Get Mystery Box with random crypto!

+ከዚያም የተወሰኑ አገልጋዮችን አስቀምጣላቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ለ7 ዓመታት በአየሩሳሌም ከኖ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

+ከዚያም የተወሰኑ አገልጋዮችን አስቀምጣላቸው ወደ
ኢየሩሳሌም በመሄድ ለ7 ዓመታት በአየሩሳሌም ከኖረች
በኋላ የእመቤታችን በዓል ለማክበር ወደ ግብፅ በመሄድ
ላይ ሳለች በመንገድ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብታ
ስትፀልይ እመቤታችን በስዕሏ ላይ ተገልጣ: ቦታዋ
በኢትዮጵያ መሆኑን ነግራ: እጇን ዘርግታ "ወደ ኢትዮጵያ
ሂጂ" ብላ ነገረቻት::

+በኋላ በብርሃን አምድና በቅዱስ ሚካኤል እየተመራች
አሁን ወደ ምትታወቅበትና የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ወደ
ተገለፀበት እመ ምዑዝ ኪዳነ ምህረት ቅድስት ፍቅርተ
ክርስቶስ አንድነት ገዳም ደርሳለች፡፡
+በቦታው ስትደርስ የቦታው ልምላሜ የሚያስደስት ነበርና
"ይህች ቦታ ምን ታምር!" ብላለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን
ድረስ ምንታምር በመባል ይጠራል፡፡

+ምንታምር ላይ ከአገልጋዮቿ ጋር በመሆን አርፋ ሳለ
ከኢየሩሳሌም መርቶ ያመጣት የብርሃን አምድ በዚያ ቦታ
ላይ በስፋት ረቦ (ከምድር እስከ ሰማ ተተክሎ) ብታየው:
መልአኩም "ቦታሽ ይሄ ነው" ብሎ ቢነግራት በዚያው
ተቀምጣለች፡፡

+የቦታው ባለ አባት "ይህን ቦታ ልቀቂ" ቢሎ ቢጠይቃት
"እግዚአብሔር የሰጠኝ ቦታዬ ነው" ብላዋለች፡፡ እርሱም
ለክስ ወደ ጎንደር በመሄድ አፄ ሱስንዮስ አርፈው አፄ
ፋሲል ነግሰው ነበርና እሳቸውን ፍርድ ቢጠይቃቸው በዝና
ያውቋት ነበርና "ቤተ ክርስቲያን ካልተሰራ ትልቀቅልህ:
ከተሠራ ግን ሌላ ቦታ ይሰጥሃል" የሚል ፍርድ አስፈርዶ
ነበር::

+ሲመለስ ቅዱስ ሚካኤል ቀድሞ "ቶሎ ቤተ ክርስቲያን
ስሪ እንዲህ የሚል ፍርድ ተፈርዷል ብሎ ነግሯት ‹‹ታህሳስ
14 ቀን ከነግህ ፀሎት በኋላ በሰንሰልና በስሚዛ
ግድግዳዋን: በአይጥ ሀረግ ማገር አድርጋ: የግድግዳ
ቤተ መቅደስ በዕለተ አርብ: በአንድ ቀን ሰርታ ታህሳስ 16
ቀን እሁድ ታቦተ ኪዳነ ምህረትን አስገብታ ቅዳሴ
አስቀድሳለች::››

+ቅዳሴውም ከተፈፀመ በኋላ ጌታችን ከቅዱስ መንበሩ
ላይ እንዳለ ሆኖ ከእናቱ ከእመቤታችን ጋራ ታያቸው፡፡
ከመንበሩ ወርዶም ይህን ቦታ በባረከው ጊዜ የስሚዛው
ቤተ መቅደስ በአራቱም አቅጣጫ ለፈጣሪው ሰገደ፡፡

+የመሬት መናወጥም ሆነ:: ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም
"ልታጠፋን መጣህን? ቤተ ክርሰቲያኔንስ ልታፈርሳት
ነው?" ብላ ብትጠይቀው "ይህ የሰንሰል ቤተ መቅደስሽ
ዳግም እስከምመጣ ድረስ ሳይፈርስ: ሳይታደስ ፀንቶ
ይኖራል፣ በውስጡም እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ
የክሀድያንና ፣ መናፍቃን እግር አይገባበትም፣ በውስጧ
ቁርባንን የተቀበሉ ሁለ ኃጢያታቸው ይሰረይላቸዋል፣
ዘወትር ምህረቴ በረከቴ ከእነርሱ ጋር ይኖራል" በማለት
ተናግሮ ተሰወራቸው፡፡

+ከዚያም በኋላ መነኮሳትና መነኮሳይያት የቅድስት ፍቅርተ
ክርስቶስን የትሩፋት ዜናዋን ሰምተው ከየአቅጣጫው
ተሰበሰቡ፡፡ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም በአምላክ ሀይል
ተጋድሎአቸውን ይፈፅሙ ዘንድ ታስተምራቸው ፣
ትመክራቸው፣ በተግባርም እያሳየቻቸው ለብዙ ዘመናት
ከኖሩ በኋላ በገዳሙ ላይ የአጋንንት ፆር እንዳይነሳ
ወንዶቹን ለብቻ ሴቶቹን ለብቻ አደረገች፡፡

+ዘወትርም እንዳይተያዩ የእግዚአብሔር መልዐክ
በቅድስተ ፍቅርተ ክርሰቶስ ፀሎት ይጠብቃቸው ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከዚህ
ኃላፊ ዓለም መለየቷ በቀረበ ጊዜ ሁለት መላዕክት ወደ
እርሷ መጥተው በብርሃን ሰረገላ ጭነው ወደ ደብረ ነባት
(ወደ ብሔረ- ህያዋን) ወስደው በዚያ ቅዱስ ቁርባንን
አቀብለው ወደ ቦታዎ መለሷት፡፡

+መልዐኩም "ከጻማ: ከድካም: ከመታረዝ: ከረሐብ
ከጥም: ከመትጋት: ከእንባ: ከዚህ ዓለም የምትለይበት
ጊዜ እነሆ ደረሰ" አላት፡፡ የካቲት 27 ቀንም ወደ ምስራቅ
እጇን ዘርግታ ቆማ ስትጸልይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ
ከደስታ ብርሀን ጋር ያማረ ሽታ መላ::

+ጌታችን ከአዕላፋት መላዕክትና ቅዱሳን ጋር ወደ እርሷ
መጣ፡፡ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ሰገደች፡
ተንበረከከች: እጅግም አለቀሰች፡፡ ከወደቀችበት ቦታ
አንስቶ ‹‹ላጠፋሽ አልመጣሁም ወዳጄ ላከብርሽ ነው
እንጂ›› አላት፡፡

+"የዘለአለም መንግስት አዘጋጅቼልሻለሁና ደስ ይበልሽ"፡፡
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ቃል ኪዳን እንዲገባላት
ተማጸነችው:: ጌታችንም ‹‹ሁሉም እንደ ቃልሽ ይሁንልሽ::
በስምሽ ስሜ ተጨምሯልና ለቤተ ክርስቲያንሽ መባ
የሰጠ፣ የተላከ ፣የተቀበረ፣ ቤተ መቅደስሽ መጥቶ
የተሳለመ ፣ እስከ 12 ትውልድ የምህረት ቃል ኪዳን
ሰጠሁሽ::

+በረከቴም በቤቱና በልጆቹ በገንዘቡም ላይ ይደር::
የገድልሽ መጽሐፍ ባለበት አጋንንት (ሰይጣናት)
አይቀርቡም:: በአዝመራ ስምሽን በጠሩት ጊዜ የለመለመ
ይሁን:: በጸሎትሽ የተማጸነ ሁሉ ባለጤና ይሁን::

+ስምሽን በእውነት የሚጠራ የከበረ ነው፡፡ ያለመጠራጠር
በቀናች ሐይማኖት የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ: ያጻፈ:
ያነበበ: የተረጎመ በሐይማኖት የሰማ: እስከ ቀዝቃዛ ውሃ
ድረስ የሰጠ ኃጢያቱ ይሰረይለታል::
ስለ ድካምሽ ስለ ትሩፋትሽ 7 አክሊሎችን እና ይህን ሁሉ
ቃል ኪዳን ሰጠሁሽ፡፡ ላልምረው ቦታሽን
አላስረግጠውም›› ብሏት ወደ ሰማይ አረገ፡፡

+በማግስቱ ትንሽ ህመም ታመመች ደናግል መነኮሳትን
ጠርታ የእረፍት ቀኗ መድረሱን ነገረቻቸው:: ከመካከላቸው
አንዷን ለገዳሙ አስተዳዳሪነት መርጣ በፍቅር ስም
ተሰናበተቻቸው፡፡ የዳዊት መዝሙርንም ስትጸልይ የካቲት
29 ቀን እሁድ አጥቢያ ጠዋት በጌታ በዓል አንቀላፋች
(ነፍሷ ከስጋዋ ተለየች)፡፡

+ጌታችንም ከእናቱ: ከቅዱሳኑ ጋር መጥቶ ነፍሷን
ተቀብሎ ወደ ዘለዓለም ገነት ወሰዳት፡፡ ቅዱሳንም
ከመላእክት ጋር እልል እያሉ እያመሰገኑ ወደ ዘለዓለም
ቦታ ገነት አስገቧት፡፡ ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ መቃብር
ላይ 40 ቀናት ብርሃን ሲበራበት ታይቷል፡፡

+በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት: በመቂት ወረዳ ጥባ
ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ
በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅ
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ ምዑዝ
ኪዳነ ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት ገዳምም
በዓላቶቿ የሚከበሩት ታህሳስ 16 የቅዳሴ ቤቷ እንዲሁም
የካቲት 29 ቀን በዓለ እረፍቷ ይከበራል፡፡

††† ከቅድስት እናታችን በረከት አምላክ አይለየን::

††† የካቲት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
2.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
3.ቅዱሱ ሕፃን (የፍቅርተ ክርስቶስ ልጅ)
4.ቅዱስ ቢላካርዮስ ዘሃገረ አርሞኒ (አረጋዊ: ደራሲ: ጻድቅና ሰማዕት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ

††† "መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ:: አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ::
ውበት ሐሰት ነው:: ደም ግባትም ከንቱ ነው::
እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች:: ከእጇ ፍሬ ስጧት:: ሥራዎቿም በሸንጐ ያመስግኗት::" †††
(ምሳሌ. 31:29)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††