Get Mystery Box with random crypto!

ሚስጥራዊ መረጃዎቻችንን ለመመንተፍ በማሰብ ወደ አካዉንታችን የሚላኩ መልእክቶች (የፊሺንግ) ጥቃቶ | JOSIE TECH™💡

ሚስጥራዊ መረጃዎቻችንን ለመመንተፍ በማሰብ ወደ አካዉንታችን የሚላኩ መልእክቶች (የፊሺንግ) ጥቃቶች እንዴትስ መከላከል እንችላለን?

ፊሺንግ /Phishing/ አንዱ የሳይበር ጥቃት ዓይነት ሲሆን የኢ-ሜይል አድራሻችንን መሠረት በማድረግ ለሚፈፀም የጥቃት ዓይነት የተሰጠ ሙያዊ ቃል ነው፡፡

የፊሺንግ ጥቃት ወንጀለኞች ግላዊ የሆኑ መረጃዎቻችንን ለመስረቅ ወይም ላልተገባ ዓላማ ለማዋል የሚጠቀሙበት የማጭበርበሪያ መንገድ ነው፡፡ ለምሣሌ የባንክ የሒሳብ ቁጥራችንን ወይም የይለፍ-ቃሎቻችንን ለመመንተፍ በኢ-ሜይል አድራሻችን የሚላኩ የማደናገሪያ መልዕክቶች ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡

በኢ-ሜይል አድራሻ የሚላኩ የፊሺንግ መልዕክቶች ለተጠቃሚዎች እውነተኛ የሚመስሉ፤ ተጠቃሚውን ከተለያየ የጥቃት ሥጋት ለመጠበቅ ወይም ለመርዳት እንደሆነ የሚገልፁ እና አንዳንድ ጊዜም ተጠቃሚዎች ሎተሪ ወይም ነጻ የትምህርት ዕድል አሸናፊ እንደሆኑ የሚያበስሩ በመምሰል የማታለል ዓላማ ያላቸው ይዘቶች ናቸው፡፡
ፊሺንግ የመረጃ መንታፊዎቹ ያዘጋጁትን አገናኝ /Link/ ተጠቃሚዎች እንዲከፍቱ በማግባባት እውነተኛ የዕድሉ አሸናፊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በሚመስል አግባብ አካውንታቸውን እና ምስጢራዊ የይለፍ ቃል እንዲያስገቡ በመጠየቅ ጥቃት ለማድረስ የሚጠቀሙበት ዘዴም ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ የፊሺንግ ጥቃት ፈጻሚዎች ዋና ዓላማ የግለሰቦችን የባንክ ቁጥር ለመመንተፍ ወይም ግላዊ መረጃዎችን ለሌሎች አሳልፎ ለመሸጥ በማቀድ የሚፈጸም ህገ-ወጥ ተግባር ነው፡፡

የፊሺንግ ጥቃትን ለመከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች
የርዕሰ ጉዳዩ ትክክለኛነት መረጋገጥ /Subject Line and Tone/

• አብዛኛውን ጊዜ ከምንጠቀምባቸው ባንኮች ወይም የፋይናንስ ተቋማት የተላኩ የሚመስሉ የፊሺንግ መዝባሪዎች መልዕክቶች በኢ-ሜይል አድራሻዎቻችን ተልከው እናገኛለን፡፡ በዚህ ወቅት መልዕክቶቹን ከመክፈታችን በፊት ትክክለኛ አድራሻ መሆኑን ወደ ባንኮቹ ወይም ፋይናንስ ተቋማቱ በመደወል ልናረጋግጥ ይገባል፡፡ አንዳንድ የመልዕክት አድራሻዎች የትክክለኞቹን የፋይናንስ ተቋማት ስያሜ በተወሰነ ፊደል ለውጥ በማድረግ በቀላሉ ለማታለል የሚሞክሩ ናቸው፡፡
አባሪ /Attachments/

• የፊሺንግ ጥቃት ፈጻሚዎች ኢ-ሜይል አካውንታችንን ለመስረቅ የኛን ትኩረት የሚስቡ አባሪ ፋይሎችን የሚልኩልን ሲሆን ፋይሎቹን በምንከፍታቸው ጊዜ የተላኩልን መልዕክቶች ለህገወጥ ተግባር ሆን ተብለው የተሰሩ ማጥመጃዎች በመሆናቸው ኮምፒውተራችንን ለጉዳት ያጋልጣሉ፡፡ በመሆኑም ሁሉም አባሪዎች ጠቃሚ መረጃዎች ናቸው ብሎ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑንና የሚላክልንን መልዕክት ከምናውቀው ትክክለኛ አካል የተላከ መሆኑን መረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡
አገናኝ /Link/

• ሁልጊዜም በኢ-ሜይል ለሚላኩ አገናኞች ተገቢውን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ የተላኩልን ሊንኮች ትክክለኝነታቸውን ለማረጋገጥ ሊንኩን በቀጥታ በድረ-ገጽ ላይ በመተየብ እውነተኛ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ አንዳንድ የፊሺንግ ሊንኮች “Click here”፣ “Preview document” ወይም “Sign In” የሚሉ እንድንከፍታቸው የሚጋብዙ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡
ስልክ ቁጥሮች /Phone Numbers/

• በኢ-ሜይል የሚላኩ የማረጋገጫ ስልክ ቁጥሮችን መጠራጠር ተገቢ ነው፡፡ የተላከልን ስልክ ቁጥሩ ትክክለኛነቱን ከባንክ ደብተር ላይ ከሚገኝ አድራሻ በመውሰድ ደውለን ልናረጋግጥ ይገባል፡፡ አለበለዚያ በኢ-ሜይል የቀረበልንን መልዕክት በኢ-ሜይል አድራሻችን በተላከ ስልክ ቁጥር ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ከደወልን አጥፊዎች አስቀድመው ያዘጋጁት ቁጥር ከሆነ በሚፈልጉት መንገድ መረጃ በመስጠት ለጥቃት ልንጋለጥ ስለምንችል ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡


   |||  - @josie_Tech - |||