Get Mystery Box with random crypto!

በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ‹‹በስ | "ቃለ እግዚአብሔር "

በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ‹‹በስድስተኛው ወር ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተላከ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፩፥፳፮)፡፡ በዚህ ቃለ ወንጌል ‹‹ስድስተኛው ወር›› የሚለው ሐረግ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ለብሥራት መላኩን ያመለክታል፡፡
በአብርሃም ቤት (በድንኳኑ) ውስጥ ወይፈኑ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ እንዳመሰገነ ዅሉ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ›› እያሉ እግዚአብሔርን በአንድነት አመስግነዋል (ሉቃ. ፪፥፲፬)፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የይስሐቅን መወለድ እና በሥጋ ማርያም መገለጡን ከነገረው በኋላ ተመልሶ ሔዷል፡፡ ‹‹ሔዷል›› ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት በሰው አምሳል ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ዅሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡
ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ተገኝቶ የይስሐቅን መወለድና የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የተናገረበት ዕለት ከመኾኑ ሌላ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ዅሉ በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱ፤ ይህንን ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው፤ አብርሃምም በአማላጅነት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የተማጸነው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ ድኅነት እንደሚጸልዩ እና እንደሚያማልዱ፤ እንደ አብርሃም ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ተግባራቸው አድርገው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እግዚአብሔር እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤት ወደ ሰው ቤት ሲገባም የተዘጋ ማኅፀን እንደሚከፍትና ቤቱን በበረከት እንደሚሞላ፤ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየታየ አምላክነቱን ለዘመናት እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከታሪኩ እንማራለን፡፡
በአጠቃላይ ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት የመገለጥ ትምህርት በአንድ ወቅት ብቻ የተፈጸመና ‹‹ነበር›› እየተባለ የሚነገር ያለፈ ታሪክ ሳይኾን፣ ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ቃል ነው፡፡ ይህንም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ለዘመናት በሚያደርገው ድንቅ ሥራና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡ ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመለየት በተጨማሪ ለተቸገሩ በመራራት፣ በደግነት፣ በቀና አስተሳሰብ ከተጓዝን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ እርሱ ያደረበት ሰውነት ይባረካል፤ ይቀደሳልና፡፡ ደግሞም ልጅ ለሌለን ልጅ፤ ዘመድ ላጣን ዘመድ በመስጠት ዘራችንንም ይባርክልናል፡፡ በጥቅሉ የልባችንን መሻት ዐውቆ የምንሻውን መልካም ነገር ዅሉ ይፈጽምልናል፡፡ ይህ ዅሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ እኛም በርትዕት የተዋሕዶ ሃይማኖት እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባርም እንትጋ፡