Get Mystery Box with random crypto!

ወደ ፌስቡክ ስገባ አንድ የሚዘዋወር ፀያፍ ፖስት አየሁኝ። ዘወርወር ብዬ ሃሳቦችን ለመቃኘትም ሞክሬ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ወደ ፌስቡክ ስገባ አንድ የሚዘዋወር ፀያፍ ፖስት አየሁኝ። ዘወርወር ብዬ ሃሳቦችን ለመቃኘትም ሞክሬያለሁ። የኔ ምልከታ፦

1ኛ፦ እስካሁን ባየሁት ፖስቱ እውነተኛ ለመሆኑ ማረጋገጫ አልቀረበም። መቶ በመቶ ውሸት ነው ብዬ ባልደመድም ለራሴ እውነተኛ መስሎ አልታየኝም። እንዲያውም "ምልልሱ" የአንድ ሰው ድርሰት ነው የሚመስለው። "ሙሉ መረጃውን ከሰዓታት በኋላ አሳያለሁ" ያለውም ወንድም ቢሆን መነሻውም መድረሻውም የማይመስል ነገር ነው የፃፈው። ሙሉ ቀርቶ 1% መረጃም አላመጣም።
ለማረጋገጥ በዚህ ቁጥር አናግሩ ማለትም አስቂኝ ነው። ባለ ቁጥሩ አቀናባሪው ራሱ ይሁን ሌላ ሰው ይሁን፣ ታማኝ ይሁን አይሁን ምን ፍንጭ ይሰጣል? ማረጋገጫ ማለት እንደዚህ ነውንዴ?
ብቻ እውነት ይህንን የሰራ ኡስታዝ ካለ ነገ አላህ ፊት ይቀርባል። ቅንብር ከሆነም ነገ ምላስ ተለጉማ አካሎች በሚመሰክሩበት ቀን ውርደት ይከናነባል። ማንም ቢሆን የዘራውን ማጨዱ አይቀርም። መቼስ ከሞት በኋላ ህይወት፣ ከአላህ ፊት ቀርቦ ሂሳብ እንዳለ እናምናለን።

2ኛ፦ ባይሆን ያለንበት ተጨባጭ ከዚህ የባሰ እንጂ ያነሰ አይደለም። የቀረበው "ድርሰትም" እውነትም ሆነ ውሸት ላለንበት ችግር አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። የመስጂድ ኢማሞች፣ ኡስታዞች ኧረ እንዲያውም በእድሜ የገፉ ሸይኾች ሳይቀሩ ከዚህ የባሰ ዘረኝነት ላይ የወደቁ ብዙ አሉ። ባህር አቆራርጠው ዒልም ፍለጋ የከተሙ ወጣቶች ላይ አስቀያሚ ዘር ወለድ ችግሮችን በራሴ ታዝቤያለሁ። ከታማኝ ወንድሞችም ብዙ ሰምቻለሁ። ሱብሒ ሶላት ሳይቀር ከሰው በፊት ቀድሞ መስጂድ የሚጣድ ሰው እዚህ ላይ ልገልፀው የሚሰቀጥጥ ተግባር በዘረኝነት ተነሳስቶ ሲፈፅም ባይኔ ተመልክቻለሁ። ላኢላሀ ኢለላህ ከሚያስተሳስራቸው ወንድሞቻቸው ሞት ይልቅ ዘር የሚያገናኛቸውን የሌላ እምነት ተከታዮች የሚያስቀድሙ ብዙ አይተናል። በመስጂዶች ላይ ሳይቀር የዘር መቧደንና ጥላቻ የታየባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።

ቢሆንም፡

1- እንዲህ አይነት ችግሮችን ስናይ አላህን በመፍራት ላይ በጥብቅ መተዋወስ እንጂ ያለብን ይበልጥ ለመቆራረጥና ለመራራቅ አይደለም ማራገብ ያለብን። አነሰም በዛ ከዘር ይልቅ እምነታቸውን የሚያስቀድሙ ወገኖች በየ ብሄሩ አሉና ቢያንስ ስለነሱ ስንል እንኳ ከጅምላ ፍረጃ ርቀን ችግሩን በጥንቃቄ ማከም ላይ ብናተኩር መልካም ነው።
2- ዘረኝነት አንድን ብሄር ለይቶ የሚያጠቃ ልክፍት አይደለም። መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ጋር አለ። ጉዳዩን የኛ ሳይሆን የሌሎች አድርጎ መሳሉ ራሱ ራሱን የቻለ ዘረኝነት ነው። ወደራሳችን እንመልከት።

ይልቅ መፈራራታችንንም መፈራረጃችንንም ትተን ችግሩን እንጋፈጠው። እንዲህ እንመን። በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያለ ሙስሊም አጠቃላይ ሁሉም ወገኔ ነው። ትግሬ ሆነ በርታ፣ ኦሮሞ ሆነ አማራ፣ አፋር ሆነ ሱማሌ፣ ስልጤ ሆነ ጉራጌ፣ አደሬ ሆነ ሃላባ፣ ... ለኔ ልዩነት የለውም። በብሄር ስለሚቀርበኝ የተለየ ቦታ የምሰጠው አካል የለኝም። ሰው ለወጣበት ብሄረሰብ መቆርቆሩን አልኮንንም። ራሱን በወጣበት ዘር መግለፁንም አልነቅፍም፣ ለራሴ ባልመርጠውም። በብሄር አይን ባይሆንም እኔም የወሎ ህዝብ ከልብ ያሳዝነኛል። በተለየ እየተገፋ ያለ ከመሆኑ ጋር ተቆርቋሪ ያጣ፣ የመሰሪ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ የሆነ ብኩን ህዝብ እንደሆነ ይሰማኛል። ምናልባት ለወጣሁበት ማህበረሰብ ልበ ስስ ሆኜ ተሳስቼ ከሆነም አላውቅም። ምናልባት!
የሆነ ሆኖ ለአማራ ህዝብ ለመታገል ኦሮሞን፣ ለኦሮሞ ህዝብ ለመታገልም እንዲሁ አማራን መግፋትም መጥላትም አያስፈልግም። ማንም በዘርም በሃይማኖትም ልዩነት መብበደል የለበትም። አባት ያጣው ሙስሊሙ ወገኔ ደግሞ የበለጠ ህመሙ ያመኛል። የኦሮሞው ሙስሊም ወንድሜ ነው። በዘር ልዩነት መገፋቱን አልሻም። የአማራው ሙስሊምም ወገኔ ነው። በማንም መበደሉን አልሻም። እንዲሁ መሻት! እነዚህን ብሄሮች የምጠቅሰው ለኔ ከሌሎች ብሄሮች የተለየ ቦታ ኖሯቸው ሳይሆን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ የሚናገረው ነገር ስላለ ነው።
ሳጠቃልል ማረጋገጫ የሌለውን ፅሁፍ ሐቂቃውን ለአላህ አሳልፈን ማራገቡን እንተወው እላለሁ። ችግሩ ግን አመንም አላመንም መሬት ላይ አለና ለመዘላለፍና ነጥብ ለማስቆጠር ሳይሆን አላህን ፈርተን ለመመካከር ስንል ትኩረት ሰጥተን እንስራበት።
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 5/2016)
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMunewor