Get Mystery Box with random crypto!

ብትደርብብህስ? | ቅዱስ ብልግና

ብትደርብብህስ? ወንዶች ለትዳራቸው ወይም ለፍቅረኛቸው የማይታመኑ እንደሚሆኑ ሁሉ፤ ሴቶችም ከወንዶች ባልተናነሰ መልኩ ከትዳራቸው ወይም ከፍቅረኛቸው ውጭ ሊማግጡ (ቺት ሊያደርጉ) ይችላሉ። “እሷ ታማኜ ናት፤ ከልቧ ታፈቅረኛለች፤ ሌላ ወንድ በፍጹም አታስብም፤ ሐይማኖተኛና ንጹህ አፍቃሪዬ ናት፤ ህይወቷን አሳልፋ ለእኔ ትሰጣለች!” በማለት፣ በእርግጠኝነት ቀበቶህን አጥብቀህ የምትከራከርላት ሚስትህ ወይም ፍቅረኛህ ከሌላ ወንድ ጋር በድብቅ የፍቅር ግንኙነት ጀምራ ብትይዛት ለማመን ይከብድህ ይሆናል። አንዳንድ ወንዶች ራሳቸውን የሚገድሉት ወይም ፍቅረኛቸውንና አፍቃሪዋን ገድለው እስርቤት ቀሪ ዘመናቸውን የሚያሳልፉትም በዚህ ምክንያት ነው።

ሚስትህ ወይም ፍቅረኛህ በላይህ ላይ ደርባ ከሆነ የሚከተሉት ምልክቶች ፍንጭ ሰጪዎች ናቸው፦

1) ያልተለመደ የባህሪ ለውጥ ካሳየች። ገና ስትተዋወቁ ብዙ የወንድ ጓደኞች ካሏትና ግንኙነት ከጀመራችሁም በኋላ ከነሱ ጋር ጊዜዋን አልፎ አልፎ የምታሳልፍ ከሆነ፣ ይሄ ብዙም ሊያሳስብህ አይገባም። ነገር ግን በቅርቡ ከሆነ ወንድ ጋር ጓደኝነት መጀመሯን ከነገረችህ ወይም ወሬ ከሰማህ፣ መጠርጠር ይኖርብኻል።

2) ያንተን ርዳታ መፈለግ ካቆመች። ከዚህ በፊት አንተ በሌለህበት ጥናት የማታጠና፣ ገበያ ወይም ጂም የማትሄድ፣ መንገድ የማታቋርጥ ከሆነ፤ ሆኖም ከመሬት ተነስታ እነዚህን ነገሮች ብቻዋን ማድረግ ከጀመረች፣ ምክንያቷም ግልጽ ካልሆነ፣ ሌላ ሰው ያንተን ቦታ ተክቶ እየተራዳት መሆን አለበት።

3) መናደድ ካቆመች። ከዚህ በፊት ምሳ አብረኻት ካልበላህ፣ ግንቧሯን ሳትስም ከቤት ከወጣህ፣ ከጓደኞቿ ጋር ለመዝናናት አልወጣም ካልክ፣ ስልክ ሳትደውልላት ከቀረህ በጣም የምትናደድ ከነበረች፤ አሁን ግን ያ ባህሪህ ምንም የማያናድዳት ከሆነ፣ ወይ ላንተ ያላት ፍቅር እየተሟጠጠ መጥቷል አልያም ሌላ ሰው ቦታህን ወስዷል። ያለምክንያት ግዴለሽ ልትሆን አትችልም።

4) በጣም ሚስጥረኛ መሆን ካበዛች። እንደድሮው ስለውሎዋ አታወራም። ገና ምንም ሳትጠይቃት ስታደርግ የዋለችውን ሁሉ ትቀባጥርልህ ነበረች፣ ዛሬ ግን አንተ ነህ ጠያቂ። ጠይቀህም በቂ ምላሽ አታገኝም። የተድበሰበሰ ምላሽ ነው የምትሰጥህ ወይም ከነጭራሹ የማውራት ፍላጎት የላትም። ሚስጥረኛነት ካበዛች፣ አንተ እንድታውቅባት የማትፈልገው ነገር አለ ወይም አንተ ጋር የምትመጣው ከሌላ ሰው ጋር አውርታ ባትሪዋን ከጨረሰች በኋላ ነው።

5) ከመጠን በላይ ጥሩ ከሆነች። ስታጠፋ አትቆጣህም። ስትበድላት ስቃ ታሳልፋለች ወይም ትንሽ አኩርፋ የረሳች መስላ ታልፈዋለች። እስኪሰለችህ ድረስ በስልክም ሆነ አልጋ ላይ በጣም እንደምትወድህ ትነግርኻለች። በቀን አንዴ ወይም ሁለቴ እወድኻለው የምትልህ፣ በቀን ሺ ጊዜ መውደዷን በተለያየ መንገድ የምትገልጽ ከሆነ፣ አንተን ለመካስ የምታደርገው ጥረት ሊሆን ይችላል። ከአንተ ተደብቃ ሌላ ወንድ በመብዳቷ ወይም በመሳሟ ስለተጸጸተች ወይም “ሌላ ፍቅረኛ ይዛለች” ብለህ እንዳትጠረጥራት ከመጠን በላይ ጥሩ ሆና ትገኝ ይሆናል።

በርግጥ እነዚህ ምልክቶች ሚስትህ ወይም ፍቅረኛህ ባንተ ላይ ስለመደረቧ መቶ በመቶ የሚያረጋግጡ አይደሉም። “ከጀርባዬ እያማግጥሽ ነው” የሚል ክስ ከማቅረብህ በፊትና ግንኙነታችሁን አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ከመወሰንህ በፊት ነገሮችን በደንብ መርምር። በደንብ አጣራ። በስማበለው ወይም መረጃ በሌለው ጥርጣሬ አትደንፋ። ጥርጣሬህ ከቅናት የመነጨ ይሆናል። የማያከራክር መረጃ እጅህ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ጥርጣሬህን በውስጥህ ያዝ። ሰው ነገረኝ ብለህ ወይም ከሌላ ወንድ ጋር ስታወራ፣ ጊዜ ስታሳልፍ ስላየኻት ብቻ በአማጋጭነት መኮነን የለብህም።

“እያማገጠችብኝ ነው” ብለህ የምታስብ ከሆነ፣ ስለማማገጥ ሳታነሳ በግልጽ አወያያት። ችግር ካለ ጠይቃት። ባህሪዋ ሰሞኑን እየተቀያየረብህ መምጣቱን ምሳሌ እየጠቀስክ ንገራት። የሚያስጨንቃት ነገር ካለ ማወቅ እንደምትፈልግና መፍትሄ በማፈላለግ እንደምትተባበራት ግለጽላት። ፍላጎትህ ነገሮችን ካንተ እንድትደብቅ ሳይሆን ግልጽ ሆና የሚያስጨንቃትን ነገር እንድታወያይህ መሆን አለበት። በደንብ መነጋገር መቻል አለባችሁ። ውይይት የጎደለው ግንኙነት ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ያንተ አቀራረብ ወሳኝነት አለው። አቀራረብህ ካላስፈራት ወይም ወደ ኋላ እንድታፈገፍግ ካላደረጋት፣ ቀስ በቀስ የሚያሳስባትን ነገር ወይም ባህሪዋ የተለወጠበትን ምክንያት ትነግርኻለች።

መቶ በመቶ እርግጠኛ ካልሆንክ፣ የሆንክ ቢመስልህ እንኳ “እያደረግሽ ያለውን ደርሼበታለሁ! በጀርባዬ ምን እያደረግሽ እንደሆነ አውቃለሁ!” በማለት ውንጀላ ውስጥ አትግባ። ውንጀላህ እውነት ሆኖ ካልተገኘ፣ ልታምናት ባለመቻልህና ባላደረገችው ነገር በመወንጀልህ አዝና ልትለይህ ትችላለች። ባንተ ላይ መደረቧን ብታውቅ እንኳ ከሷ እስኪመጣ ድረስ የማታውቅ መስለህ ጠብቅ። ምንም ከሷ የሚመጣ ነገር ከሌላ የማያከራክር መረጃ በእጅህ ከያዝክ በኋላ አፋጥጣት። መለያየት የግድ ከሆነ ደግሞ በሰላም አሰናብታት። “ልግደልሽ፣ ልስቀልሽ፣ ልሰንጥቅሽ፣ ራሴን ልግደል፣ ወ.ዘ.ተ.” ድሮ የቀረ ነገር ነው። በሆነ ሰዓት ትወድህ ነበር፣ አሁን አትወድህም። አከተመ። በኃይል ያንተ ልታደርጋት አትችልም። “የእኔ ካልሆንሽ አፈር ይብላሽ!” ማለት ደግሞ ራስ ወዳድነት ነው። ከልብህ የምታፈቅራት ከሆነ ምኞትህ እሷን ደስተኛ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ” ብለህ ሸኛት። ነገር ግን ምኞትህ እሷን መበቀል ከሆነ የምትወደው እሷን ሳይሆን ራስህን ነው። Share our channel Link: @kidusblgna ለአስተያየት ወይም ጥያቄ :@kidusblgnabo