Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለእናታችን ብጽዕት ሣራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† | ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን

††† እንኳን ለእናታችን ብጽዕት ሣራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅድስት ሣራ ብጽዕት †††

††† አበው እናታችን ሣራን " #ቡርክተ_ማሕጸን" ይሏታል:: (የቅዱሱ ዘር የይስሐቅ እናት ናትና) በዚያውም ላይ የደጉ ሰው የአብርሃም ሚስት ናት:: ልክ በዓለም ታሪክ "ከጠንካራና ስኬታማ ወንዶች ጀርባ ጠንካራ ሴቶች አሉ" እንደሚባለው ከአብርሃም አባታችን ስኬታማ የቅድስና ሕይወት ጀርባ ብጽዕት ሣራ አለች::

ለአብርሃም አባታችን መጽሐፍ የተናገረው ክብር ሁሉ ለቅድስት ሣራ ይገባታል:: አንድም ገንዘቧ ነው:: ቅድስቷ እናት ደጉ አብርሃምን ያገባችው ገና በከላውዴዎን (በ2ቱ ወንዞች መካከል) ሳለ ነው:: ገና ከልጅነቷ ጀምራ አብርሃምን "ጌታየ" እያለች ታገለግለው እንደ ነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል:: (1ዼጥ. 3:5)

በዚህም ከብራበታለች: ገናበታለች እንጂ አልተጐዳችበትም:: አብርሃም ወደ ካራን ሲወጣ "ለምን?" አላላችም:: እንዲሁ ለፈቃደ እግዚአብሔር ታዘዘች እንጂ:: በካራን ታራን ቀብረው: በፈጣሪ ትዕዛዝ ወደ #ከነዓን ሲፈልሱም ቅድስት ሣራ አልተቃወመችም::

ለፈጣሪዋ ትዕዛዝና ለባሏ ስትል ርስቷን: ሃገሯን: ዘመዶቿን ሁሉ ትታ ሔዳለች:: ይሔውም በጐ ምናኔ ነው:: እናታችን ሳራ በከነዓን የተመቸ ነገር አልገጠማትም:: ከአንዴም ሁለቴ በረሃብና በድርቅ ምክንያት ወደ ግብጽ እና #ጌራራ ተሰደዋል::

በዚያም ፈርዖን "እነካለሁ" ቢል እግዚአብሔር ተቆጥቶ: ፈርኦንንና ግብጽን በደዌ መታ:: በዚህም ክብረ ሣራን ተመለከትን:: ከስደት መልስም በኬብሮን (በተመሳቀለ መንገድ ላይ) ድንኩዋን ሠርተው የወጣ የወረደውን ሲያበሉ: እንግዳ ሲቀበሉ ኑረዋል::
(ልብ በሉልኝ ይህን ትጋትና ደግነት ያሳየችውን ቅድስት ሣራን ልናከብራት ይገባል)

እድሜ ዘመኗን ያሳለፈችው እንግዳ በመቀበል: እግዚአብሔርን በማምለክ ነው:: ምንም እንኩዋ ማሕጸኗ ለጊዜው ቢዘጋ ተስፋ አልቆረጠችም:: ለአብርሃምም ከአጋር እንዲወልድ ፈቃድ ሰጥታለች::

ዕድሜዋ 89 ዓመት በሆነ ጊዜ ሰይጣን እንግዳ እንዳይመጣ ለ3 ቀናት ቢያስቀርባቸው እንደ ባሏ እርሷም 3 ቀናትን ያለ ምግብ አሣልፋለች:: በ3ኛው ቀን ሥላሴን በቤቷ አስተናግዳለች:: ስለ ክብሯም ከ3 መሥፈሪያ ዱቄት ለውሳ ያዘጋጀችውን እንጐቻ ሥላሴ በልተውላታል:: (ምንም ሥላሴ ምግብን ባይመገቡም)

የሥላሴ በዚያች ድንኩዋን ውስጥ መስተናገድ ታላቅ ምሥጢር አለው:: ከግብዣው በሁዋላም እግዚአብሔር አለ:- "አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ . . . እንዲሁ ከርሞ እመለሳለሁ: ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች" አለው::

ያን ጊዜ ሣራ በውሳጤ ሐይመት (በድኩዋኑ ውስጥ) ሆና ሰምታ ሣቀች:: ለምን ሳቀች ቢሉ:- እጅግ ደስ ቢላት! አንድም ቢገርማት:: ይሕስ በምን ይታወቃል ቢሉ:- ልጇ " #ይስሐቅ" የተባለው "ለእናቱ ሣቅን: ደስታን ያመጣ" ለማለት ነውና::

ሥላሴም:- "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ: እንዘ ትብል ዓዲየኑ እስከ ይእዜ: ወእግዚእየኑ ልሕቀ: ቦኑ ነገር ዘይሰዓኖ ለእግዚአብሔር - ሣራን ምን አሳቃት? ለእግዚአብሔርስ የሚሳነው ነገር አለን" ብለዋል::

ቅድስት ሣራ በ90 ዓመቷ ይስሐቅን ወልዳ በቀሪ ዘመኖቿ በደስታ ኑራለች:: በዚህች ቀንም በመልካም ሽምግልና ዐርፋ: አባታችን #አብርሃም ከታላቅ ሐዘን ጋር ቀብሯታል:: ሐዋርያው #ቅዱስ_ዻውሎስ ብጽዕት ሣራን በበጐ ምሳሌ መስሏታል:: (ዕብ. 11:11)

††† ቅዱሳን ሞይስስና ሣራ †††

††† እነዚህ ቅዱሳን ግብጻውያን የአንድ እናት: የአንድ አባት ልጆች ሲሆኑ የነበሩትም በዘመነ ሰማዕታት ነው:: ከወላጆቻቸው ጋር በሥርዓተ ክርስትና አድገው ዕድሜአቸው ለአካለ መጠን ሲደርስ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው::

ያን ጊዜ #ቅዱስ_ሞይስስ እህቱን ቅድስት ሣራን ጠርቶ "እህቴ! እኔ ወደ ገዳም መሔዴ ስለሆነ አንቺ ባል አግብተሽ: ሃብት ንብረቱን ወርሰሽ ኑሪ" አላት:: #ቅድስት_ሣራ ግን መልሳ "እንዴት እኔን በዚህ ዓለም ወጥመድ ውስጥ ትተወኛለህ? ሁለታችንም ከአንድ ማሕጸን ነን:: ስለዚህ ላንተ የምትፈልገው ሁሉ ለእኔም ያስፈልገኛልና እኔም መናኝ ነኝ" አለችው::

ቅዱስ ሞይስስ የልቡናዋን መጨከን ሲያይ ነዳያንን ሰበሰበ:: ገንዘቡን: ቤቱን: ሃብቱንና ንብረቱን ሁሉ በየስልቱ ለነዳያን አካፈለ:: ሳይዘገይም እህቱን ይዞ ወደ በርሃ ተጉዋዘ:: እርሷን ከደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ከወንዶች ገዳም ውስጥ መነኮሰ::

ለ10 ዓመታት ሁለቱም ለፈጣሪያቸው በጾምና በጸሎት: ከስግደት ጋር ሲገዙ: ለአባቶችና እናቶች ደግሞ በትሕትና ሲታዘዙ ኖሩ:: በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አንድም ቀን ተገናኝተው አያውቁም ነበር:: አንዱ ለሌላኛው ተግቶ መጸለይን ግን ቸል አላሉም::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ) ነውና መከራው እየገፋ ሲመጣ ቅዱስ ሞይስስ አንድ ነገር አሰበ:: በክርስቶስ ስም ደሙን ለማፍሰስም ወሰነ:: ወደ ከተማ ከመውጣቱ በፊት ግን ለቅድስት ሣራ መልዕክት ላከባት:: "እኔ ወደ ምስክርነት እየሔድኩ ስለሆነ ቸር ሁኚ" የሚል ነበር መልእክቱ::

እርሱ ይህንን ብሎ ወደ ከተማ ሲሔድ ግን መንገድ ላይ እህቱን አገኛት:: ገርሞት የፍቅር ሰላምታን ከተለዋወጡ በሁዋላ "እንዴት መጣሽ?" ቢላት "ወንድሜ! ቀድሞም ነግሬሃለሁ:: ላንተ የምትፈልገው የድኅነት መንገድ ሁሉ ለእኔም ያስፈልገኛል" አለችው::

ሁለቱም ተያይዘው ወደ መከራ አደባባይ ደረሱ:: በዚያም ስመ ክርስቶስን ሰብከው: ብዙ መከራንም ተቀብለው በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነዋል::

††† አምላከ ቅድስት ሣራ ደግነቷን: መታዘዟን ያሳድርብን:: ከበረከቷ: ከሌሎችም ቅዱሳን በረከትን ይክፈለን::

††† ነሐሴ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ብጽዕት ሣራ (የአብርሃም ሚስት)
2.ቅዱሳን አባ ሞይስስና እህቱ ሣራ (ሰማዕታት)
3.ቅዱሳን አጋቦስና ቴክላ (ሰማዕታት)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና:: እንዲሁም #ሣራ_ለአብርሃም:- #ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት:: እናንተም ከሚያስደግጥ ነገር አንዳች እንኩዋ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆቿ ናችሁ::" †††
(1ዼጥ. 3:5)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††