Get Mystery Box with random crypto!

ፀሎቴን ባሰማ ፥ እንደሰው ዝም አለኝ እሱንም ዘመቻ ፥ ወሰዱት መሰለኝ ....... የእቴሜቴ ጀምበ | ቅንጭብጭብ

ፀሎቴን ባሰማ ፥ እንደሰው ዝም አለኝ
እሱንም ዘመቻ ፥ ወሰዱት መሰለኝ
.......
የእቴሜቴ ጀምበር
ሲራክ ወንድሙ
.
እረኛ አይዘምርም ፥ ዝም ነው አድባሩ
ፋኖስ ክሩን አጥቷል ፥ መሸ ደህና እደሩ
ቡሬ መንደር ራቃት ፥ የለችም ከቤቷ
በሌት አልዘመረች ፥ ከፍቷታል ወፊቷ
ማልዶ ሌት ሚያነቃኝ ፥ ዶሮ በጉድ ወጣ
የሌት ድምፁን ሸጦ ፥ መውዜር ይዞ መጣ
ወዲያም ወደ ሰማይ
ከጎጆዬ በላይ
ፀሎቴን ባሰማ እንደሰው ዝም አለኝ
እሱንም ዘመቻ ወሰዱት መሰለኝ
.
የዛች የእዝነት አርማ ፥ የህዋ ላይ ሰንደቅ
እንዴት ቀን ከፍቶባት ፥ ውብ ጀምበሯ ትጥለቅ
ከዛች ከገራገር ፥ ከደጊቱ ዳሴ
እንደምን ብርቅ ይሁን ፥ ሰላም ለእለት ጉርሴ
ኧረ እንደምን በምን
ኧረ እንደምን በምን
አምነን ያነገስነው ብራ ቀን ይዳምን
እኔን አፈር ይብላኝ ፥ ለእኔ ቀኑ ይክፋ
አንቺን ያሳጣችሽ ፥ ያች አለም ትደፋ
እስከ መች አስከ መች ፥ የአረር ሙዳይ ቋጥረን
እንደጃኖ ኩታ ፥ ዝናር ጥለት አርገን
ሀገር እያጠፋን ፥ ያልፋል እንላለን ?
እንዴት ነው መሰንበት ?
መውዜር እንደነዶ በሚመዘዝበት?
ኧረ እንደምን በምን
ኧረ እንደምን በምን
አምነን ያነገስነው ብራ ቀን ይዳምን?
.
ከጩኸትሽ ማዶ ፥ ካኮረፈው ሰማይ
ቄራ ከመሰለው ፥ ከአድማስሽ ሸራ ላይ
እብሪት ያጠላበት ፥ ምስል ድንገት ካየው
ለቸር አንመስለኝም ፥ ያን ጊዜ ፈራለሁ
አርብ አርቡን አመሻሽ
የሰማዩ ገላ ሲመስል የደም ሻሽ
ንትብ የለበሰ
ከወደ አንገቱ ዘሞ የተዘለሰ
ይሁዳሽን ባላይ ፥ ወድቆ ሲያንሰራራ
መስቀል ሆኗል ለሻጭ ፥ ገዢ ራሱን ያኩራ
ከክርስቶስ ይልቅ ፥ ይሁዳ ነውና ሚረከብ መከራ
ምክኒያቱም ......
ዘመን እያሰፉ
ትውልድ ለሚነቅፉ
ነገር ጠንቷል ዛሬ ፥ አውቀውት ይረፉ
ለሻጭ መስቀል ሊሆን ፥ ምሏልና ዛፉ
.
በኑረት ቀራንዮ ፥ በህይወት ጎለጎታ
ከገዳይሽ ቀዬ ፥ አንቺ ሆነሽ ጌታ
በሰማያ አኮርባጅ ፥ ወዲያ ስትላጊ
የመከራን መስቀል በሌት ተሸክመሽ ፥ መንገድ ስትፈልጊ
ጨረቃዋ ገባች ፥ ከደመና ጉያ
ከዋክቶች ሸሽተው ፥ እንደሰደድ ቋያ
ጠረንሽን ገፍተው ፥ ከገላሽ ሲርቁ
በንቄት ሸምቀው ፥ ሊጥሉሽ ዘለቁ
.
ዞር ብንል ወዲያ ፥ አራራይ መረዋ
ቀና ብንል ኦና ፥ የጠቆረ ህዋ
የፀሎትሽ ጩኸት ፥ ካልደረሰው ያ ' ቃል
እሱም እንደሰዉ ዘምቶልሽ ይሆናል።
..................... //// ..............
ሲራክ ወንድሙ @siraaq
የእቴሜቴ ጀምበር
ህዳር ፳፻፲፬ ዓ.ም
http://t.me/kinchebchabi