Get Mystery Box with random crypto!

በኢትዮጵያ አሁን ያለው አሰራር ከቀጠለ፤ ሁሉም የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ | ልዩ መረጃ ®

በኢትዮጵያ አሁን ያለው አሰራር ከቀጠለ፤ ሁሉም የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ 20 ዓመት ያስፈልጋል ተባለ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁን ባለው አሰራር የሚቀጥል ከሆነ፤ ሁሉም የገጠር ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ 20 ዓመት እንደሚፈጅበት ገለጸ። መንግስታዊው ተቋም በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለመተግበር የያዘውን ስትራቴጂክ እቅድ ለማስፈጸም ከሚያስፈልገው 2.76 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን በ“ጉድለት” (deficit) የተመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኘው ይህ የልማት ድርጅት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በጅምላ ገዝቶ ለደንበኞች የመሸጥ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው። ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ መስመሮችንም ያስተዳድራል። ይህ  መንግስታዊ ድርጅት ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ እየተገበረው በሚገኘው ስትራቴጂክ እቅድ፤ የኤሌክትሪክ ስርጭት መሰረተ ልማት ሽፋንን ለመጨመር፣ ያረጁ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን እና የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ ወጥኗል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በስትራቴጂክ እቅዱ የመጨረሻ ዓመት በሆነው በ2017፤ የደንበኞቹን ቁጥር አሁን ካለበት 4.5 ሚሊዮን ወደ 7.9 ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዱንም አስታውቋል። ተቋሙ ይህን ያስታወቀው፤ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ የካቲት 27፤ 2015  ከ“ቁልፍ ደንበኞች” ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያለበት የፋይናንስ ውስንነት፤ በ2022 ዓ.ም በሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ጥያቄ ውስጥ እንደከተተውም በዛሬው ውይይት ላይ ተነስቷል። ባለፉት 12 ዓመታት በአማካይ 423 ከተሞች በየዓመቱ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ መደረጉን የጠቀሱት የተቋሙ የለውጥ እና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው፤ በዚህ አካሄድ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ኤሌክትሪክ ለማዳረስ 20 ዓመት እንደሚፈጅ ተናግረዋል። 

via Ethiopiainsider