Get Mystery Box with random crypto!

የኡድሒያን እርድ የሚመለከቱ ጥቂት ወሳኝ ነጥቦች - ኡድሒያ ማለት በዒደል አድሓ ቀን ወደ አላህ ለ | ኢስላማዊ እና ጠቅላላ እውቀት

የኡድሒያን እርድ የሚመለከቱ ጥቂት ወሳኝ ነጥቦች
-
ኡድሒያ ማለት በዒደል አድሓ ቀን ወደ አላህ ለመቃረብ ታስቦ የሚታረድ እርድ ነው፡፡ ነብዩ ﷺ በተግባር ፈፅመውታል፡፡ መዲና ላይ አስር አመት ሲኖሩም ኡድሒያን ያርዱ ነበር፡፡ (ሚሽካት፡ 1475) እንዲፈፀምም አዘዋል፡፡ ስለዚህ አቅም ያለው ሰው ሊፈፅመው ይገባል ማለት ነው፡፡ ነብዩ ﷺ “አቅሙ እያለው ኡድሒያን ያላረደ ሰው መስገጃችንን እንዳይቀርብ” ብለዋል፡፡ (ከኡድሒያ ጋር የተያያዙ እጅግ አስፈላጊ ነገሮች፡-
የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት :-

1. የሚታረደው እንስሳ ከሚከተሉት የእንስሳት አይነቶች ብቻ መሆን አለበት፡- በግ፣ ፍየል፣ ከብትና ግመል፡፡
2. ከነዚህ እንስሳቶች የትኛውን ማረድ ነው የሚበልጠው? በቅደም ተከተል ግመል፣ ከብት፣ በግ፣ ፍየል፣ ግመል በጋራ፣ ከብት በጋራ።
(ፈትዋ ለጅነተ ዳኢማህ) (ኢብኑ ዑሠይሚን፡ አሕካሙል ኡድሒያ ወዘካት)
* ከብትና ግመልን በጋራ ማረድ የፈለገ አንዱ ለ7 ሰው ነው መሆን አለበት፡፡
* ፍየልና በግ ለጋራ ማራድ አይቻልም፡፡

3. የሚታረደው እንስሳ እድሜው የደረሰ መሆን አለበት፡፡ በግ 6 ወር፣ ፍየል 1 አመት፣ ከብት 2 አመት፣ ግመል ከሆነ 5 አመት የሞላው መሆን አለበት፡፡

4. የሚታረደው እንስሳ እውር፤ በሽተኛ፤ አንካሳ፤ በጣም ያረጀ፣ አብዛኛው ወይም ግማሽና ከዚያ በላይ የሆነ ጆሮው፣ ጅራቱ፣ ላቱ፣ ቀንዱ፣ የተቆረጠ ወይም የተሰበረ መሆን የለበትም፡፡

5. የሚታረደው እንስሳ ህጋዊ በሆነ መልኩ የራስ ንብረት መሆን አለበት፡፡ (የተሰረቀ፣ የተነጠቀ፣ የተጭበረበረ ..መሆን የለበትም።)

6. የሚታረደው የግድ በተገደበው ጊዜ መሆን አለበት፡፡ እሱም ከዒድ ሶላት በኋላ እስከ ዙልሒጃ 13 ባሉት አራት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ ነብዩ ﷺ (ዒድ) ከመሰገዱ በፊት ያረደ በሷ ቦታ (እርዱን) ይድገም፡፡ ያላረደ ይረድ” ይላሉ፡፡ (ቡኻሪ)

7. ያለምንም ልዩነት ከሁለቱም ፆታ ከወንድም ከሴትም ለኡድሒያ ማረድ ይፈቀዳል፡፡ (ኢብኑ ባዝ፣ ፈታዋ ኑሪን ዐለደርብ፡ ካሴት ቁ. 72)

8. ቆዳውንም ይሁን የትኛውንም ክፍሉን መሸጥ አይፈቀድም፡፡ ለአራጁ የሚከፈለውም ከኡድሒያው ቆዳ ወይም ሌላ ክፍሉ መሆን የለበትም፡፡ ነብዩ ﷺ “የኡድሒያውን ቆዳ የሸጠ ኡድሒያ የለውም” ብለዋል፡፡ (ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 2/1055) ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “ከኡድሒያው ስጋ፣ ሞራ፣ ቆዳ፣ ወይም ሌላ ነገር መሸረጥ ክልክል ነው፡፡ ምክኒያቱም ለአላህ ያወጣው ገንዘብ ስለሆነ ልክ እንደ ሰደቃ መመለስ አይቻልም፡፡ (ፈታዋ ኢብኒ ዑሠይሚን፡ 25/162) ባይሆን ስጦታ የተሰጠው ሰው ቢሸጥ ምንም ችግር የለበትም፡፡

9. ስጋው ምን ይደረጋል? በእለቱ ከቤት ይበላል፤ ለዘመድ፣ ለጓደኛ፣ ለምስኪን ይሰድቃል ወይም ስጦታ ይሰጣል፣ ቀሪ ከኖረ ያስቀምጣል፡፡ ስጦታ የተሰጠው ሰው ግን መሸጥን ጨምሮ ሐላል በሆነ መልኩ ለፈለገው አገልግሎት ማዋል ይችላል፡፡

10. ኡድሒያውን እራሱ ባለቤቱ ቢያርድ በላጭ ነው፡፡ ካልቻለ ወይም ካልተመቸው ግን ሰው መወከል ይችላል፡፡
ከተለያዩ ፈትዋዎች የተሰበሰበ ነው፡፡

https://t.me/hooral_ayn2