Get Mystery Box with random crypto!

መምህር ዐምደ ወርቅ እስጢፋኖስ ይባላል። ከልጅነቱ ዠምሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማያልቅ መንፈ | "ቃለ እግዚአብሔር "

መምህር ዐምደ ወርቅ እስጢፋኖስ ይባላል። ከልጅነቱ ዠምሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማያልቅ መንፈሳዊ ዕውቀትና ጥበብ ከደጋጎቹ ዕንቁ ሊቃውንት አባቶቻችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረ ነው።
አባቶቻችንን በዕውቀት ብቻ ሳይኾን በሕይወታቸው የሚመስላቸው ይኽ ታላቅ ሊቅ ታላቋን ገዳማችንን ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያምን ለረዥም ዘመናት ያገለገለ አኹንም በሚጠበቅበት ኹሉ እያገለገላት ያለ እጅግ ትኁት አባት ነው። በዚኽ ዘመንም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የገዳማችን እና የሰ/ት/ቤታችን ዐይን ነው።
ዕድሜውን በአገልግሎት፣ በጸሎት፣ በትህትና፣ በፍቅር የሚመራ ስለኾነ የሰ/ት/ቤታችንን መምህራን፣ አባላት እና ቤተሰቦች በማስተማር፣ በመምከር፣ በመገሰጽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አደራ እንዲወጡ እያደረገ ያለ አባት ነው።
ይኽ ታላቅ ሊቅ መምህራችን (ጋሽ ዐምዴ) ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ ለቀጣዩ የቤተ ክርስቲያን ትውልድ የሚቀመጡ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያዘጋጀ ያበረክታል። ትልልቅ የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ደራሲያንና አዘጋጆች መጻሕፍቶቻቸውን በጥልቀት እየመረመረ የአርትዖት ሥራን በየጊዜው ይሠራላቸዋል::
ይኽ ሊቅ በግሉም እስካኹን "ኆኅተ ብርሃን ወእንዚራ ስብሐት - በግዕዝና በአማርኛ" እና "ገድለ ቅድስት አርሴማ ተኣምረ ቅድስት አርሴማ መልክአ ቅድስት አርሴማ - በግዕዝና በአማርኛ" የተሰኙ መጻሕፍትን አዘጋጅቶ ለሕትመት አቅርቦአል:: በቅርቡም "መጻሕፍተ ድርሳናቲሁ ለቅዱስ ቄርሎስ ድርሳነ ቄርሎስ ዘውእቱ እሰትጉቡእ ግጻዌ ድርሳን ዘውእቱ ጰላድዮን ተረፈ ቄርሎስ" የተሰኘ መጽሐፍ በትዕግሥት ተርጎሞ አዘጋጅቶአል።
ይኽነንም ብዙ ምሥጢራትን የያዘ መጽሐፍ እሑድ ዕለት ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 7 ሰዓት ዠምሮ በሰ/ት/ቤቱ አዳራሽ እኛ ልጆቹ ባለንበት ተጋባዥ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና ምዕመናን በተገኙበት ይመረቃል።