Get Mystery Box with random crypto!

Daniel: ✞ እንኩዋን ለዓለም ሁሉ ጌታ 'ኢየሱስ ክርስቶስ' ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

Daniel:
✞ እንኩዋን ለዓለም ሁሉ ጌታ "ኢየሱስ ክርስቶስ" ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞

"+" ልደተ ክርስቶስ "+"

=>ዓለማትን: ዘመናትን: ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ: ወልደ አምላክ ነው:: የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ሲሆን ራሱም እግዚአብሔር ነው:: በባሕርየ ሥላሴ መበላለጥ የለምና ወልድ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው እንጂ አይበልጥምም: አያንስምም::

+እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረ: ማዕከለ ዓለም ያለና ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ጌታ ነው:: ቀዳማዊና ደኃራዊው: አልፋና ኦሜጋ እርሱ ነው:: (ዮሐ. 1:1, ራዕ. 1) ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው::

+እርሱ እውነተኛ አምላክ (ሮሜ. 9:5): የዘለዓለም አባት: የሰላምም አለቃ ነው:: (ኢሳ. 9:6) ቅድመ ዓለም ሲሠለስ: ሲቀደስ ኑሮ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እርሱ ሁሉን ያስገኛል እንጂ ለእርሱ አስገኝ የለውም::
< አንድ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ሊያውቀው የሚገባ መሠረተ እምነት ይሔው ነው !! >

+መድኃኒታችን ክርስቶስን በዚህ መንገድ የማያምንና የማያመልክ ሁሉ እርሱ ክርስቲያን አይደለም:: ምንም ሥጋችንን ተዋሕዶ ብዙ የትሕትና ሥራዎችን ቢሠራም: ቢሰቀል: ቢሞትም እርሱ እግዚአብሔር ነውና ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው ብለን ልናመልከው ይገባል::

+እንደ አርዮስ: ንስጥሮስና ልዮን የማይገቡ ነገሮችን መናገር ጐዳናው የሞት: መዳረሻውም ገሃነመ እሳት ነው:: እንኩዋን የክብር ባለቤት መድኅን ክርስቶስ ላይ በፍጡር ላይ እንኩዋ የማይገባ ነገርን የተናገረ ሁሉ የገሃነም ፍርድ አለበት::

<< ለእርሱ የዓለም ፈጣሪ: ጌታና ቤዛ ለሆነው መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ምስጋና: ጌትነት: ውዳሴና አምልኮ ይሁን !! >>

+እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ:: በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ: በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ: በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት:: በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው::

+ከዚህ በሁዋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር:: ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር: ሱባኤ ይቆጠር: ምሳሌም ይመሰል ገባ::

+ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ:: ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል:: ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት / ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል::

+ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል:: እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል::

*"+" ልደተ ክርስቶስ እምድንግል "+"*

=>"ጊዜው ሲደርስ አንባ ይፈርስ" እንዲሉ አበው መደኃኒታችን የጥልን ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ: ከኃጢአትና ከሞት ቁራኝነት ይፈታን ዘንድ: ለሰዎች ቤዛ ይሆን ዘንድ: ትንቢተ ነቢያትን ይፈጽም ዘንድ: በቀጠሮ (በ5 ቀን ተኩል) ወደዚህ ዓለም መጣ::

+የሰማይና የምድር ጌታ በእንግድነት በመጣ ጊዜም እርሱን ለመቀበል በተገባ የተገኘች ንጽሕት ሙሽራ ድንግል ማርያም ሆነች:: ከእርሷ በቀር ለዚህ ክብር ሊበቃ የሚቻለው ፍጥረት: እንኩዋን ኃጢአት ካደከመው የሰው ልጅ ከንጹሐን መላእክት ወገን አልተገኘም::

+በጊዜውም መልአከ ትፍሥሕት ቅዱስ ገብርኤል መጋቢት 29 ቀን ወደ ድንግል ወርዶ የአምላክን ሰው የመሆን ዜና ከውዳሴና ከክብር ጋር ነገራት:: (ሉቃ. 1:26) ድንግልም ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ሰማይና ምድር የማይችሉትን መለኮትን ተሸከመች::

+ልክ ሙሴ በደብረ ሲና እንዳያት ዕጽ ድንግል ማርያምንም ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም:: ስለዚህም ነገር "ወላዲተ አምላክ: ታኦዶኮስ: ንጽሕተ ንጹሐን: ቅድስተ ቅዱሳን: ንግሥተ አርያም: የባሕርያችን መመኪያ . . ." እያልን እንጠራታለን::

+ግሩም ድንቅ ጌታን ጸንሳ ዘጠኝ ወራት እስኪፈጸሙ ድረስ ብዙ ተአምራትን ሠራች:: መላእክተ ብርሃን እየታጠቁ አገለገሏት: አመሰገኗት:: ልጇን አምላክ: እርሷን እመ አምላክ እያሉ ተገዙላት::

+ከዚያም በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች::

+በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14, ሕዝ. 44:1) ተፈትሖም አላገኛትም:: ልማደ አንስትም አልጐበኛትም:: ምጥም አልነበረባትም::

+ድንግል ማርያም ክርስቶስን በወለደች ጊዜ ልጇ አምላክ: እርሷም የአምላክ እናት መሆኗ ይታወቅ ዘንድ:-

1.የብርሃን ጐርፍ ፈሰሰ:
2.99ኙ ነገደ መላእክት ወርደው "ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም" እያሉ ዘመሩ:
3.ትጉሐን እረኞች በቅዱስ ገብርኤል መሪነት መጥተው ክብሩን ተካፈሉ:
4.በሰማይም ልዩ ኮከብ ድንግልና ልጇ ተስለውበት ዝቅ ብሎ ታየ:
5.ቅድስት ሰሎሜም በድፍረት የድንግልን ሆድ ዳስሳ እጇ ቢቃጠል እንደ ገና በተአምራት ድኖላታል::

+በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ: የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም: በሁዋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ::

+ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው 12 ነገሥታት በየግላቸው 10 10 ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ::

+12ቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ 9 ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ:: 3ቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከ30ሺ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ::

+እነዚህም መሊኩ የኢትዮዽያ (የሳባ ንጉሥ ተወራጅ): በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው:: ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሔሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ::

+እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በሁዋላ በጐል ድንግል ማርያምን: ክርስቶስን: ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ:: ለ2 ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል: ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ::

+በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ:: "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል:: ወርቁን: እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው: በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ:: 3 ጊዜም እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕጻን: በ2ኛው እንደ ወጣት: በ3ኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል::

+ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ለሰብአ ሰገል ሰጠቻቸው:: እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የ2 ዓመቱን መንገድ በ40 ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም:: ተአምራትንም ሠርቷል::

<< የልደቱ ነገር እንዲሁ ተተርኮ የሚያልቅ አይደለምና ይቆየን:: የከርሞ ሰውም ይበለን:: >>

+*" ቅዱስ ላል-ይበላ ንጉሥ "*+

=>በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ:-
+በብሥራተ መልአክ ተወልዷል:
+ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል:
+የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት: በትሕርምት አድጉዋል::