Get Mystery Box with random crypto!

ሰላም ለእናንተ ይሁን እንዴት አደራችሁ 'በመታነጽ ላይ ሳለህ የቦዘንክ ቢመስላቸው አትደነቅ!' | ከዚም ከዚያ ጉዞ ወደ መልካምነት!

ሰላም ለእናንተ ይሁን እንዴት አደራችሁ

"በመታነጽ ላይ ሳለህ የቦዘንክ ቢመስላቸው አትደነቅ!"

ድሮ እኛ ሃይ ስኩል ስንማር 'ከመማር ይልቅ ፋብሪካ መሥራት ይሻላል' ብለው ትምህርት አቋርጠው ሥራ የገቡ ጓደኞቻችን ነበሩ።

እነዚህ ጓደኞቻችን ወድያው በወሩ ደመወዝ አገኙ፤ ልብስ ቀየሩ። ሲቆዩ ቤት ተከራዩ፤ አልጋና ፍራሽ ፣ ቁምሳጥን ፣ ወንበርና ጠረጴዛ ገዙ። ጓደኛ ያዙ፤ ኬክ ጋበዙ። ኋላም አንዳንዶቹ አግብተው ሌሎቹም በውጭ ወለዱ።

ያኔ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ አንዱ ወዳጄ አገኘኝና "አሁንም እየተማርክ ነው?" አለኝ። አዎ! ነበር መልሴ። "አይደክምህም? አይሰለችህም?" አለኝ። "አሁን እኮ ልጨርስ ነው" አልኩና ተለየሁት።

ከዓመት በኋላ እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ይዤ ሥራ ስጀምር የወዳጄ ደመወዝ የእኔን ሩብ ያህል ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ አንድ ምሽት ላይ ወዳጄን አገኘሁት። "ከየት ነው?" ስለው "ከትምህርት" አለኝ። የማታ ትምህርት ጀምሮ ነበር። በቀን "አይሰለችህም?" ያለኝን እሱ በማታ መትጋት ጀምሮበት ኖሯል። "ህምምም..." ብዬ "ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?" ስለው እኔ ቀን የተማርሁትን እጥፍ ጊዜ ጠራልኝ።

አንዳንዱ እንዲህ ነው። መጀመሪያ ሳይታየው ኋላ ከረፈደ እጥፍ ዋጋ ሊከፍል ይገደዳል። ስኬት ቀድሞ በመራ አይደለም። ከእውቀት ሥራን ባስቀደመም አይደለም። ሥራ በዕውቀት ካልሆነ ልፋት ነው።

6ተኛ ፎቅ ላይ በፓምፕ እየተገፋ ኮንክሪት ሲሞላ አይተሃል? ያ በእውቀት የሚሠራ ነው። ያለእውቀት የሚሠራው ግን በባሬላ እያጋዘ ይደክማል።

ትጋት እና ልፋት ይለያያሉ። ትጋት የእውቀት ሥራ፤ ልፋት ደግሞ ተቃራኒው ነው። ትጋ እንጂ አትልፋ!

በልፋት የትም አትደርስም። ይልቅ ጭንቅላትህን አጎልምስ።

አየህ አንተ ስትታነጽ ፣ ስትተጋ ማንም ልብ አይልህም። ያንተ ራስን ማነጽ አርቀው ለማያስቡት ቦዘኔነት ነው። ሲያዩህ መሬት አትቆፍርም ፣ እንጨት አትልግም ፣ ምስማር አትመታም ፣ ልብስ አትሰፋም ፣ ዳቦ አትጋግርም ፣ መርፌ አትወጋም። ለእነርሱ አንተ እየቦዘንክ ነው።

መጨረሻ ተሳክቶልህ ፣ በኑሮ ከፍ ብለህ ሲያዩህ ግን "እድለኛ ነህ" ይሉሃል። እውነት ነው እድል ማለት ስትተጋ ሳትታይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻል ነው።

ስንዴዋ አፈር ውስጥ ገብታ ስትበሰብስ ውጤቱን ለሚያውቀው ለገበሬው እንጂ ለሌላው ብክነት ነው። ሌሎች ውጤቱን የሚያዩት ስንዴዋ ስታፈራ ነው።

ዘሩን የሚያናንቁ በፍሬው ቢደነቁ አትገረም።

አንተ ግን ለሌሎች ታይታ ሳይሆን በገባህ መንገድ አቅጣጫህን መርጠህ ትጋ!

አንድ ቀን ውጤቱን ሲያዩ "እድለኛ ነህ" ይሉሃል።

ጌታቸው ከበደ

ከእዚሁ ከቴሌግራም መንደር የተወሰደ!

መልካም ቀን፤ ቸር ያሰማን፤ ቸር ያውለን

@Kezimkezia