Get Mystery Box with random crypto!

የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ቆቦ ወረዳ ኦፕሬሽን መጀመሩ ተገለጸ ማምሻውን ጀምሮ መከላከያ | LEYU NEWS

የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ቆቦ ወረዳ ኦፕሬሽን መጀመሩ ተገለጸ

ማምሻውን ጀምሮ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ በነዋሪዎች ላይ የቤት ለቤት ፍተሻ እያደረገ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከሥፍራው ነዋሪዎች አረጋግጣለች፡፡

<<የአማራ ክልል ብልፅግና ጽሕት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላን የገደላችሁት እናንተ ናችሁ።>> በማለት ፋኖዎች እየተሳደዱ እና ቤተሰቦቻቸውም እየታሰሩ መሆኑን ነው ነዋሪዎች የገለጹት፡፡

በዚህም፤ ከአርብ ዕለት ጀምሮ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ ከቆቦ ወደ አላማጣም ይሁን ወደ ወልድያ ለመሄድ መንገድ ተዘግቶ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች፤ ከቀናት በፊት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በሽምግልና ታርቀው ወደማህበረሰቡ የተቀላቀሉ የፋኖ አባላትም እየተሳደዱ ነው ብለዋል፡፡

ከአስር በላይ የፋኖ አባላት ቤተሰቦች ለእስር እንደተዳረጉም ጠቅሰው፣ ሌሊት በሚደረገው የቤት ለቤት ፍተሻ በተለይ ሴቶች እየተሳቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል።

<<ሰውዬው የተገደሉት ሰሜን ሸዋ ሆኖ ሳለ ገዳዮቹ ቆቦ ውስጥ ናቸው ብሎ ማህበረሰቡን ሰላም መንሳት ተገቢ አይደለም።>> ያሉት ነዋሪዎቹ እየተደረገ ያለው ነገር ህዝብን ለአመጽ ከማነሳሳት ውጭ ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡

<<እንደ ሸኔ ያሉ ታጣቂ ኃይሎች ዜጎችን ከቀያቸው እያፈናቀሉ እና መንገድ ላይ እያገቱ ብዙ ጥፋት የሚያደርሱ ኃይሎችን ችላ በማለት፤ ምንም ባልተፈጠረበት ቆቦ ላይ ይህን ሁሉ ግርግር መፍጠር የመንግሥት አካሄድ ፍትሃዊነት የጎደለው አገዛዝ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ነው።>> ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በዚህ ወቅት ተዘግተው የነበሩ መንገዶች ተከፍተው መደበኛ እንቅስቃሴ የቀጠለ ቢሆንም ማህበረሰቡ አሁንም መደናገጥና ስጋት ላይ ነው ተብሏል።

ከአማራ ክልል ብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ መገደል በኋላ፤ የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር በሚጥሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰድኩኝ ነው ሲል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ግብረ ኃይሉ ‹‹ፅንፈኛ ኃይሎች›› ብሎ የሚጠራቸው አካላት የአማራ ሕዝብ የልማትና የሰላም ተጠቃሚ እንዳይሆንና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው እንዲሁም በመንግሥት የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዳይተገበሩ እንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸን ነው የገለጸው፡፡

ይሁን እንጂ በተለይ ግብረ ኃይሉ በክልሉ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ካሳወቀ በኋላ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ግራ መጋባት መፈጠሩን አዲስ ማለዳ ተገንዝባለች፡፡

ብዙዎች <<ምን እየተካሄደ ነው>> የሚል ጥያቄ እያነሱ ሲሆን፤ ጽንፈኛ ተብለው የሚጠሩ አካላትም እነማን እንደሆኑ መንግሥት በግልጽ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል፡፡ 

መንግሥት ሰበብ ፈልጎ የፋኖ አባላትን ለመምታት እንዲሁም ክልሉን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ የታሰበ ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ነው የሚሉም በርካታ ቅሬታዎች እየተነሱ ይገኛል፡፡(አዲስ ማለዳ)

@Leyu_News
@Leyu_News