Get Mystery Box with random crypto!

ድንግል ሆይ! የኃጢአቴን አጽር ቅጽር ታፈርሽልኝ ዘንድ እታመንሻለሁ፡፡ ድንግል ሆይ! የዕዳ በደሌን | "ቃለ እግዚአብሔር "

ድንግል ሆይ! የኃጢአቴን አጽር ቅጽር ታፈርሽልኝ ዘንድ እታመንሻለሁ፡፡ ድንግል ሆይ! የዕዳ በደሌን ደብዳቤ በጅሽ ትቀጅው ዘንድ እታመንሻለሁ፡፡ ድንግል ሆይ በንጽሕና ውሀ ሰውነቴን ታጽቢልኝ ዘንድ እታመንሻለሁ፡፡ ድንግል ሆይ! በመከራዬና በጭንቀቴ ጊዜ እንድትደርሽልኝ ድንግል ሆይ! እታመንሻለሁ፡፡ ለጠላቶቼ አሳልፈሽ እንዳትሰጭኝ በጠላቶቼም እጅ እንዳትጥይኝ ድንግል እታመንሻለሁ፡፡ የሚጥለኝን እንድትጥይው፣ የሚቃረነኝንም እንድትቃረኒው፡፡
ድንግል ሆይ! እታመንሻለሁ፡፡ የሚበረታታብኝን ልምሾ ታደርጊው ዘንድ የሚቃወመኝንም ትቃወሚው ዘንድ ድንግል ሆይ! እታመንሻለሁ፡፡ ስወጣ ስገባም እንድትከተይኝ ስቀመጥና ስነሣም እንድትጠብቂኝ፡፡ ጠንካራዪቱን አምባ መጠጊያ አንቺን የታመንሽቱን ጋሻ እታመንሻለሁ፡፡ አንቺን ተጠጋሁ ነፍሴንም በፊትሽ እጥላለሁ፡፡ አንቺን ተጠጋሁ፡፡ እራሴንም በእጅሽ ሰጠሁ፡፡ ከንፈሮቼንም ለምስጋናሽ መሣሪያ አደረግሁ፡፡ የሚቃረነኝ ጠላቴ እንዳያገኘኝ የሰይጣንም ፈረሶች ሠረገላ እንዳይደርስብኝ አንቺን ተጠጋሁ፡፡ በአንቺም አመንሁ ከመስቴማ ሠራዊት ከመከበብ ከርኩሳንም መናፍስት ወጥመድ እንድድን አንቺን ተጠጋሁ፡፡ የመላእክተ ጽልመት ፍላፃ እንዳይነድፈኝ፣ ከአመፀኞችም ጦር እንድድን፣ ልዩ ከሆነ ሰይፍም እንድድን አንቺን ተጠጋሁ፡፡ የጽድቅንም መንገድ ከሚቃወሙ ሰዎች ወጥመድ እንድድን አንቺን ተጠጋሁ፡፡ አንቺን አመንሁ እኔን አገልጋይሽን አድኝኝ፡፡