Get Mystery Box with random crypto!

=>በወንጌላዊው አንደበት የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው:: ሐረገ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

=>በወንጌላዊው አንደበት የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው:: ሐረገ ሙላዷም ከቅዱስ አሮን ካህን ወገን ይመዘዛል:: ከአሮን በቴክታና በጥሪቃ ወርዶ ሔርሜላ ላይ ይደርሳል::

+ይህቺ ሔርሜላ የምትባል ደግ ሴት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል የተባረከ ሰው አግብታ 3 ቡሩካት ልጆችን ወለደች:: የመጀመሪያዋን 'ማርያም' አሏት:: እርሷ ቅድስት ሰሎሜን ወለደች:: ሁለተኛዋን 'ሶፍያ' አሏት:: እርሷ ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች::

+ሦስተኛዋ ግን የተለየች ናት:: 'ሐና' ብለው ሰየሟት:: እርሷም የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ወለደች:: በዚህም መሠረት ድንግል ማርያም: ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሰሎሜ የእህትማማች ልጆች ናቸው::

+ቅድስት ኤልሳቤጥ እድሜዋ በደረሰ ጊዜ ስም አጠራሩ የከበረ: ደግ ካህን ለሆነ: ለቅዱስ ዘካርያስ አጋቧት:: እርሷ የሊቀ ካህናቱ ሚስት ናትና ክብሯ ከፍ ያለ ነበር:: ምንም ልጅ ባይኖራትም ዘወትር በጸሎትና በጾም: ምጽዋትንም በማዘውተር: ነዳያንንም በማሰብ የምትኖር እናትም ነበረች::

+ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል::
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

+የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

+ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው:: ቅድስቲቷ መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች::

+ድንግል እመቤታችን ወደ እርሷ መጥታ 'ሰላም' ባለቻት ጊዜ ምንም ያሳደገቻት ልጇ ማለት ብትሆን: መንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላባት እመ ብርሃንን አመስግናታለች:: ቡርክት: ብጽእት: ከፍጥረተ ዓለሙ የከበረች መሆኗንም መስክራለች::

+በማሕጸኗ ያለ የ6 ወር ጽንስም የእመ አምላክን ድምጽ ቢሰማ በደስታ ዘሏል:: ለፈጣሪውም ስግደተ-ስባሔ አቅርቧል:: ቅድስት ኤልሳቤጥ አክላም "ወምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ-የጌታየ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይገባኛል?" ስትል በትኅትና ተናግራለች:: ከጌታ እናት ጋር ለ3 ወራት በአንድ ቤት ቆይታለች::

+ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

+እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት:: ኤልሳቤጥ ማለት 'እግዚአብሔር መሐላየ ነው': አንድም 'የጌታ አገልጋይ' ማለት ነው::

+ሊቃውንትም:-
+"+ ሰላም ለኤልሳቤጥ እንተ ወደሳ ወአልዓላ:
ሉቃስ ወንጌለ ሶበ ጸሐፈ ለታኦፊላ:
ሐገረ ይሁዳ አሜሃ ሶበ በጽሐት እምገሊላ:
ተሐስየ በውስተ ከርሣ ወአንፈርዓጸ ዕጉዋላ:
ለማርያም ድንግል ሶበ ሰምዓት ቃላ:: +"+ ሲሉ አወድሰዋታል::

=>ከቅድስት እናታችን ክብሯንና በረከቷን ይክፈለን::

   ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞