሱና "ሒዱ! ሃገሪቱን ታበሩ ዘንድ ተጋደሉ" ብለው አሰናበቷቸው::

+ክእነዚህ መካከልም ታላላቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን: አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እና የሁዋላውን ፍሬ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን መጥቀስ እንችላለን:: በዚህም ምክንያት ጻድቁ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን - አእላፍ ቅዱሳንን የወለደ" ሲባሉ ይኖራሉ::