Get Mystery Box with random crypto!

የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 - መንግሥት በፉጨት የጠራውን በጅራ | 🇪🇹ዘወልድ ምክረ-ሕግ🇪🇹‼️

የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 - መንግሥት በፉጨት የጠራውን በጅራፍ የገረፈበት ሕግ

“The execution of the laws is more important than the making of them” Thomas Jefferson

“የሕጎች አተገባበር ሕጎቹን ከመደንገግ በላይ አጅግ አስፈላጊ ነው”

“ይህ ጽሑፍ በሕግ ትምህርት ዘርፍ በተለይም በውል ሕግ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ዛሬም በሕግ ሥርዓቱ መሻሻል ላይ አሻራቸውን እያኖሩ ላሉት ለፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ትንሽ ምስጋና ትሁንልኝ”

ዛሬም ያልተላቀቅነው እርግማን ነው፡፡ ትውልድ ቢቀያየርም፤ መሪ ቢለዋወጥም፤ ዓለም ብትሰለጥንም፤ ዕውቀት ቢገባንም፤---ትላንት ታሪካችን ነበር፡፡ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ብለው በልጅ አዕምሮ ያስተማሩንም ይህንኑ ነው….‘የእርስ በእርስ ጦርነት’፡፡ዛሬም ይህ ትውልድም ይህን እርግማን ዕውቀት አድርጎት እርስ በእርሱ እየተገዳደለ የራሱን ታሪክን በመጻፍ ላይ ነው፡፡ የኢፌዲሪ መንግሥትም “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ብሎ ለጠራው ለዚህ ጦርነት “ወንዱን ትጥቅ ሴቷን ስንቅ” ይዛችሁ ውጡ ብሎ አስቸኳይ አዋጅ በነጋሪት ጎስሞ ከድሉ መልስ በጦርነቱ ጊዜ ለተጠቀምብክበት ትጥቅ ፍቃድ የለህም ብሎ ታህሳስ 30 ቀን 2012ዓ.ም ባወጣው የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በሕግ ጅራፍ ህዝቡን ዛሬም እየገረፈ ነው ብልህ---ምላሽህ እንደ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “ጃንሆይ ይህን ህዝብ ግን እንደራስዎ ህዝብ ያዩታል?” የሚለው ጥያቄ አይሆንም ወዳጄ? ተከተለኝማ ነገሩን ልዝለቅህ…



1. መነሻ ምክንያት

አንድ

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ በጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም የጦር መሣሪያ ፍቃድ ሳይኖረው 16 ጥይትና 01 ካርታ ይዞ በመገኘቱ የጦር መሣሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዎጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4/1/ እና 22/3/ ተላልፎል የሚል በማቅረቡ ነው፡፡ ተከሳሹ የተከሰሱባቸው መሣሪያዎች አስቀድመው ከያዙትና ፍቃድ ካላቸው መሣሪያዎች በተጨማሪ ነው፡፡

ሁለት

መንግሥት በህልውናው ዘመቻ ጊዜ ያወጣሁን ልዩ መመሪያ ተከትሎ የያዘውን ሽጉጥና 1 ጥይት አስመዝገቦ በዘመቻው ከተሳተፈ በኃላ ዘመቻው ሲጠናቀቅ ግለሰቡን ተከሳሽ በማድረግ ከሳሽ በየካቲት 7 ቀን 2014ዓ.ም የጦር መሣሪያ ፍቃድ ሳይኖረው 1 ጥይትና አንድ ሽጉጥ ይዞ በመገኘቱ የጦር መሣሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዎጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4/1/ እና 22/3/ ተላልፎል የሚል ክስ በፌደራል ዐቃቤ-ሕግ የቀረበባቸው መሆኑ ነው፡፡

2. የጦር መሣሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዎጅ ቁጥር 1177/2012 የአተገባበር አድማስ

ይህ የጦር መሣሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዎጅ በአንቀጽ ቁጥር 29 ላይ ከታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆንና የደነገገ ቢሆንም በመሸጋገሪያው ድንጋጌ በሆነው አንቀጽ ቁጥር 23(1) ላይ ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት መሣሪያ የያዙና ለያዙት የጦር መሣሪያ ፍቃድ የመያዝና የመጠቀም ፍቃድ ያላቸው ሰዎች በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ፍቃድ የመጠየቅና በአዎጁ የተመለከቱትን መስፈርቶችን አሟልተው ከተቆጣጣሪው ተቋም ፍቃድ መውሰድ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡
እንደዚሁም ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት ፍቃድ ሳይሰጣቸው ግን ደግሞ የጦር መሣሪያ የያዙ ሰዎች ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ፍቃድ የመጠየቅና በአዎጁ የተመለከቱትን መስፈርቶችን አሟልተው ከተቆጣጣሪው ተቋም ፍቃድ መውሰድ እንዳለባቸው በአንቀጽ ቁጥር 23(2) ላይ ተደንግጓል፡፡
በመሆኑም አስቀድሞ በነበረው የሕግ አሰራር የጸና ፍቃድ ያላቸው ግለሰቦች በአንቀጽ 23(1) መሰረት ቀርበው አዲስ ፍቃድ ለማውጣት የሁለት ዓመታት ማለትም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2014ዓ.ም ጊዜ ድረስ አላቸው፡፡
እንደዚሁም አስቀድሞ በነበረው አሰራር ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሣሪያ የያዙ ሰዎች ደግሞ የአንድ ዓመት ማለትም እስከ ታኀሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ፍቃድ የማውጣት መብት በሕጉ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተለይም የጦር መሣሪያ የያዙ ግለሰቦች ከላይ የተመለከተውን ግዴታቸውን እንዲወጡ አዲስ ፍቃድ እንዲያወጡ የጊዜ ሰሌዳ የማስቀመጥ ግዴታ በተቆጣጣሪው ተቋም ላይ ተጥሏል። ዳሩ ግን ተቋጣጣሪ ተቋሙ የጊዜ ሰሌዳ አላወጣም። በዚህም ተቋሙ ይህን መንግሥታዊ ግዴታውን አልተወጣም። ስለዚህ የማስመዝገቢያ ጊዜ ባላለፈበት፣ መመሪያና የጊዜ ሠሌዳ ባልወጠዓበት ሁኔታ ግለሰቦችን ተፈጻሚ ሊደረግ የማይገባባቸውን የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012ን መሠረት በማድረግ ምንም ዓይነት ክስ ሊቀርብ አይገባም።
ነገር ግን ዛሬም እራሱ መንግሥት ላልተወጣው ግዴታ ግለሰቦችን እየቀጣ ነው፡፡ ፍ/ቤቶችም እንደ ሦስተኛ የመንግሥት አካልነታቸውና ሌሎች የመንግሥት አካል የሆኑትን ሕግ አውጪና ሕግ አስፈጻሚ በcheck & balance ስልጣናቸው መቆጣጠርና ይህ አለመተግበሩን በመከታተል ግለሰቦችን ነጻ ሊያደርግ ሲገባው ሕጉን እንደ ወረደ በመተግበር የአስፈጻሚው አካል ጅራፍ የሚጮህበት ሜዳ መሆናቸው ሊቀር ይገባል፡፡
3. ልዩ ሁኔታ

የጸና ፍቃድ የሌላቸው የጦር መሣሪያዎችን ሁሉ በአዲስ ምዝገባ ህጋዊ ለማድረግ መመሪያ የወጣ ስለመሆኑ

ሀገራችን የነበረችበትን ህልውና የማስከበር የጦርነት ዘመቻን ተከትሎ መንግሥት ማንኛውም ሰው የጸና ፍቃድ ባይኖረውም የጦር መሣሪያ የያዘ በሙሉ ይህን የጦር መሣሪያ እንዲያስመዘግብና አስቀድሞ ያለፍቃድ በመያዙም የወንጀል ተግባር ተደርጎ እንደማይቆጠር የሚገልጽ መምሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ሲደደረግ ነበር፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም የወንጀል ሕግን አስመልክቶ የሚወጣ ሕግና መመሪያ ለተከሳሹ ጥቅም የሚሰጥ ከሆነ ወደኃላ በመሄድ ተፈጻሚ ሊሆን የሚገባው ስለመሆኑ የሚደነግግው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ ቁጥር 5(3) እና ኢትዮጵያ ያጸደቀችሁ ዓለምአቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ ቁጥር 9(4) አንዱና ዋናው የሕጉ መርህ ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ልዩ የመንግሥት የዘመቻ ጥሪና መመሪያ ያለፍቃድ የጦር መሣሪያ መያዝን አስመልክቶ በጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012 መሰረት ክስ የቀረበባቸውን እና ጉዳያቸው በፖሊስ በምርመራ ላይ ያሉ ጉዳዮችን ሁሉ ወንጀልነታቸውን ያስቀረ በመሆኑ ይህ ልዩ መመሪያ በስራ ላይ በነበረ ጊዜና ከዚያ በፊት በነበሩ ጉዳዮች ላይ አዎጅ ቁጥር 1177/2012 ተፈጻሚነት የለውም፡፡
4. ትግበራ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑኝን ምክንያቶች በግል የገጠሙኝ ጉዳዮች ሲሆኑ በትግበራ ላይ ያለውን ሂደት ለመጠቆም የሚረዱ ከመሆኑ ባሻገር አጠቃላይ ስለአተገባሩ መደምደሚያ ላይ ልንደርስባቸው የሚገቡ አይደሉም፡፡ በመሆኑም እናንተም የገጠማችሀን ጨምራችሁበት በዕውቀት ብርህን ይበልጥ እንድንቀራረብና ወጥ እና ታማኝ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የበኩላችንን እንድናዋጣ አደራ እላለሁ፡፡

አመሰግናለሁ! Dagim Assefa source Abyssinia Law blog , Apr 20 2022