Get Mystery Box with random crypto!

የፌደራል መንግስት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ መላክ ሊጀምር ነው የፌ | LEYU NEWS

የፌደራል መንግስት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ መላክ ሊጀምር ነው

የፌደራል መንግስት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ መልቀቅ እንደሚጀምር የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ። ለክልሉ የሚለቀቀው በጀት፤ ለሌሎች ክልሎች እንደሚደረገው ሁሉ በወራት ተከፋፍሎ የሚላክ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ይህን የተናገሩት፤ ለመንግስት ቅርበት ካለው ፋና ቴሌቪዥን ጋር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ነው። የፌደራል መንግስት ለትግራይ በጀት ለማስተላለፍ ከስምምነት ላይ መድረሱን በተመለከተ አቶ ጌታቸው ረዳ ከቀናት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የሰጡትን ቃል፤ ሚኒስትር ዲኤታው ትላንት አርብ መጋቢት 22፤ 2015 ምሽት በተሰራጨው ቃለ ምልልሳቸው አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት አቶ ጌታቸው፤ የፌደራል መንግስት በጀት መፍቀዱን፤ ሆኖም የገንዘብ መጠኑን በተመለከተ ግን “ገና እንነጋገራለን” ማለታቸው ይታወሳል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው በበኩላቸው፤ የትግራይ ክልል በጀት “የሚታወቅ” መሆኑን ገልጸዋል። የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እስኪቋቋም የበጀት ድጎማ ሳይለቅቅ ቢቆይም፤ በክልሉ ውስጥ ያሉ የፌደራል ተቋማትን ግን አስቀድሞ “ወደ ስራ ማስገባቱን” ዶ/ር እዮብ ተናግረዋል። ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሱት የመብራት እና የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ነው።
@Leyu_News
  @Leyu_News