Get Mystery Box with random crypto!

ሰው መሳይ በሸንጎ ~ ዑለማኦች ከሰውነት አጥር ውጭ አይደሉም። የሰው ልጅ ላይ የሚታዩ ድክመቶች ይ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ሰው መሳይ በሸንጎ
~
ዑለማኦች ከሰውነት አጥር ውጭ አይደሉም። የሰው ልጅ ላይ የሚታዩ ድክመቶች ይታዩባቸዋል። ከዒልምና ከተቅዋ አንፃር በአመዛኙ ከሌሎች ስለሚሻሉ የተሻለ ነገር እንጠብቃለን። ይሁን እንጂ "የኣደም ልጅ ሁሉ በጣም ተሳሳች ነው" ከሚለው እውነታ ውጭ እንዳልሆኑ መዘንጋት አይገባም። ስለሆነም፡
* አንዳንዴ ስሜታዊነት፣ ምቀኝነት፣ ጥቅመኝነት፣ ዝናን መሻት፣ አጉል ተጠራጣሪነት፣ ... የመሳሰሉ መጥፎ ባህሪዎች ሊፀናወቷቸው ይችላሉ።
* ወይም ተቆርቋሪና ታማኝ የመሰለ የቅርብ ሰው የሚያሳስታቸው ሊኖሩም ይችላሉ።
በነዚህ ወይም በሌላ ምክንያቶች አንዱ ዓሊም ሌላው ላይ ከባድ ቃል ሊናገር ይችላል። ይሄ በአየር ላይ ያለ ምናብ ሳይሆን ተጨባጭ ምሳሌዎች ሊጠቀሱበት የሚችል እውነታ ነው።

ይህንን ከተረዳን አንድ ዓሊም በሌላው ዓሊም ላይ ከባድ ትችት ቢሰነዝር ሳያጣሩ ከማራገብ በፊት ጉዳዩን ቆም ብሎ ማጤን ይገባል።
* ሌሎች ዓሊሞች ምን ይላሉ? ጉዳዩን ከማወቃቸው ጋር የተለየ ትንታኔ ሰጥተዋል? ተማሪዎች በጉዳዩ ላይ አርፈው እንዲቀመጡ አሳስበዋል? ዝምታን መርጠው ከሆነም ለነሱ የበቃ ዝምታ ለኛም ሊበቃን ይገባል።
* ጉዳዩ በልኩ ተይዞ ይሆን? ወይስ ድንበር ባለፈ መልኩ ነው የተያዘው?
* የትችቱ መነሻ ምንድነው? አሉባልታ ላይ ወይስ ተጨባጭ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ነው?
* ተወንጃዩ አካል ምን ይላል? እንደተዋሸበት ይናገር ይሆን? ንግግሩ ተቆልምሞ ሌላ ትርጉም ተሰጥቶበት ይሆን? እየተከሰሰ ያለው ከጥፋቱ ከተመለሰ በኋላ ይሆን?
ይሄ ትችቱ በዑለማኦች የተሰነዘረ ከሆነ ነው። ካልሆነስ?
* ሲጀመር ተቺዎቹ እነማን ናቸው? አንዳንዶቹ እዚህ ግባ የማይባሉ ከንቱ ፍጥረቶች ናቸው ከተራራ የገዘፉ ዓሊሞች ላይ አንጋጠው የሚተፉት። የሆነ ጊዜ አንዱ ጎረምሳ ዐብዱልሙሕሲን አልዐባድን ሲዘረጥጥ ነበር። በአደብ ቢያርርም ምንም አልነበረም። "ሁሉም አራሚና ታራሚ ነውና።" ነገሩ ግን እንደዚያ አልነበረም ያደረገው። ሸይኽ ዐብዱልሙሕሲን የሱን ብጤ ቀርቶ እሱ የሚያጣቅሳቸውን ሸይኾች ያስተማሩ የሸይኾቹ ሸይኽ ናቸው። እሱ በገለፀበት መልኩ ሸይኾቹ እንኳ አይደፍሯቸውም። ታላላቆቹ በሚያፍሯቸው ታላቅ ሸይኽ ላይ ሲዳፈር ማየት ያሳቅቃል።
ይህን እንድፅፍ ያደረገኝ ሸይኽ ፈላሕ ሙንደካርን፣ ሸይኽ ሷሊሕ አሱሐይሚን፣ ሸይኽ ዐብዱረዛቅ አልበድርን የሚያብጠለጥሉ አካላትን አይቼ ነው። በቃ ብልግና ጀብድ ሆነ። ለሆነ ሸይኽ ቅርብ ስለሆኑ ወይም ከሆነ አካል ተዝኪያ ስላላቸው ራሳቸውን አይነኬ የሚያደርጉ አንዳንድ "ከተዘሩ ያልታረሙ" ዋልጌዎች አሉ። ለእንዲህ አይነቶቹ ሙጅሪሞች ቦታ መስጠት ራስን ማርከስ ነው። ምግባሩ ያቆሸሸውን የማንም ተዝኪያ አያፀዳውም። አላሁል ሙስተዓን!
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor