Get Mystery Box with random crypto!

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ሲታወሱ. | የዲያሪ ላይ ጥቅሶች ❤️💋💋(1)

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ሲታወሱ......

#ታሪክን_ወደኋላ

የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ የተለየ ቀን ነው፡፡ የኢጣሊያዋ ኔፕልስ ግዛት ልዑል ልጅ መውለዱን ለመዘከር ግራዚያኒ በዚህ ቀን የአዲስ አበባን ደሃዎች ሰብስቦ ለመመጽወት ባደረገው ጥሪ መሰረት ከ 3ሺ የሚበልጡ አቅመ ደካሞች በጥዋቱ በ 6 ኪሎው ቤተመንግስት ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለው መረጃ እስከ ሮም በመሰማቱ የቤተመንግስቱ ውስጥና ዙሪያ መትረየስ በታጠቁ ልዩ ወታደሮች እንዲጠበቅ ተደርጓል፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ይህንን ጠንካራ ጥበቃ አልፈው ውስጥ ገብተዋል፡፡

ከቀኑ ለ6 ሩብ ጉዳይ አካባቢ ሲሆን ከፍተኛ ፍንዳታ በቤተመንግስቱ ተሰማ፡፡ ከፍ ወዳለው የቤተመንግስቱ ደረጃ የተወረወረው ቦምብ ደግሞ ግቢውን በጩሀት አናጋው፡፡ የመጀመሪያው ቦምብ ባለመትረየስ ጠባቂውን አስወገደው፡፡ 2ኛው ቦምብ ከግራዚያኒ አጠገብ የነበረውን ምሰሶ አፈራረሰው፡፡ ግራዚያኒ ወደ ውስጥ ሲሸሽ ጀርባው፣ ትከሻውና የቀኝ እግሩን ከ350 በሚበልጥ የቦምብ ፍንጣሪ ቆሰለ፡፡ የካሜራ ባለሙያውና ወታደሮች ግራዚያኒን ከወደቀበት አንስተው በመኪና በመጫን ወደ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡

3 ኛው ቦምብ ፖጊያሊ ፊት በመውደቅ ፍንጣሪው አቡነ ቄርሎስን ሲያቆስላቸው ጃንጥላ ያዣቸውን ደግሞ ገደለው፡፡ የኢጣሊያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ሊዮታ በቦምብ እግሩን አጣ፡፡ የፋሺስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊና የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች በድንጋጤ ለምጽዋት በ6 ኪሎ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ እሩምታ በመተኮስ ከ1ሺ የሚበልጡትን ገደሉ፡፡ የጥቃቱ ዋና ፈጻሚዎች ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ከጊቢው በመውጣት ተሰወሩ፡፡

በቀጣይ ሰአታት ጥቁር ከነቴራ ለባሽ የኢጣሊያ ልዩ ወታደሮች የቴሌፎንና የፖስታ አገልግሎትን ዘጉ፡፡ ወዲያው መሃል ፒያሳ አራዳ ባለው የፋሽስት ዋና ጽ/ቤት የነበረው ጎዶ ኮርቴሌ የፋሽስት ወታደሮች ለሚቀጥሉት 3 ቀናት ኢትዮጵያውያንን እንዲጨፈጭፉ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚሁ ምሽት አዲስ አበባ የእርድ ቄራ ሆነች፡፡ ነዋሪዎቿ ቤት ከውጭ እየተቆለፈባቸው ከውጭ በሚለኮስ እሳት እንዲነዱ ተደረገ፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተገኙት ደግሞ እየታፈሱ በመኪና ተጭነው ተወስደው በግራዚያኒ ዋና መምሪያ ተረሸኑ፡፡ ከሚነዱት ቤቶች አምልጦ ለመውጣት እድል ያገኘውን ደግሞ የኢጣሊያ ወታደሮች ከደጅ ሆነው በጥይት ለቀሙት፡፡

የጥቃቱ አቀናባሪዎችንና አድራሾችን ለመያዝ ጥብቅ ምርመራና አሰሳ ተጀመረ፡፡ የኢጣሊያ ደህንነቶች ከምሽቱ በ2 ሰአት የአብረሃ ደቦጭን ቤት ሰብረው ሲገቡም እጀታው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ በሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት በተቀባ ሳንጃ የኢጣሊያ ባንዲራ ተቦጫጭቆ አገኙ፡፡ በመቀጠል የሞገስና የአብርሃ ጓደኞችን ማደን ተጀመረ፡፡ አብርሃና ሞገስ ከምሽቱ 1 ሰአት አካባቢ ወደ ጀርመን ሚሽን በመሄድ ጓደኛቸው ስብሀትን በአጥር ቢያስጠሩትም ስብሀት አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁ ስላልነበር ብቻቸውን ከተማውን ለቀው ሸሹ፡፡ ከጥቂት ሰአታት በኋላ የኢጣሊያ ወታደሮች የጀርመንን ሚሽን በመክበብ ስብሀትን እያዳፉ ወሰዱት፡፡ አርበኛ ሸዋ ረገድ ገድሌንም በማታ ወስደው በኤሌክትሪክ ንዝረት ቢያሰቃይዋትም ሚስጥር ሳታወጣ ቀረች፡፡

ቅዳሜ ጥዋት በድንጋጤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሲሯሯጡ የተገኙ ነዋሪችም ታፍሰው ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አጠገብ ተረሸኑ፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ተሸሽገው የነበሩ በ100ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ኤምባሲው አሳልፎ እንደሰጣቸው ኤምባሲው በር ላይ እንደ ውሻ እየተቀጠቀጡ ተገደሉ፡፡ ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር እና ኢትዮጵያ የሚገኘው አምባሳደር ዜናውን በማግስቱ አስተባበሉ፡፡ ምኒልክ አደባባይ አቅራቢያ ሆኖ ይህንን ግፍ ይመለከት የነበረው ወጣቱ ልጅ እምሩ ዘለቀም ከሰአታት በኋላ ቤቱን ሰብረው በገቡ የኢጣሊያ ወታደሮች ከእናቱና 2 እህቶቹ ጋር ተይዞ ታሰረ፡፡

እሁድ እለት የ3 ቀኑን ጭፍጨፋ ለማስቆም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የሚከተለው አዋጅ ተለጠፈ፣

“ሞሶሎኒ እንደ ፈጣሪ ሃያል ነው፡፡ ፈጣሪም ሆነ ሞሶሎኒ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ ሞሶሎኒ ተበሳጭቶባችሁ ነበር፡፡ አሁን ግን ቁጣው በርዷል፡፡ ወደ የቤታችሁ በመሄድ እለታዊ ተግባራችሁን ቀጥሉ፡፡”

ይሁን እንጂ ከዚህ አዋጅ በኋላም ግድያው ቀጥሎ ነበር፡፡ የበቀል ቅጣቱን ለማምለጥ ከቤታቸው ከወጡት ወደ 5ሺ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ ብዙዎቹ የአርበኞችን ትግል ተቀላቀሉ፡፡ በሁለት ቀን ተኩል በኢጣሊያ የግፍ ጭፍጨፋ የተገደሉትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር አንዳንድ ወገኖች እስከ 30ሺ እንደሚደርስ ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን ከ17ሺ-18ሺ ያደርሱታል፡፡

የአርበኞች ጀብዱ፣ Jeff Pearce እንደጻፈው፣ ኤፍሬም አበበ እንደተረጎመው፣ ገጽ 205-212

➻ ከታች የተቀመጡት ምስሎች በዕለቱ በህዝቡና በከተማዋ ላይ የተከናወኑት ፎቶዎች ናቸው።

ክብና ዘላለማዊ ዕረፍት ለሰማዕታት


ምንጭ ፦ ከታሪክን ወደኋላየfacebook page(ገፅ)

ላይክ እና ሼር በማድረግ ለወዳጅ ዘመዶቻችሁ አድርሱ