Get Mystery Box with random crypto!

+ ለእግዚአብሔር ስጦታ + ............................................. | የጅ/ዩ/ቴ/ኢ/ግ/ግቢ ጉባኤ [Y/M/M/Y/I/T/Jimmaa]

+ ለእግዚአብሔር ስጦታ +
.............................................................
ለአምላክህ ስጦታ ለመስጠት አስበህ ታውቃለህ? ለፈጠረህ፣ ፈጥሮም ለሚመግብህ፣ ቅዱስ መንፈሱን አሳድሮብህ ልጁ እንድትባል ላደለህ ለአባትህ ምን እንደምትሰጠው ጨንቆህ ያውቃል? እንደ አቤል አምላክህን የሚያስደስት መሥዋዕት ለማቅረብ ዓይንህ አማትሮብህ ያውቃል? "ሁሉን ለፈጠረ፣ ሁሉም በእርሱ ለሆነ፣ ያለእርሱም ምንም ምን የሆነ ለሌለ" አምላክ ስጦታ መስጠት ምንኛ ያስጨንቃል? የሁሉም ነገር ባለቤት ለሆነው ጌታ የእርሱ ያልሆነውን አዲስ ነገር ምን ልትሰጠው ትችላለህ? ከእርሱ ሳይሰጥህ ለእርሱ የምትሰጠውስ ምን አዲስ ነገር አለህ?

በእርግጥ እግዚአብሔር እኛን በየምክንያቱ ለመማርና ዋጋ ለመስጠት ስለሚቸኩል እያንዳንዷን ስለእርሱ ብለን የምናደርገውን ነገር ሁሉ ይቆጥራታል። "ያደረግነውን ስራ ስለስሙም ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመጸኛ ያልሆነው እግዚአብሔር" ለእርሱ የምንሰጠውን ገንዘብ፣ ጉልበት፣ ጊዜና ሌላው ቀርቶ ተግባር ላይ ሳይውል በሃሳብ ብቻ የቀረብንን መልካም መሻታችንን እንደ በጎ መዓዛ ያለው መሥዋዕት በደስታ ይቀበለዋል። ከእነዚህ ሁሉ ግን ይበልጥ የትኛው ስጦታ ያስደስተው ይሆን? ዕብራ 6፥10

አንድ ወላጅ ከልብ የሚደሰተው ልጁ እርሱ ያሰበለት እጅግ መልካም ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው። ለምን ቢባል ለልጁ እጅግ ብዙ ዋጋ ስለከፈለለት ነው። እጅግ ብዙ ዋጋና መሥዋዕትነት የከፈልንበት ጉዳይ ፍጻሜውን ሲያገኝ ወይም ሲሳካ ከማየት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። እግዚአብሔርም ልክ እንደዚህ ነው። ለእርሱ ብዙ ወርቅ ገዝተህ ከምትሰጠው ይልቅ አንተ ንስሐ ገብተህ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን ብትቀበልለት ከምንም በላይ ይደሰታል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለወርቅ ከመፍጠር ውጪ የከፈለለት ዋጋ የለም። ለአንተ ግን መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሕይወቱን ከፍሎልሃል። ንጹሐ ባሕርይ ሲሆን የአንተን ኃጢአት ተሸክሞ በሞቱ ደምስሶልሃል። ዋጋ ከፍሎ የሰጠህን የራሱን ስጋና ደም ኃጢአትህን ትተህ ስትበላለትና ስትጠጣለት ከምንም በላይ ታስደስተዋለህ። ስለዚህ ለእግዚአብሔር የምትሰጠው የመጨረሻ ስጦታ እርሱ የሰጠህን ስጦታ መቀበል ነው። እርሱም ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙን ነው።

ወዳጄ ሆይ ለእግዚአብሔር እንደ አየር የምትፈልገውን ነገር እንዲሰጥህ ስዕለት ስትሳል ለእርሱም የሚፈልግህን ራስህን ለመስጠት ተዘጋጅ። "ይህን ካደረግክልኝ ይህን ያህል ብር፣ ይህን ያህል ጥላ አስገባለሁ" ሳይሆን "ይህን ብታደርግልኝ ንስሐ ገብቼ እቆርባለሁ" ብለህ ተሳል። ዋጋ ከከፈለልህ ከራስህ በላይ ለእግዚአብሔር ስጦታ ልትሰጠው አትችልምና።
.........................................
ዲያቆን ዮሐንስ ደረጀ
ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ከአንድ አስተዋይ እህቴ የተማርኩት
@dnJohannes


@jitgibigubae