Get Mystery Box with random crypto!

የስዊድን ፣ ኖርዌይ ፣ ኬንያ ፣ አውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በመንግስት እና በኦሮሞ | LEYU NEWS

የስዊድን ፣ ኖርዌይ ፣ ኬንያ ፣ አውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በመንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በሚደረገዉ ድርድር እንደሚገኙ ተሰማ

ቢቢሲ አማርኛ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት ምንጮቼ እነገሩኝ እንዳለዉ ፤ መንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር በሚደረገው ንግግር የስዊድን፣ የኖርዌይ፣ የኬንያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እንደሚገኙ ዘግቧል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እነዚህ ምንጮች የተጠቀሷቸው አገራት በድርድሩ ይገኛሉ ይበሉ እንጂ የትኞቹ አገራት ምን ሚና ይኖራቸዋል፤ በዋናነት የማደራደር ኃላፊነትን የሚወስደው የትኛው አካል ነው የሚለው አልተለየም ብለዋል ሲል አክሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ መሮ ዲሪባም የሚመሩት ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚያደራድር ሦስተኛ አካል መኖሩን ያረጋግጡ ሲሆን፣ አደራዳሪዎቹ እነማን እንደሆኑ በስም ከጥቀስ ተቆጥበዋል።

መሮ ዲሪባ ታጣቂ ቡድኑን ወክለው ከመንግሥት ጋር የሚደራደሩ የልዑክ ቡድን አባላት በትናንትናዉ እለት ወደ ታንዛኒያ ጉዞ እያደረጉ ስለመሆኑም ጨምረው ተናግረዋል።

የሠራዊቱ ዋና አዛዥ መሮ ዲሪባ ይህ ንግግር በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ዛንዚባር ደሴት ላይ እንደሚከናወን ገልጸው፤ “የጥይት ድምጽ ሳይሰማ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መልስ የሚያገኝ ከሆነ በራችን ሁሌም ክፍት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

መሮ እንደሚሉት “በቅርቡ” የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና መንግሥት ሦስተኛ ወገን ባለበት በኬንያ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው የታጣቂ ቡድኑ ተወካዮች በቦታው ቢገኙም የመንግሥት ተወካዮች ግን ሳይገኙ ቀርተዋል ማለታቸዉን ዳጉ ጆርናል ከዘገባው ተመልክቷል።
“በሌሎች አገራት ግብዣ በኬንያ ለመገናኘት ቀጠሮ ነበር። ነገር ግን መንግሥት ሳይገኝ ቀረ” ያሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ድርድር ስኬት ላይ ጥርጣሬዎች ቢኖሯቸውም የንግግር ሂደቱ ሰላም ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጨምረው ተናግረዋል።

“ንግግር መጀመሩ ጥሩ ነው። መነጋገር እና መፍታት ያለብን ብዙ ነገሮች ስላሉ ጉዳዩ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይሆንም” ብለዋል ሲል ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

@Leyu_News
@Leyu_News