Get Mystery Box with random crypto!

ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ): † † እንኩዋን ለእመ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
† † እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የኪዳን በዓል በሰላም አደረሳችሁ † †

† † 7ቱ ኪዳናት † †

=>'ተካየደ' ማለት 'ተስማማ: ተማማለ' እንደ ማለት ሲሆን 'ኪዳን' በቁሙ 'ውል: ስምምነት' እንደ ማለት ነው:: ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር: ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል:: ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው::

+እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጉዋል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ 7 እንደ ሆኑ ታስተምራለች:: ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚሁን 7 ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን::

"ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ"
"ከመረጥኩዋቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ" (መዝ. 88:3)

1. +" ኪዳነ አዳም "+

=>አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት: የፍጡራን አስተዳዳሪ: ነቢይ: ካህንና ንጉሥ ነው:: እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው:: ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ:: (ዘፍ. 3:1)

+አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ: "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ:: (ቀሌምንጦስ: ገላ. 4:4)

2. +" ኪዳነ ኖኅ "+

=>ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት 10 ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች:: ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች:: ከመርከቡ ከወጣ በሁዋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ:: "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል:: (ዘፍ. 9:12)

3. +" ኪዳነ መልከ ጼዴቅ "+

=>መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ: የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ15 ዓመቱ መንኖ: አጽመ አዳምን ይዞ: በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር::

+እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ: በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል:: በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም:: ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: (ዘፍ. 14:17, ዕብ. 7:1)

4. +" ኪዳነ አብርሃም "+

=>ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት: ሥርወ ሃይማኖት: የጽድቅም አበጋዝ ነው:: ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርሕ አሕዛብ ይባረካሉ" አለው:: (ዘፍ. 12:1) የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው:: (ዘፍ. 17:1-14)

5. +" ኪዳነ ሙሴ "+

=>ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ: የእሥራኤል እረኛ: የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው:: በፈጣሪው ትዕዛዝ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለ40 ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል:: (ዘጸ. 20:1, 31:18)

6. +" ኪዳነ ዳዊት "+

=>ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት: ጻድቅ: የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው:: እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ" (መዝ. 131:11) ሲል ምሎለታል:: አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሰሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን:: (መዝ. 88:35)

7. +" ኪዳነ ምሕረት "+

=>በብሉይ ኪዳን የነበሩ 6ቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲዖል ማዳን ግን አልቻሉም:: ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር:: ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማሕጸን አደረ::

+በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ: አድጎ: ተጠምቆ: አስተምሮ: ሙቶ: ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው:: ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት ኪዳን) የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው::

+የጌታችን መጸነሱ: መወለዱ: መሰደዱ: መጠመቁ: ማስተማሩ: ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ: መሰቀሉ: መሞቱና መነሳቱ: ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ ኪዳነ ምሕረት ይባላል:: ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት::

+የእርሷ ኪዳን 6ቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ የኪዳናት ማሕተም ይባላል:: የድንግል ማርያም ኪዳኗ ከሲዖልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና:: መድኃኒታችን ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ ጐልጐታ ላይ ነው::

+እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ! በስምሽ ያመነውን: በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን እምርልሻለሁ" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና:: ይሔው በእመ ብርሃን ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት ማምለጥ ከጀመሩ 2ሺ ዓመታት ሆኑ:: ዛሬም እኛ ኃጥአን ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር እንኖራለን::

*" ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ: ኃጢአተነ: ወጌጋየነ:
ማርያም እሙ ለእግዚእነ:
በኪዳንኪ: ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ::"

"ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን: አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል::"

=>የአርያም ንግሥት: የሰማያውያንና ምድራውያን ኁሉ እመቤት: የአምላክ እናት: ቅድስት: ስብሕት: ክብርት: ልዕልት: ቡርክት: ፍስሕትና ጥዕምት የሆነች ድንግል ማርያም የድኅነታችን መሠረት: ላመኑባት አንገት የማታስደፋ እውነተኛ አማላጅ ናት::

+በዚህች ዕለት የካቲት 16 ስለ ወገኖቿ የሰው ልጆች ፍቅር በእንባ ያቀረበችውን ልመና የባሕርይ አምላክ የሆነ ልጁዋ ተቀብሎ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላታል:: በስምሽ ያመነ በቃል ኪዳንሽ የተማመነ እሳት አያይም ብሏታል::

=>ቸሩ ልጇ ከበረከተ ኪዳኗ አይለየን:: በዓሉንም የሰላም: የፍቅርና የበረከት ያድርግልን::

=>የካቲት 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት / የእመቤታችን አክስት / የሶፍያ ልጅ)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/ላሊበላ ወንድም)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
2.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
4.አባ ዳንኤል ጻድቅ

=>+"+"+ . . . ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ:: በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት:: በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች:- አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ: የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው:: የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጀሮየ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና:: ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈፀማልና ያመነች ብፅዕት ናት:: +"+"+ (ሉቃ. 1:39)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

የካቲት 16

✞ እንኩዋን ለእናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞

+ " ቅድስት ኤልሳቤጥ " +