Get Mystery Box with random crypto!

ሽመላዊ ትምህርት ሽመላ በመባል የሚታወቁት አዋፋት ወቅትን መሰረት ያደረግ ምቹ መኖሪያ | 𝐔𝐁𝐔𝐍𝐓𝐔 𝐄𝐓𝐇𝐈𝐎𝐏𝐈𝐀𝐍𝐒

ሽመላዊ ትምህርት

ሽመላ በመባል የሚታወቁት አዋፋት ወቅትን መሰረት ያደረግ ምቹ መኖሪያ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ዝውውር ያደርጋሉ፡ በጉዟቸውም ልብ ብለን አስተውለናቸው እንደሆነ የ “V” ፊደልን ቅርጽ ሰርተው ነው የሚበሩት፡፡ ከተፈጥሮ ለመማር ንቁ የሆነ ለምን ይህንን አይነት ቅርጽ ሰርተው መብረርን መረጡ የሚለውን መጠየቅ ይችላል፡፡ ሳይንስ የደረሰበት እውነታ ሽመላዎች በአንድነት ሲበሩ የሚኖረውን የአየር ግፍት ለብቻቸው ሲበሩ ከሚፈጥርባቸው የአየር ግፊት በእጅጉ ስለሚቀንስ ነው፡፡ ብቻ ለብቻ ከሚበሩት ይልቅ የ “V” ፊደልን ቅርጽ ሰርተው በአንድነት ሁነው ሲበሩ የመብረር ፍጥነታቸውም በ71% ይጨምራል፡፡ ይህንን በመረዳታቸው ነው ሽመላዎች የ “V” ፊደልን ቅርጽ ሰርተው መብረራቸው፡፡

ሌላው ሊደንቀን የሚገባው ባሕሪያቸው በሆነ ምክንያት (በጉዳትም ሊሆንይችላል) አንድ ሽመላ ተነጥሎ ከዚህ ቅርጽ ከወጣ የተወሰኑት ተነጥለው በመቅረት በግራና በቀኝ በመሆን የሚደርስበትን የአየሩን ግፊት በማገዝ ወደ መንጋው እንዲቀላቀል ያግዙታል እንጅ ጥለውት አይሄዱም፡፡ እገዛቸውም የሚዘልቀው አገግሞ ከመንጋው እስኪቀላቀል ድረስ ወይም ደግሞ ለይቶለት እስኪሞት ድረስ የሚቀይ ነው፡፡

ሽመላዎች የሚያደርጉትን እረዥም ጉዞ ይመራ የነበረው ሽመላ በደከመው ጊዜ የመሪነት ሚናውን ለአንደኛው ያስረክብና ከኋላ በመሆን እረፍት ያደርጋል፡ ሽመላዎች በሚጓዙበት ወቅት ቋቅቋቅ የሚል ድምፅ ያስተጋባሉ፡፡ ይህም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል እንደሚደረገው የደቦ ሥራ ሽለላ ጎዞውን ተበረታታው በነቃ መንፈስ እንዲጓዙት ለማድረግ የማነቃቂያ ስራ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ፊት ሆኖ መንጋውን ለሚመራው፡፡

ግብረገባዊ ትምህርት

ተፈጥሮ በራሷ ይንን ይረዱት ዘንድ ለሽመላዎች ጥበብ ሰጣቸዋለች፡፡ እኛም ከእነሱ ተምረን በአንድነት መስራት የሚያስገኘውን ጥቅም፣ በጋራ ሲሆኑ የሚፈጠረውን ተጨማሪ ጉልበት ማጤንና አንድነትን ማጠንከር እንዳለብን ያሳስበናል፡፡ አንድነት ኃይል ነው፡፡ በአንድነት በመሆናችን ለየብቻ ከነበረን የበለጠ ተደማሪ ኃይል ማግኘት እንችላለን፡፡

ትምህርት አንድ፡

የጋራ መዳረሻን በእምነት ከያዝንና እንደ አንድ ልብ መካሪ ሁነን በአንድነት መስራት ከቻልን በፍጥነት ከአሰብንበት እንደርሳለን፡፡ የላቀ ውጤትም እናስመዘግባለን፡፡

ትምህርት ሁለት፡

የመሪነት ሚናን ለመጋራት በመካከላችን መከባበርና መተማመን ሊኖር ይገባል፡፡ ሥራዎችንና ችግሮችን ስንጋራ ያለንን ብቃት በአንድነት አስተባብረን ስንጠቀምበት በአጭር ጊዜና በትንሽ ጥረት ብዙ ውጤት ማስመዝገብ አንችላለን፡ የመሪነት ቦታ ዕርስት አደለም!

ትምህርት ሦስት፡

ወቅቱን የጠበቀ ማበረታቻ ስንለዋወጥ እርምጃችን ፈጣን ይሆናል፡፡

ትምህርት አራት፡

ልዩነታችንን አድንቀን ተቀብለን ለጋራ ችግራችን በጋራ እንነሳ በተለይም ደግሞ በአስቸጋሪና በፈታኝ ጊዜ አንድነታችንን እንጠብቅ፣ እናጥብቅ፡፡

ሲጠቃለል በመሪነት ቦታ መቀመጥ ርስት መውረስ አይደለም

ምንጭ: FLIGHT OF SWANS

https://t.me/kingnan